በደጀን ከተማ በተቃውሞ መንገድ በመዘጋቱ፤ የሀገር አቋራጭ ትራንስፖርት አገልግሎት ተቋረጠ

የዜና ትንታኔአበይት ጉዳይ

4/7/20232 min read

በአማራ ክልል ምስራቅ ጎጃም ዞን ወደምትገኘው ደጀን ከተማ የሚያስገባው መንገድ የተዘጋው፤ “የክልሉ ልዩ ኃይል መበተንን በሚቃወሙ ነዋሪዎች” እንደሆነ የከተማዋ የሰላም እና ጸጥታ አስተዳደር ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አንዳርጌ ዘውዱ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። የደጀን ከተማ ወጣቶች ተቃውሟቸውን ማሰማት የጀመሩት ከትላንት አርብ ከሰዓት ጀምሮ መሆኑን ኃላፊው ገልጸዋል።

ከቀኑ አስር ሰዓት ገደማ ላይ ተቃውሞ የሚያሰሙ ነዋሪዎች፤ ወደ ከተማዋ የሚያስገባው መንገድ ላይ ድንጋይ በማስቀመጥ የተሽከርካሪዎች ፍሰት እንዲቆም ማድረጋቸውን ኃላፊው አስታውቀዋል። የከተማዋ ኮሚዩኒኬሽን ቡድን መሪ አቶ ሞኙ ሆዴ አሳየ በበኩላቸው፤ ከደጀን ከተማ መግቢያ በተጨማሪ በከተማው የሚያልፈው መንገድ መዘጋቱንም አስረድተዋል።

“ገበያ የመጣውም ህዝብ እንዲመለስ ተደርጓል። ሱቅም ተዘግቷል። የሰው እንቅስቃሴ አለ፤ ወጣቱ ላይ ታች ይላል። የንግድ እንቅስቃሴ ግን የለም። ቅዳሜ በርካታ ህዝብ ገበያውን የሚያሳልጥበት ቀን ነው። ግን ዛሬ አንድም የለም

በትላንቱ ተቃውሞ “የፌደራል ፖሊስ ንብረት የሆነ አንድ ‘ፒክ አፕ’ ተሸከርካሪ ተቃጥሏል” የሚል መረጃ እንደደረሳቸው የሚናገሩት የደጀን ከተማ የሰላም እና ጸጥታ አስተዳደር ጽህፈት ቤት ኃላፊ፤ ድርጊቱን የፈጸመው አካል ማንነት ግን ገና አልተረጋገጠም ብለዋል። “የትኛው ነው ያቃጠለው? ‘ወጣቱ ነው ወይስ ለመንግስትም ለህዝብም አልመች ያለ ጠላት ነው?’ የሚለውን ነገር አልደረስንበትም” ሲሉም አክለዋል።

በደጀን ከተማ የተቀሰቀሰው ተቃውሞ በዛሬውም ዕለት መቀጠሉን፤ ሁለቱ የከተማይቱ የስራ ኃላፊዎች እና የከተማይቱ ነዋሪዎች ገልጸዋል። በተቃውሞው ምክንያትም ዛሬ ቅዳሜ ወደ ከተማዋ የመጣ ሀገር አቋራጭ ተሽከርካሪ አለመኖሩን የከተማዋ ኮሚዩኒኬሽን ቡድን መሪ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።

“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ያነጋገረቻቸው የዘመን እና የዋልያ ሀገር አቋራጭ የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች፤ መንገድ በመዘጋቱ ምክንያት በዛሬው ዕለት ወደ ባህር ዳር ከተማ አውቶብሶችን አለማሰማራታቸውን አስታውቀዋል። ወደ ባህር ዳር ከተማ ለሚደረግ ጉዞ የተሳፋሪዎች ትኬት እየቆረጡ አለመሆኑን የገለጹት የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎቹ፤ አውቶብሶቻቸው ዳግም በዚያ መስመር አገልግሎት መስጠት የሚቀጥሉት መንገዱ መከፈቱን ሲያረጋግጡ እንደሆነ አመልክተዋል።

በደጀን ከተማ በኩል ከሚያልፉ ተሽከርካሪዎች ባሻገር፤ በከተማይቱ የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ይሰጡ የነበሩ የባለሶስት እግር “ባጃጅ” ተሽከርካሪዎች በዛሬው ዕለት ከስራ ውጭ ሆነው መዋላቸውን የከተማይቱ ኃላፊዎች ተናግረዋል። የከተማይቱ የኮሚዩኒኬሽን ቡድን መሪ አቶ ሞኙ ሆዴ፤ በደጀን በየሳምንቱ ይካሄድ የነበረው የቅዳሜ ገበያ በዛሬው ዕለት ሳይከናወን መቅረቱን ጨምረው ገልጸዋል። “ገበያ የመጣውም ህዝብ እንዲመለስ ተደርጓል። ሱቅም ተዘግቷል። የሰው እንቅስቃሴ አለ፤ ወጣቱ ላይ ታች ይላል። የንግድ እንቅስቃሴ ግን የለም። ቅዳሜ በርካታ ህዝብ ገበያውን የሚያሳልጥበት ቀን ነው። ግን ዛሬ አንድም የለም” ሲሉ በደጀን ከተማ ያለውን ሁኔታ አስረድተዋል።

የደጀን ከተማ አስተዳደር በከተማይቱ ውስጥ የሚገኙ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች እና “ተሰሚነት አላቸው” በተባሉ ወጣቶች አማካኝነት፤ የነዋሪዎችን ተቃውሞ ለማረጋጋት ጥረት እያደረገ መሆኑን የሰላም እና ጸጥታ አስተዳደር ጽህፈት ቤት ኃላፊው አቶ አንዳርጌ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። በእነዚህ አካላት በኩል የሚደረገው ንግግር፤ በከተማይቱ በተነሳው ተቃውሞ ሰዎች እንዳይጎዱ የማድረግ ዓላማ ያለው መሆኑንም ኃላፊው አስረድተዋል።

የአማራ ክልል መንግስት ትላንት አርብ መጋቢት 29፤ 2015 ባወጣው መግለጫ፤ የክልሉ ልዩ ኃይልን በሚመለከት የሚሰራጩ “ሀሰተኛ መረጃዎች” የክልሉን ህዝብ “በተጨባጭ እየረበሸ” መሆኑን አስታውቆ ነበር። እነዚህ መረጃዎች “የአማራ ክልል ልዩ ኃይል አየር ላይ እንዲበተን እየተደረገ ነው” ሲሉ ቢወነጅሉም፤ የክልሉም ሆነ የፌደራል መንግስት ግን አሁን እየተደረገ ያለው እንቅስቃሴ “የልዩ ኃይሎች መልሶ የማደራጀት ስራ ነው” ሲሉ ያስተባብላሉ። ሁለቱም አካላት በየፊናቸው ባወጡት መግለጫ፤ የ“መልሶ ማደራጀት ስራው” የልዩ ኃይል አባላትን ወደ መከላከያ ሰራዊት፣ የፌደራል ፖሊስ አሊያም ወደ ክልል ፖሊስ የማስገባት አካሄድ እንደሆነ አስታውቀዋል።

የልዩ ኃይል አወቃቀርን የሚያፈርሰውን ይህን የመንግስት ውሳኔ፤ በአማራ ክልል በስፋት የሚንቀሳቀሰው የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄን (አብን) አጥብቆ ተቃውሞታል። የአማራ ክልልን ልዩ ኃይል “ያለ በቂ ዝግጅት፣ ውይይት፣ የጋራ መግባባትና መተማመን ሳይደረስ፤ በድንገት እና ያለበቂ የጸጥታ ዋስትና ለማፍረስ መንግስት ያሳለፈው ውሳኔ እና ውሳኔውን ለማስፈጸም እየሄደበት ያለው መንገድ ኃላፊነት የጎደለው ነው” ሲል አብን ከትላንት በስቲያ ሐሙስ ባወጣው መግለጫ ተችቷል። የመንግስት እርምጃ የአማራ ክልልንም ሆነ ኢትዮጵያን “ወደ ሌላ የቀውስ አዙሪት የሚከት አደገኛ አካሄድ ነው” ያለው አብን፤ ገዢው ፓርቲ ውሳኔውን በአፋጣኝ እንዲቀለብስ ጥሪ አቅርቦ ነበር። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)

Related Stories