“ሸኔ” በተባሉ ታጣቂዎች ሰንበቴ ላይ ተከፈተ በተባለ ጥቃት ሰዎች መገደላቸው ተነገረ
የዜና ትንታኔ
ትላንት በዐማራ ክልል የኦሮሞ ብሔረሰብ ዞን ሰንበቴ አቅራቢያ፣ ታጣቂዎች ፈጸሙት በተባለ ጥቃት፣ ሰዎች መሞታቸውን፣ ከጥቃቱ የተረፉ የዐይን እማኞች ተናገሩ፡፡
ጥቃቱ በተፈጸመበት ሥፍራ እንደነበሩ የተናገሩት አስተያየት ሰጪዎቹ፣ በአኹኑ ወቅት ሕይወታቸውን ለማትረፍ ጫካ ውስጥ ተሸሽገው እንደሚገኙ ጠቅሰው፣ እስከ ዛሬ እኩለ ቀን ድረስ ምንም ዐይነት መንግሥታዊ አካል እንዳልደረሰላቸው ተናግረዋል፡፡
ጥቃቱን የሰነዘረው፣ “ኦነግ ሸኔ” ብለው የጠሩት ታጣቂ መኾኑን አስተያየት ሰጪ ገልጸዋል፡፡ ለዚኽም እንደ ማስረጃ ያቀረቡት፣ ታጣቂ ቡድኑ፣ “በአካባቢው ተደጋጋሚ ጥቃት ሰንዝሯል፤ ወታደራዊ እንቅስቃሴም ያደረጋል፤” በሚል ነው፡፡
ኾኖም፣ የታጣቂ ቡድኑ ዓለም አቀፍ ቃለ አቀባይ እና በዩናይትድ ስቴትስ ቨርጂኒያ የሚኖሩት ኦዳ ተርቢ፣ ታጣቂዎቻቸው በጥቃቱ እጃቸው እንደሌለበት አስተባብለዋል።