በኢትዮጵያ ከ4 ሚሊዮን በላይ የአገር ውስጥ ተፈናቃዮች መኖራቸው ተገለጸ

በኢትዮጵያ ከ4 ሚሊዮን በላይ የአገር ውስጥ ተፈናቃዮች መኖራቸው ተገለጸ

የዜና ትንታኔ

editors

8/23/2023

ከአራት ሚሊዮን በላይ ኢትዮጵያውያን በአገር ውስጥ ተፈናቅለው እንደሚገኙ የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ድርጅት አዲስ ያወጣው ሪፖርት አመለከተ።

ድርጅቱ በሁሉም ክልሎች ውስጥ ባደረገው ግምገማ መረዳት እንደቻለው ከ4.38 ሚሊዮን በላይ ኢትዮጵያውያን በአገር ውስጥ ተፈናቅለው ይገኛሉ።

ለኢትዮጵያውያኑ መፈናቀል ከቀረቡት ምክንያቶች መካከል ዋነኛው ግጭት ሲሆን፣ ድርቅ እና በማኅበረሰቦች መካከል የሚያጋጥም ውጥረትም ተጠቅሰዋል።

የመንግሥታቱ ድርጅት ተቋም ያወጣው ብሔራዊ የተፈናቃዮች ሪፖርት የሚሸፍነው ካለፈው ኅዳር እስከ ሰኔ ወር ያለውን ጊዜ ሲሆን፣ በጦርነት ውስጥ የቆየው የትግራይ ክልልም ከሁለት ዓመት በኋላ በሪፖርቱ ውስጥ ተካቷል።የመንግሥታቱ ድርጅት የሰብአዊ ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት እንዳለው፣ ከአገሪቱ ክልሎች በግጭት ምክንያት ከተፈናቀሉ መካከል ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎች የሚገኙት ትግራይ ክልል ውስጥ ነው።

ከግጭቶች ውጪ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ለተከታታይ ዓመታት ያጋጠመው ድርቅ ለበርካቶች መፈናቀል ሰበብ ሲሆን፣ የሶማሌ ክልል በርካታ የድርቅ ተፈናቃዮች የሚገኝበት ሆኗል።

በኢትዮጵያ ካሉ ተፈናቃዮች በተጨማሪ በተለያዩ ችግሮች ምክንያት ተጋላጭ የሆኑ 20 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን የምግብ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ቀደም ብሎ ያስታወቀ ሲሆን፣ ለዚህም 4 ቢሊዮን ዶላር ገንዘብ ያስፈልገኛል ብሎ ነበር።

ለበርካታ ሕዝብ መፈናቀል ምክንያት የሆነው የትግራይ ጦርነት ባለፈው ጥቅምት በተደረሰ ስምምነት የቆመ ሲሆን፣ተፈናቃዮችን ወደ ቀያቸው የመመለሱ ተግባር ገና መሆኑ እየተነገረ ነው።

ባለፉት ዓመታት በትግራይ ክልል የተካሄደውን ደም አፋሳሽ ጦርነትን ጨምሮ በተለያዩ አገሪቱ ክፍሎች ውስጥ ግጭቶች እየተካሄዱ ሲሆን፣ በዚህም ሳቢያ በርካታ ሰዎች ለመፈናቀል መዳረጋቸው ይታወቃል።

ከአራት ሚሊዮን በላይ ከሚሆኑት ተፈናቃዮች መካከል 66 በመቶ የሚሆኑት በግጭቶች ምክንያት መሆኑን ሪፖርቱ አመልክቷል።

በአሁኑ ወቅት ኦሮሚያ ክልል በመንግሥት ኃይሎች እና በታጣቂው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት መካከል ለዓመታት ሲካሄድ በቆየው ግጭት እና በሚፈጸሙ ጥቃቶች ስጋት ምክንያት ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎች ተፈናቅለው ይገኛሉ።

በቅርቡ በአማራ ክልል የተከሰተው ግጭት በክልሉ ውስጥ የሰላም መደፍረስ ከማስከተሉ በተጨማሪ የሰዎችን መፈናቀል ሊያስከትል ይችላል ተብሎ ተሰግቷል።

የአገር ውስጥ ተፈናቃዮችን ሁኔታ የሚከታተለው ተቋም ባለፈው ዓመት ባወጣው ሪፖርት መሠረት በኢትዮጵያ አምስት ሚሊዮን የአገር ውስጥ ተፈናቃዮች መኖራቸውን ገልጾ ነበር።

ይህም በዓለም ላይ በአንድ አገር ውስጥ ከተመዘገቡት የአገር ውስጥ ተፈናቃዮች ቁጥር ከፍተኛው እንደሆነ አመልክቶ እንደነበር ይታወሳል።