በአማራ ክልል አርሶ አደሮች በምርጥ ዘር እና በማዳበሪያ እጦት ለተቃውሞ አደባባይ ወጡ

በአማራ ክልል የሚገኙ አርሶ አደሮች በምርጥ ዘር እና በአፈር ማዳበሪያ እጦት ምክንያት ለተከታታይ ቀናት በክልሉ መዲና ባሕርዳር እና በሌሎችም አካባቢዎች የተቃውሞ ሰልፍ አካሄዱ።

የዜና ትንታኔ

editors

6/2/2023

በአማራ ክልል የሚገኙ አርሶ አደሮች በምርጥ ዘር እና በአፈር ማዳበሪያ እጦት ምክንያት ለተከታታይ ቀናት በክልሉ መዲና ባሕርዳር እና በሌሎችም አካባቢዎች የተቃውሞ ሰልፍ አካሄዱ።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው እና ከተለያዩ ወረዳዎች ወደ መዲናዋ ለተቃውሞ ያቀኑት አርሶ ደሮች፣ የእርሻ መሬታቸውን አዘጋጅተው ቢጠባበቁም ምርጥ ዘር እና ማዳበሪያ ማግኘት አለመቻላቸውን ተናግረዋል።

“ማዳበሪያ በስኒ ሳይቀር ተለክቶ በዕጣ እየተከፋፈለ ነው። አስካሁን እንደዚህ አይነት የባሰ ችግር ገጥሞን አያውቅም” ይላሉ።

በዚህም ምክንያት አደባባይ በመውጣት፣ በክልሉ ርዕሰ መስተዳድሩ ቢሮ እንዲሁም በግብርና ቢሮ በመገኘት ያለባቸውን ችግር ለማስረዳት መገደዳቸውን፤ ነገር ግን አጥጋቢ ምላሽ እንዳላገኙ አስረድተዋል።

“ዘርም፣ ማዳበሪያም የለም። ሁሉም ነገር በነጋዴ ነው። የምናደርገው ጠፋን” ሲሉም ምክንያታቸውን አስረድተዋል።

አርሶ አደሮች የአፈር ማዳበሪያ አቅርቦትን በተመለከተ ቅሬታቸውን ሲያሰሙ ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ አይደለም።

ባለፈው ዓመትም ከማዳበሪያ ዋጋ መናር እና እጥረት ጋር ተያይዞ የደረሰባቸውን በደል ለቢቢሲ ገልጸው ነበር።

ይህንን በተመለከተ ያነጋገርናቸው የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አምሳሉ ጎባው፣ በክልሉ አርሶ አደሮች የሚፈልጉት የምርጥ ዘር ዓይነቶች ካልሆነ በስተቀር የምርጥ ዘር ችግር አቅርቦት አለመኖሩን ገልጸው፤ ነገር ግን የማዳበሪያ እጥረት ማጋጠሙን አረጋግጠዋል።

አቶ አምሳሉ እንዳሉት በዚህ ዓመት ክልሉ ካቀረበው 9.2 ሚሊየን ኩንታል የማዳበሪያ ፍላጎት በግብርና ሚኒስቴር 5.2 ሚሊየን ኩንታል ግዥ ተፈፅሞለታል።

ይሁን እንጂ በተለያየ ምክንያት [በፀጥታ ችግር፣ በጎርፍ . . . ] እስካሁን ወደ ክልሉ መግባት የቻለው 1.9 ሚሊየን ኩንታል ኤንፒኤስ እና ዩሪያ የተባሉ ማዳበሪያብቻ ነው።

በመሆኑም “ባለፈው ዓመት የገባውን ጨምረን 2.2 ሚሊየን ኩንታል ማዳበሪያ ለአርሶ አደሩ ለማሠራጨት ያለ እረፍት እየሠራን ነው” ብለዋል ኃላፊው።

ኃላፊው ይህን ይበሉ እንጂ አርሶ አደሮቹ የገባው ማዳበሪያም ቢሆን በነጋዴ እጅ እንዳለ እና ለዚህም እስከ አምስት ሺህ ብር እየተጠየቁ እንደሆነ ይከሳሉ።

ቅሬታቸውን ለግብርና ቢሮ እና ለርዕሰ መስተዳድሩ ቢሮ ማቅረባቸውን የገለጹት አርሶ አደሮቹ የተሰጠን ምላሽ ግን የተለያየ ነው ይላሉ።

በግብርና ቢሮ በኩል “ይመጣላችኋል ታገሱ። ሕገ ወጥ ነጋዴዎችን እራሳችሁ ያዟቸው” የሚል መልስ እንደተሰጣቸው ገልጸዋል።

“መጀመሪያ ይህ ማዳበሪያ እንዴት በነጋዴ እጅ ሊገባ ቻለ? ይህንንስ መፍታት የእኛ ኃላፊነት ነውን?” ሲሉም ይጠይቃሉ።

የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው አቶ አምሳሉም ማዳበሪያ በነጋዴ እጅ መግባቱን አረጋግጠው፣ በአሃዝ ጠቅሰው ዝርዝር ማብራሪያ ባይሰጡም እስካሁንም ከማዳበሪያ ሕገ ወጥ ሽያጭ ጋር በተያያዘ በቁጥጥር ሥር የዋሉ አካላት መኖራቸውን ገልጸዋል።

በክልሉ ርዕሰ መስተዳዳር ቢሮም በኩልም “የአቅርቦት ችግር እንደሌለ እና የዞን እና የወረዳ የአሰራር ቅንጅት ችግር መሆኑን እንደገለጹላቸው እና በ24 ሰዓት ውስጥ ይህንን የሚያሳልጥ ቡድን አዋቅረው ችግራቸውን እንደሚፈቱላቸው” እንደገለጹላቸው አርሶ አደሮቹ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

“በሬ አቁመን ስንጓለል [ስንንከራተት] ነው የምንውለው”

ሰኞ ዕለት ጀምረው ማሽላ ለመዝራት ተዘጋጅተው እንደነበር የሚናገሩት አርሶ አደር አማረ፣ ባለው የዘር እና የማዳበሪያ እጦት ምክንያት ተስፋቸው እየተሟጠጠ እንደሆነ ይናገራሉ።

“ያልሄድንበት የለም። እንደ ‘ኩታራ’ [ልጅ] መዝለል ነው እንጂ ምን መልስ አለው? በሬ አቁመን ስንጓለል [ስንንከራተት] ነው የምንውለው። ምን ተስፋ አለው? ተስፋም የለው” ይላሉ አርሶ አደር አማረ ተስፋ በመቁረጥ።

“ማዳበሪያ ከ50 አርሶ አደር ለ15 አርሶ አደር በዕጣ እንዲደርሰው እየተደረገ ነው። በዕጣ ያላገኘም ተራህን ጠብቅ እየተባለ ነው” ብለዋል እኝህ አርሶ አደር የደረሰባቸውን ሲያስረዱ።

ባለፉት ቀናት ከተደረጉ ሰልፎች በአንደኛው ላይ እንደነበሩ የገለጹልን ሌላኛው የባሕርዳር ዙሪያ ወረዳ አርሶ አደር ይሁን አዲስ በበኩላቸው፣ ዘር እና ማዳበሪያ እናገኛለን በሚል መሬታቸውን አለስልሰው ለዘር ቢያዘጋጁም ያገኙት ነገር እንደሌለ ይናገራሉ።

በዘንድሮው ዓመት ጥሩ ምርት ለመሰብሰብ ትራክተር ተከራይተው መሬታቸውን እንዳረሱ የሚናገሩት እኝህ አርሶ አደር፣ “ወይ ሳናርሰው ለከብቶች ግጦሽ አልሆነን፣ ወይ አልዘራንበት ባዶ ቀርተናል” ብለዋል በቁጭት።

“የሚሸጥ ነጋዴ ካለም ያዙት” የሚል ምላሽ እንደተሰጣቸው የተናገሩት አርሶ አደሮቹ፣ “እነሱ ምን ሥራ ይዘው ነው ማዳበሪያው ነጋዴ እጅ የገባው? ከየት አግኝቶ ነው ነጋዴ የሚሸጠው?” ሲሉም ተጠያቂነትን ያነሳሉ።የማዳበሪያ ችግር ለምን መፍታት አልተቻለም?

አቶ አምሳሉ በአገሪቷ ውስጥ የማዳበሪያ ፋብሪካ አለመኖሩ እና በፌደራል ደረጃ በሚካሄደው የማዳበሪያ ግዢ እና በማጓጓዝ ሒደት የሚያጋጥመው መጓተት ዋነኛው ምክንያት ነው ይላሉ።

ክልሉ የአርሶ አደሩን ፍላጎት ሰብስቦ ዕቅዱን ለፌደራል ከማቅረብ ውጪ ሌላ ሥልጣን እንደሌለው የገለጹት ኃላፊው፣ በተለያዩ ምክንያቶች በሚያጋጥሙ ተግዳሮቶች ችግሩ መከሰቱን ያስረዳሉ።

“አርሶ አደሮች የሚያነሱት ፍላጎት ትክክል ነው። እኛ ማድረግ የሚገባን ያለውን ማሰራጨት ነው። ይህንንም ለማድረግ ቢሮው ይህንን የሚከታተል አመራር መድቦ እየሠራ ነው” ብለዋል።

መጀመሪያ ላይ ሁሉንም ዓይነት ሰብሎች ለሚዘሩ አርሶ አደሮች ማዳበሪያ ተሰራጭቶ ነበር ያሉት ኃላፊው፣ እጥረቱ ከተከሰተ በኋላ የሚመጡ ማዳበሪያዎችን ቅድሚያ በቆሎ ለሚዘሩ አካባቢዎች እያሰራጩ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ሆኖም አሁንም መሠረታዊ ችግሮች መኖራቸውን አልካዱም።

“ችግሩ ታውቋል። የእኛ ቢሮ ኃላፊዎችም እየተነጋገሩ ነው። አገሪቱ በምትችለው አቅም በቅርብ ጊዜ መፍትሔ ይመጣል ብለን ተስፋ እናደርጋለን” ብለዋል።

ኢትዮጵያ 12.8 ሚሊየን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ግዢ መፈፀሟን ባለፈው ዓመት የግብርና ሚኒስቴር አስታውቆ ነበር።

ይሁን እንጂ ይህ ቁጥር ከቀደመው ዓመት ጋር ሲነጻጻር በ5 ሚሊየን ኩንታል ያነሰ ሲሆን፣ የተፈፀመው ግዢ ካለው ፍላጎት 70 በመቶው ብቻ መሆኑ ተገልጾ ነበር።