በአንዳንድ የአማራ ከተሞች እንቅስቃሴዎች መገታታቸውን እና የመከላከያ ሠራዊት መሰማራቱን ነዋሪዎች ተናገሩ
በአማራ ክልል መንግሥት “ሕግ ማስከበር” ያለውን ዘመቻ ተከትሎ በተፈጠረው ውጥረት የመከላከያ ሠራዊት ከወትሮው የተለየ ስምሪት ስጋት እንዳሳደረባቸው ነዋሪዎች ተናገሩ
የዜና ትንታኔ
በአማራ ክልል መንግሥት “ሕግ ማስከበር” ያለውን ዘመቻ ተከትሎ በተፈጠረው ውጥረት የመከላከያ ሠራዊት ከወትሮው የተለየ ስምሪት ስጋት እንዳሳደረባቸው ነዋሪዎች ተናገሩ።
በጎንደር፣ በደብረሲና እና በሸዋ ሮቢት ከተሞች የወትሮ እንቅስቃሴዎች መገታታቸውን እና ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የመከላከያ ሠራዊት አባላት መሰማራታቸውን ተናግረዋል።
ቢሆንም ግን ግጭት እና የተኩስ ድምጽ እምብዛም እንዳልሰሙ ቢቢሲ ያናገራቸው ነዋሪዎች ገልጸዋል።
ቢቢሲ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች ከዚህ ቀደም ጦርነት በተካሄደባቸው ከተሞች፣ አሁንም የፀጥታ ኃይል ከወትሮው የተለየ እንቅስቃሴ በተለይ በሕጻናት ላይ ከፍተኛ ድንጋጤን መፍጠሩን ተናግረዋል።
“ሕጻናቱ በጦርነቱ ወቅት የሰሙትን የጦር መሣሪያ ድምጽ፣ ያይዋቸውን የወታደር መኪኖች እና የጦር መሣሪያዎች ድጋሚ መመልከታቸው አስጨንቋቸዋል” ብለዋል።
ቢቢሲ ያነጋገራቸው በሰሜን ሸዋ፣ የሸዋ ሮቢት ከተማ ነዋሪ ከሚያዝያ 23/ 2015 ዓ.ም ቀን ከሰዓት ጀምሮ ከተማዋን የሚያቋርጡ እና በከተማዋ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ የትራንስፖርት አገልግሎቶች መቋረጣቸውን፣ ነገር ግን ዛሬ አርብ በአንጻሩ በከተማው ውስጥ የትራንስፖርት እንቅስቃሴ መመልከታቸውን ተናግረዋል።
እንደ ነዋሪው ከሆነምትምህርት ቤቶች፣ የመንግሥት ተቋማት፣ ባንኮች እና ሌሎች አገልግሎቶችም እንደተቋረጡ ናቸው።
በከተማዋ “ትጥቅ ለማስፈታት መከላከያ ቤት ለቤት ፍተሻ ማካሄዱን ተከትሎ” ተቃውሞ እንደነበር የገለጹት ማንነታቸው እንዲገለጽ ያልፈቀዱት ነዋሪው፣ በተፈጠረው ግጭትም ቁጥሩን በውል ባያውቁትም የሰዎች እና የእንስሳት ሕይወት መጥፋቱን፣ ቤቶች ላይም ጉዳት መድረሱን እንደሚያውቁ ተናግረዋል።
በከተማዋ ከትናንት በስቲያ ረቡዕ ተጨማሪ የመከላከያ ኃይል ከገባ በኋላ መንገድ ቢከፈትም፣ ደብረሲና ላይ ተቃውሞው በመቀጠሉ ዛሬም ድረስ መንገድ እንደተዘጋ ነዋሪው አክለዋል።
“የመከላከያ ሠራዊት አባላት አንዳንዴ በከተማዋ ውስጥ ይንቀሳቀሳሉ። ትናንት ቤት ለቤት ፍተሻ ነበር። ዛሬ ግን ይህ አይስተዋልም” ብለዋል።
በጎንደር ከተማም ከትናንት ሐሙስ ጀምሮ መሠረታዊ አገልግሎቶች መቋረጣቸውን ቢቢሲ ያነጋገራቸው ነዋሪ ገልጸዋል።
“ከትናንት ጀምሮ ወሳኝ ከሆኑ ከሆስፒታል፣ ከመድኃኒት ቤቶች፣ ምግብ መሸጫ ቤቶች ውጪ የትራንስፖርትም ሆነ የባንክ አገልግሎት የለም። መንገዶች ዝግ ናቸው” ብለዋል።ዛሬ አርብ በከተማዋ የተኩስ ድምጽ እንደማይሰማ የተናገሩት ነዋሪው፣ በከተማ የመከላከያ ኃይል ተሰማርቶ መመልከታቸውን ተናግረዋል።
ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ እና ቢቢሲ ያነጋገራቸው የደሴ ከተማ ነዋሪዎችም በከተማው ሰላማዊ እንቅስቃሴ ቢኖርም፣ የመከላከያ ኃይል አባላት ተሰማርተው መመልከታቸውን ገልጸዋል።
ነዋሪዎቹ፣ የሠራዊት አባላቱ የቤት ለቤት ፍተሻ እንደሚያደርጉ እና አንዳንዴም ፍተሻው ሌሊት ስለሚካሄድ የነዋሪውን ሰላማዊ ሕይወት እያወከ ነው ብለዋል።
ትናንት ከአዲስ አበባ ወደ ደሴ በአውሮፕላን እንደተጓዙ የገለጹልን ነዋሪም፣ ከአዲስ አበባ - ደሴ መንገድ በመዘጋቱ ተሽከርካሪዎች ደብረ ብርሃን ላይ ከቆሙ አራት ቀናት ተቆጥረዋል ብለዋል።
“ለንግድ ከአዲስ አበባ ያስጫንኩት ዕቃ እስካሁን ደሴ አልገባም። መኪኖቹ ደብረ ብርሃን ላይ እንደቆሙ ነው” ብለዋል ነዋሪው።
ይህም በከተማዋ የንግድ እንቅስቃሴ ላይ ተጽዕኖ እንዳሳደረ ተናግረዋል።
ከወራት በፊት የፌደራል መንግሥቱ የክልል ልዩ ኃይሎችን ወደ ሌሎች የፀጥታ መዋቅሮች እንዲቀላቀሉ ያሳለፈውን ውሳኔ ተከትሎ በአማራ ክልል ከተሞች ከፍተኛ ተቃውሞ ተቀስቅሶ እንደነበር ይታወሳል።
ተቃዋሚ ፓርቲዎች እና ነዋሪዎች “እርምጃው ውይይት ላይ መሠረት ያደረገ እና ጊዜውን የጠበቀ አይደለም። የክልሉ ሕዝብ ማንነት ተኮር ጥቃቶች እየተሰነዘረበት እና የፀጥታ ስጋት ባለበት ሰዓት የተፈፀመ ነው” ሲሉ መንግሥት የወሰደውን እርምጃ ተቃውመውት ነበር።
በኋላም ፌደራል መንግሥቱ እርምጃው በሁሉም ክልሎች ላይ ተፈፃሚ እንደሚሆን የገለጸ ሲሆን፣ የሌሎች ክልሎች ርዕሳነ መስተዳድሮችም ውሳኔውን መቀበላቸውን ማስታወቃቸው አይዘነጋም።
ውጥረቱ ረገብ ብሎ ከቆየ በኋላም የብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል እና የአማራ ክልል ብልጽግና ጽ/ ቤት ኃላፊ ባለፈው ሳምንት ሚያዝያ 19/2015 ዓ.ም. መገደላቸውን ተከትሎ መንግሥት “ጽንፈኛ” ያላቸው ኃይሎች ላይ የሕግ ማስከበር ዘመቻ እንደሚጀምር አስታውቆ ነበር።
ይህንንም ተከትሎ የመከላከያ ሠራዊት አባላት ወደ ተለያዩ አካባቢዎች መሰማራታቸውን ነዋሪዎች ለቢቢሲ ገልጸዋል።
በአንዳንድ የክልሉ አካባቢዎችም በታጣቂ ኃይሎች፣ በወጣቶች እና በሠራዊቱ መካከል በተፈጠረ ግጭት የሰላማዊ ሰዎች ሕይወት ማለፉንና ጉዳት መድረሱ ተገልጿል።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ትናንት ሐሙስ ሚያዝያ 26/2015 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ በአማራ ክልል በሚገኙ የተለያዩ አካባቢዎች ውስጥ በመከላከያ ሠራዊት እና በታጣቂዎች መካከል ግጭት መኖሩን እና በሰው ሕይወት ላይ ጉዳት መድረሱን አስታውቋል።
ከዚህ “የሕግ ማስከበር ዘመቻ” ጋር በአማራ ክልል በሰሜን ጎንደር፣ በሰሜን ወሎ እና በሰሜን ሸዋ ዞኖች አንዳንድ አካባቢዎች በመከላከያ ሠራዊት እና በታጣቂዎች መካከል ግጭት መካሄዱን ኢሰመኮ አመልክቷል።
መንግሥት በአማራ ክልል የተወሰኑ አካባቢዎች እያካሄደ ያለውን “የሕግ ማስከበር ዘመቻ” በሰብአዊ መብቶች ላይ ያለውን አንድምታ እና ተጽእኖ በቅርበት እየተከታተለ መሆኑንም ገልጿል።
የፌደራል መንግሥትም ሆነ የአማራ ክልል መስተዳድር ተከሰተ ስለተባለው ግጭት እና ስለደረሰው ጉዳት እስካሁን ያሉት ነገር የለም።