በአማራ ክልል በመከላከያ ሠራዊት እና በታጣቂዎች መካከል ግጭቶች መቀጠላቸው ተነገረ
በአማራ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች በታጠቁ ሚሊሻዎች፣ ፋኖ እና በመከላከያ ሠራዊት መካከል የሚደረጉ ግጭቶች መቀጠሉን ነዋሪዎች እየተናገሩ ነው።
አበይት ጉዳይየዜና ትንታኔ
በአማራ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች በታጠቁ ሚሊሻዎች፣ ፋኖ እና በመከላከያ ሠራዊት መካከል የሚደረጉ ግጭቶች መቀጠሉን ነዋሪዎች እየተናገሩ ነው።
በታሪካዊቷ ከተማ ጎንደር አዘዞ እና ማራኪ አካባቢዎች በዛሬው ዕለት (ሐሙስ) እኩለ ቀን ድረስ የተኩስ ድምጽ እየተሰማ መሆኑን ቢቢሲ ያነጋገረው የከተማዋ ነዋሪ ገልጸዋል።
በጎንደር ከተማ አውሮፕላን ማረፊያ አካካቢም ግጭት በመፈጠሩ የትራንስፖርት አገልግሎት መቆሙን ነዋሪዎች ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ይሁንና በከተማዋ ማዕከል በተለይም በተለምዶ ፒያሳ እና አራዳ በሚባሉት አካባቢዎች መደበኛ እንቅስቃሴ እየተከናወነ መሆኑን ነዋሪው ገልጸዋል።
በመከላከያ ሠራዊት እና በታጠቁ ሚሊሻዎች፣ ፋኖ መካከል “ከባድ ግጭት” ከትናንት በስቲያ ማክሰኞ እና ትናንት ረቡዕ እንደነበር የተዘገበባት ከታሪካዊቷ ላሊበላ ከተማ 25 ኪሎሜትር ርቆ በሚገኘው አየር ማረፊያ በዛሬው ዕለት ወታደራዊ እንቅስቃሴም ሆነ የተኩስ ድምጽ እየተሰማ እንዳልሆነም ቢቢሲ ከነዋሪዎች ሰምቷል።
በግጭቱ ምክንያት በላሊበላ አየር ማረፊያ በረራዎች መስተጓጎላቸውን እና የላሊበላ ሹምሽሃ አውሮፕላን ማረፊያ በፋኖ ታጣቂዎች ስር ገብቶም እንደነበር ተገልጿል።
ፋኖ ከትናንት በስቲያ ተቆጣጥሮታል የተባለው የላሊበላ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ አሁም በስሩ እንደሚገኝ እና በረራዎች እየተደረጉ እንዳልሆነ ቢቢሲ ያነገጋገራቸው የከተማዋ ነዋሪ አስረድተዋል።
በላሊበላ አየር ማረፊያ ስለተከሰተው ሁኔታ ከኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅት እና ከኢትዮጵያ አየር መንገድ መረጃ ለማግኘት ቢቢሲ ያደረገው ጥረት እስካሁን አልተሳካም።
በሌላ በኩል ላሊበላን ጨምሮ ወደ አማራ ክልል የሚደረጉ የአውሮፕላን የዛሬ በረራዎች መሰረዛቸውንም ቢቢሲ ለአየር መንገዱ ቅርበት ካለው ምንጭ እና ከመንገደኞች ለመረዳት ችሏል።
እንዲሁም አየር መንገዱ በኢንተርኔት አማካኝነት ሽያጭ የሚያደርግበት መተግበሪያ ላይ የላሊበላን ጨምሮ በአማራ ክልል ያሉ አራት መዳረሻዎች በዛሬው ዕለት በረራ እንደሌለ ያሳያሉ።
ማክሰኞ ዕለት ወደ ላሊበላ የተጓዘው አውሮፕላን መንገደኞችን ከመድረሻቸው ሳያወርድ መመለሱ ይታወሳል።
ከወልዲያ ወደ ባሕርዳር በሚወስደው ዋና መንገድ ላይ በተለይም ስታይሽ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የተኩስ ልውውጥ እየተደረገ እንዳለም ቢቢሲ ከነዋሪዎች ሰምቷል።
በአካባቢው ተጨማሪ የሠራዊት እንቅስቃሴ ስለመኖሩ የሚናገሩት ነዋሪዎች ከወልዲያ ባሕርዳር ባለው መንገድም የትራንስፖርት እንቅስቃሴ መገደቡን ገልጸዋል።
በጎጃምም በተመሳሳይ መልኩ የተለያዩ ከተሞች መንገዶች መዘጋታቸውን የሚናገሩት ነዋሪዎች፣ መንገዶች በተለየ ሁኔታ የተዘጉባቸው አካባቢዎች በውል ባይታወቁም እንቅስቃሴዎች መስተጓጎላቸውን ካነጋገርናቸው ነዋሪዎች ማረጋገጥ ችለናል።
በላሊበላ የኢንተርኔት አገልግሎት ሙሉ በሙሉ መቋረጡንም ነዋሪዎች ገልጸዋል።
የአማራ ክልል መቀመጫ ባሕርዳርን ጨምሮ በክልሉ በሚገኙ አምስት ከተሞች የሞባይል የዳታ ኢንተርኔት አገልግሎት መቋረጡን ቢቢሲ ያናገራቸው ነዋሪዎች ገልጸዋል።በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት እና የፋኖ ታጣቂዎች በደቡብ ጎንደር ዞን ዋና ከተማ ደብረ ታቦር አቅራቢያ ረቡዕ እና ሐሙስ ግጭት መካሄዱን ሮይተርስ ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ የሕክምና ባለሙያ እና ፖሊስን ዋቢ አድርጎ ዘግቧል።
የሕክምና ባለሙያው በተኩስ እና በከባድ መሳሪያዎች ሦስት ከባድ የአካል ጉዳት እንዲሁም 10 ቀላል የአካል ጉዳት የደረሰባቸውን ግለሰቦች እያከመ እንደሆነ መግለጻቸውን ተዘግቧል።
ግጭቶች ከከተማዋ ወጣ ባሉ ስፍራዎች መቀጠሉን የተናገሩት የሕክምና ባለሙያው ወደ ደብረ ታቦር የሚወስደው መንገድ መዘጋቱንም ተናግረዋል።
በተጨማሪ ሁለት የቆቦ ነዋሪዎችም ማክሰኞ ማለዳ ላይ ከከተማዋ ወጣ ብሎ ከሚገኝ ስፍራ ከባድ ውጊያ እንደሰሙ ለዜና ወኪሉ የተናገሩ ሲሆን፣ ረቡዕ ግን ሁኔታው በተወሰነ መልኩ መረጋጋቱን ተናግረዋል።
ፋኖን የሚደግፉ ተቃዋሚዎች የመከላከያ ሠራዊቱን እንቅስቃሴ ለማደናቀፍ በድንጋይ እና በዛፍ መንገዶች መዝጋታቸውን በተለያዩ ማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ የወጡ ምስሎች አሳይተዋል።
ከቡድኑ ጋር ግንኙነት ያላቸው ሚዲያዎች እና አክቲቪስቶች ፋኖ በርካታ ከተሞችን እና መንደሮችን መቆጣጠራቸውን ተናግረዋል።
ቢቢሲ ፋኖ ከተሞችን ተቆጣጥሯል መባሉን በገለልተኛነት ማረጋገጥ አልቻለም። በአንዳንድ ከተሞች ማረሚያ ቤቶች እና የፖሊስ ጣቢያዎች እየተሰበሩ መሆናቸውን መረጃዎች አመልክተዋል።
ከወራት በፊት በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች የተቀሰቀሰው ግጭት ከሰሞኑ እንደ አዲስ አገርሽቷል። በክልሉ አንዳንድ አካባቢዎች ከሦሰት ቀናት በፊት እንደ አዲስ የተቀሰቀሰው ግጭት አሁንም ተባብሶ መቀጠሉን ቢቢሲ ያናገራቸው የየአካባቢው ነዋሪዎች አረጋግጠዋል።
በክልሉ ከወራት በፊት የልዩ ኃይልን እንደገና መዋቀር መነሻ በማድረግ የተቀሰቀሰውን ግጭት በሰላማዊ መንገድ መፍታት እንደሚገባ የክልሉ ምክር ቤት ከሳምንታት በፊት ያነሳ ሲሆን ርዕሰ መስተዳድር ይልቃል ከፋለም (ዶ/ር) ሃሳቡን በአወንታ ተቀብለውት የሰላ ምጥሪ አቅርበው ነበር።
አዲስ ያገረሸው ግጭት ከመነሳቱ አንድ ቀን ቀደም ብሎም ርዕሰ መስተዳድሩ ከአገር ሽማግሌዎች እና ከሃይማኖት መሪዎች ጋር የፀጥታ ችግሮች በሰላማዊ መንገድ በሚፈቱበት ዙሪያ ተወያይተዋል።
በሌላ በኩል የመከላከያ ሠራዊት ከቀናት በፊት በሰጠው መግለጫ በፋኖ ስም በሚንቀሳቀሱ ኃይሎች ላይ እርምጃ መውሰዱን እንደሚቀጥል አስጠንቅቋል።
ግጭቱን ተከትሎ ርዕሰ መስተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ/ር) ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ መፍታት አሁንም አስፈላጊ መሆኑን ጥሪ አቅርበዋል።
ለክልሉ የቴሌቪዥን ጣቢያ በሰጡት መግለጫ ርዕሰ መስተዳድሩ አክለውም “የሕግ ማስከበር ሥራውን ለማስቀጠል ሕብረተሰቡ ትብብር ሊያደርግ ይገባል” ብለዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ደግሞ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ ባጋሩት መልዕክት “በአማራ ክልል እያጋጠሙ የሚገኙ የፀጥታ ችግሮች አሳሳቢ እየሆኑ መጥተዋል” ብለዋል።
መፍትሄውም “የሁሉም ዋስትና የሆነውን ሕግ እና ሥርዓት በተሟላ መልኩ ማክበር እና ማስከበር” መሆኑንም አቶ ደመቀ ጠቅሰዋል።