የዴሞክራሲና የመልካም አስተዳደር ችግር የኢትዮጵያን 16 በመቶ የልማት ውጤት እንደሚያሳጣ ተነገረ

NEWS

4/6/20232 min read

በኢትዮጵያ ኢኮኖሚክስ አሶሴሽን የተከናወነ ሁሉን አቀፍ የልማት አመላካች ጥናት፣ የዴሞክራሲና የመልካም አስተዳደር ችግር 16 በመቶ የሚሆነውን የኢትዮጵያ ልማት ውጤት እንደሚያሳጣ፣ አመላከተ፡፡

በኢትዮጵያ ኢኮኖሚክስ አሶሴሽን አሰናጅነት መጋቢት 23 ቀን 2015 ዓ.ም. በተዘጋጀው የውይይት መድረክ ላይ የሥርዓተ ፆታ አለመመጣጠን እያስከፈለ ያለውን ዋጋ መሠረት በማድረግ ጥናት ያቀረቡት፣ የአሶሴሽኑ የሪሰርችና ፕሮግራም ዳይሬክተር ደግዬ ጎሹ (ዶ/ር)፣ 16 በመቶ የሚሆነው የኢትዮጵያ ልማት የሚታጣው በመልካም አስተዳደርና በዴሞክራሲ ችግር መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ደግዬ (ዶ/ር) አሶሴሽኑ በቅርቡ ያስተዋወቀው ሁሉን አቀፍ መለኪያ (Multi-Dimensional Index) እንቅስቃሴ መጀመሩን አስታውሰው፣ አዲሱ መመዘኛ ግንዛቤ ውስጥ ከሚያስገባቸው ጉዳዮች ውስጥ አንዱ አገር በማኅበራዊ ልማት፣ በዴሞክራሲና በመልካም አስተዳደር፣ በኢኮኖሚ ልማት የት ደርሷል የሚለው ይገኝበታል ብለዋል፡፡

የአንድ አገር ዘላቂ ዘርፈ ብዙ የልማት ዕድገት የኢኮኖሚ ዕድገትን፣ የማኅበራዊ ዕድገትን፣ የአካባቢ ጥበቃ ጉዳዮችን፣ ዴሞክራሲን፣ መልካም አስተዳደርን፣ የሥነ ፆታ እኩልነትን፣ የኢኮኖሚ ነፃነትን፣ የፖለቲካ ነፃነትን (የፖለቲካ መብቶችንና የመደራጀት ነፃነትን) ማሟላት እንደሚጠበቅበት በጥናቱ ተመላክቷል፡፡

ከኢትዮጵያ አንፃር ሲታይ የዴሞክራሲና የመልካም አስተዳደር ችግር ከፆታ እኩልነት ችግር በበለጠ እስከ 16 በመቶ የተመዘገበውን የልማት ውጤት እንደምታጣ ተገልጿል፡፡

‹‹ወደ 15 በመቶ የሚሆነው የልማት ጥረታችን የሚጠፋው በፆታ አለመመጣጠን፣ ሁሉንም ሴቶች ወደ ልማት ባለማስገባታችን፣ ከሥነ ተዋልዶ ጋር በተያያዘ፣ ሴቶች ገበያው ውስጥ ባለመሳተፋቸው ምክንያት ነው፤›› በማለት ደግዬ (ዶ/ር) አስረድተዋል፡፡

በአጠቃላይ 31 በመቶ የሚሆኑት የኢትዮጵያ የልማት ጥረቶች የሚጠፉት በሁለቱ (ዴሞክራሲና መልካም አስተዳደር፣ እንዲሁም በሥርዓተ ፆታ አለመመጣጠን) ምክንያቶች እንደሆነ የተናገሩት የኢኮኖሚ ተመራማሪው፣ ይህም የተረጋጋጠው የዘርፈ ብዙ የልማት አመላካች ጥናት ፕሮጀክት አንድ አካል በሆነው ጥናት ነው ብለዋል፡፡

ዘርፈ ብዙ የልማት መለኪያው አራት ዘርፎች (ኢኮኖሚ፣ ዴሞክራሲና መልካም አስተዳደር፣ ማኅበራዊ፣ ሥነ ፆታ)፣ 15 ምሰሶዎችን የሚለኩ 63 አመላካቾች (ኢንዲኬተርስ) ሲኖሩት፣ ኢኮኖሚው በስድስት ምሰሶዎች፣ ማኅበራዊ ዕድገት በአራት ምሰሶዎች፣ ዴሞክራሲና መልካም አስተዳደር በአራት ምሰሶዎች፣ እንዲሁም ቀሪው አንድ ምሰሶ የሥርዓተ ፆታ አለመመጣጠን የሚመዘንበት መሆኑ ተመላክቷል፡፡

የቀረበው የጥናት ግኝት ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ. በ2021 የሥርዓተ ፆታ አለመመጣጠን ከፍተኛ ልዩነት ፈጥሮባቸዋል ከሚባሉት አሥር አገሮች ዝርዝር ውስጥ አንዷ መሆኗን ያሳየ ሲሆን፣ በ2020 ደግሞ በሥርዓተ ፆታ አለመመጣጠን ምክንያት የኢኮኖሚ ዕድገታቸው ዝቅተኛ ከሆነባቸው አሥር አገሮች ዝርዝር ውስጥ እንደምትገኝበት አስታውቋል፡፡

የሥርዓተ ፆታ አለመመጣጠን በተመሳሳይ የአንድ አገር ማኅበራዊ ዕድገትን እንደሚገታ ያመላከተው ጥናቱ፣ እ.ኤ.አ. በ2020 ኢትዮጵያ አነስተኛ የማኅበራዊ ዕድገት ያላቸው በማለት ከዘረዘራቸው አገሮች ውስጥ አንዷ መሆኗን ጠቁሟል፡፡

በተመሳሳይ የሥርዓተ ፆታ እኩልነት አለመረጋገጥ በፈጠረው የዴሞክራሲ አስተዳደር እ.ኤ.አ. በ2020 ዝቅተኛ ነጥብ ከተሰጣቸው እንደ እነ አፍጋኒስታን፣ ሊቢያና ሱዳን ዝርዝር ውስጥ ኢትዮጵያ ትገኝበታለች የሚል ግኝት ቀርቧል፡፡

እ.ኤ.አ. ከ2017-18 ጀምሮ ያሉት የኢትዮጵያ የፀጥታ፣ የዴሞክራሲና የመልካም አስተዳደር ችግሮች በተዘዋዋሪ የአገሪቱን ልማት እንዳይፈጥን ማድረጋቸው ደግዬ (ዶ/ር) ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

የፆታ አለመመጣጠን ችግር እንዳለ ሆኖ ከዚያ በፊትም በሚታዩት የልማት ችግሮች፣ እንዲሁም በነበሩ አገራዊ ሁኔታዎች የተነሳ ከአፍሪካ አማካይ ደረጃ ሲታይ ኢትዮጵያ በጣም ወደ ታች እንደምትገኝ፣ በሁሉም ዘርፍ መልከ ብዙ የዕድገት መኮማተሮች ሁኔታ ላይ መገኘቷ ተገልጿል፡፡

በኢትዮጵያ እ.ኤ.አ. ከ2017 ጀምሮ በመልካም አስተዳደር፣ በማኅበራዊ (ትምህርት፣ ጤናና የመሳሰሉት)፣ በማክሮ ኢኮኖሚ (በገበያ፣ በኑሮ ሁኔታ) በሁሉም ዘርፈ ብዙ የሆነ ቀውስ መከሰቱን ሁሉም የሚያውቀው ነው የሚል አስተያየት የሰጡት ደግዬ (ዶ/ር) ይህም የጦርነቱ፣ የተለያዩ ግብዓቶችና የመልካም አስተዳደር ውጤት ነው ብለዋል፡፡

‹‹ትምህርት፣ ጤና፣ የመልካም አስተዳደር መቃወሶች የመጡት በአንድ ጊዜ አይደለም፡፡ በረዥም ጊዜ የሚመጡ በመሆናቸው የፖሊሲ ምላሾች ከሚሆኑት ውስጥ የአጭር ጊዜ ተብለው የሚወሰዱት ነገሮች ሲሆኑ፣ የዴሞክራሲና የመልካም አስተዳደር ችግሮች ይገኙበታል፡፡ ለሁለቱ ችግሮች በአጭር ጊዜ ውስጥ መፍትሔ ማምጣት ይቻላል፤›› ሲሉ ደግዬ (ዶ/ር) ገልጸዋል፡፡

ኢኮኖሚን ለማሻሻል የአጭር፣ የመካከለኛና የረዥም ጊዜ የፖሊሲ አማራጮችን አስቀምጦ መሥራት ይገባል የሚሉት የኢኮኖሚ ተመራማሪው፣ አሁን ባለው ነበራዊ ሁኔታ ማክሮ ኢኮኖሚውም ሆነ የመልካም አስተዳደር ችግር ውስጥ ከወደቁ የፖሊሲ ለውጥ አስፈላጊነትን አስረድተው፣ ፖሊሲን ለመለወጥ ደግሞ መጀመሪያ ችግሮቹ መታወቅ ይኖርባቸዋል ብለዋል፡፡

Related Stories