ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ ስለወልቃይት የወደፊት ዕጣ እና ስለሚቀርብባቸው ክስ ምን ይላሉ?

ወታደራዊ መንግሥትን በትጥቅ ትግል የጣለው ኢሕአዴግ የአገሪቱን የአስተዳደር አወቃቀር ቋንቋ እና ማንነትን መሠረት ወዳደረገ ፌደራላዊ አወቃቀር ሲቀይር የማንነት ጥያቄ ከተነሳባቸው አካባቢዎች መካከል ወልቃይት/ምዕራብ ትግራይ አንዱ ነው።

አበይት ጉዳይየዜና ትንታኔ

editors

6/19/2023

ወታደራዊ መንግሥትን በትጥቅ ትግል የጣለው ኢሕአዴግ የአገሪቱን የአስተዳደር አወቃቀር ቋንቋ እና ማንነትን መሠረት ወዳደረገ ፌደራላዊ አወቃቀር ሲቀይር የማንነት ጥያቄ ከተነሳባቸው አካባቢዎች መካከል ወልቃይት/ምዕራብ ትግራይ አንዱ ነው።

ከአዲሱ አወቃቀር ቀደም ብሎ በጎንደር ክፍለ አገር ሥር የነበረው የወልቃይት ጠገዴ አካባቢ፣ ወደ ትግራይ ክልል ተካቶ ምዕራብ ትግራይ በመባል ለሦስት አስርት ዓመታት ለሚጠጋ ጊዜ ቆይቷል።

በዚህ ጊዜ ውስጥ ግን የአካባቢው ሕዝብ ካለው ታሪክ እና ማንነት በተቃራኒ አላግባብ ወደ ትግራይ ተካሏል በሚል ሕዝባዊ ጥያቄን ያነሱ ሰዎች እስከ ፌዴሬሽን ምክር ቤት ድረስ የዘለቀ አቤቱታን ሲያቀርቡ ነበር።

የዚህ ጥያቄ ዋነኛ መሪ ከሆኑት መካከል አንዱ እና የአገሪቱ ሠራዊት የቀድሞ አባል፣ አሁን ደግሞ የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ እና የሰላም እና ፀጥታ መምሪያ ኃላፊ ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ “የወልቃይት ሕዝብ የማንነት ጥያቄውን ለማስመለስ ጥረት ያደረገው ገና ህወሓት የትጥቅ ትግል በማካሄድ እያለ ጀምሮ ነው” ይላሉ።

የአካባቢው ማኅበረሰብ ‘ከፋኝ’ በሚል አደረጃጀት የትጥቅ ትግል ሲያካሂድ እንደነበር የሚያስታውሱት ኮ/ል ደመቀ፣ ከመስከረም 2008 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ ከትግራይ ክልል እና ከፌደራል መንግሥቱ በሕገ መንግሥቱ መሠረት ምላሽ እንዲሰጣቸው ጥያቄያቸውን ሲያቀርቡ መቆየታቸውን ይገልጻሉ።

ያልተቋጨው የማንነት ጥያቄ

“እኛ የእናት ቋንቋችን አማርኛ ነው፣ ባሕላችን አማራ ነው፣ ሥነ ልቦናችን የጎንደር ማኅበረሰብ ነው። ስለዚህ ታሪካችን እና ማንነታችን ከጎንደር ጋር እንጂ ከትግራይ ጋር የተሳሰረ አይደለም” በማለት ጥያቄያቸው “ተቀማን” ያሉትን ማንነት የማስመለስ ሕገ መንግሥታዊ ጥያቄ ነው ይላሉ።

በህወሓት የበላይነት ይመራ የነበረው የፌደራሉ መንግሥት ጥያቄያቸውን ለማፈን በማኅበረሰቡ ተወካዮች ላይ እንግልት እና እስር እንደተፈጸመባቸው የሚናገሩት ኮ/ሌ ደመቀ፤ ሐምሌ 05/2008 ዓ.ም. እርሳቸው የሚገኙበትን የኮሚቴ አባላት አፍኖ ለመውሰድ የተደረገው ሙከራ ወደ ሕዝባዊ ተቃውሞ መሸጋገሩን ያስታውሳሉ።

በኢትዮጵያ መንግሥት ውስጥ ጉልህ ለውጥ መምጣቱን ተከትሎ በፌደራሉ መንግሥት እና በህወሓት መካከል ጥቅምት 2013 ዓ.ም. ትግራይ ውስጥ ጦርነት ሲቀሰቀስ አወዛጋቢው አካባቢ ከትግራይ ክልል አስተዳደር ቁጥጥር ሥር ወጣ።

ባለፉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ “ሁኔታዎች በየጊዜው እየተቀያየሩ አሁን የማንነት አስመላሽ ኮሚቴው በአብላጫ የተሳተፈበት አስተዳደር ተመስርቶ አካባቢያችንን እያስተዳደርነው እንገኛለን” ሲሉ ኮሎኔል ደመቀ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በተጨማሪም የወልቃይት ጉዳይ ሕጋዊ ምላሽ እና ዕውቅና እንዲያገኝ የፌዴሬሽን ምክር ቤትን እየጠበቁ ሲሆን፣ ለአካባቢው ተገቢው በጀት ተመድቦ ነዋሪው ተገቢውን ጥቅም እና አገልግሎት እንዲያገኝ የአማራ ክልልን እና የፌደራል መንግሥቱን መጠየቃቸውን ገልጸዋል።

“አካባቢውን እያስተዳደርነው እስከሆነ ድረስ፣ መንግሥት የሚያጣራውን ጉዳይ እስኪያጣራ እንጠብቃለን። የማንነቱ ጉዳይ ያን ያክል የሚያስቸኩለን አይደለም። ማንነቱ ቢመለስም በጀቱ ግን እስካሁን አልተሰጠንም። በጀት እና ማንነት ደግሞ ተለያይተው መኖር አይችሉም” ይላሉ።

ይሁን እንጂ የትግራይ ክልል አካባቢው በኃይል የተወሰደበት ሕጋዊ ግዛቱ መሆኑን እየገለጸ ይገኛል። የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ባለሥልጣናትም ተወስደውብናል የሚሏቸውን አካባቢዎች ማስመለስ ከቀዳሚ ዓላማዎቻቸው መካከል መሆናቸውን በተደጋጋሚ ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት በአማራ ክልል በኩል ወልቃይት ጠገዴ በሚባለው እና በትግራይ በኩል ደግሞ ምዕራብ ትግራይ በሚባለው አካባቢ፣ ደም አፋሳሹ ጦርነት ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ ከባድ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች መፈጸማቸው በስፋት ሲዘገብ ቆይቷል።በኮሎኔሉ ላይ የሚቀርቡ ክሶች

በቅርቡ የመብት ተከራካሪው ሂዩማን ራይትስ ዋች ባወጣው ሪፖርት ላይ ከአካባቢው በርካታ የትግራይ ተወላጆች በግዳጅ መፈናቀላቸውን፣ ብዙዎችም በእስር ላይ እንደሚገኙ እና ግድያዎችም እንደሚፈጸሙ አመልክቷል።

ኮ/ል ደመቀ ግን አስተዳደሩ ከአካባቢው ያፈናቀለው የትግራይ ተወላጅ የለም በማለት ያስተባብላሉ።

“ህወሓት ወልቃይትን ወደ ትግራይ አስተዳደር ያስገባው ነባሩን ማኅበረሰብ በማፈናቀል እና በመግደል የታጠቀ ኃይል አምጥቶ በማስፈር ነው። ይህ የታጠቀ ኃይል ደግሞ ለ27 ዓመታት ብዙ የአካባቢውን ነዋሪዎች ስላፈናቀለ እና ስለገደለ ጦርነቱ ሲጀመር ሸሽቶ ነው የሄደው” ይላሉ።

“ለዘመናት ስንበደል የኖርነው እኛ ሆነን ሳለ እነሱ ተመልሰው ተበዳይ ሆነው መቅረባቸው ያሳዝነናል” የሚሉት ኮሎኔሉ፣ ከእራሳቸው ፍላጎት ውጪ የትግራይ ተወላጅ በመሆናቸው ብቻ በደል የሚደርስባቸው እና የሚፈናቀሉ ሰዎች እንደሌሉ፣ አሁንም በርካታ የትግራይ ተወላጆች በአካባቢው በሰላም እየኖሩ እንደሆነ ማንኛውም አካል መጥቶ ማረጋገጥ ይችላል ብለዋል።

በአካባቢው ከሚፈጸሙ የመብት ጥሰቶች ጋር በተያያዘ በቅርቡ ሂዩማን ራይትስ ዋች ባወጣው ሪፖርት ላይ በአካባቢው ማንነትን መሠረት ያደረገ ወንጀል ሰርተዋል በማለት በስም ጠቅሶ ኮሎኔል ደመቀን ከሷል።

ለዚህ ክስ ምን ምላሽ እንዳላቸው በቢቢሲ የተጠየቁት ኮሎኔሉ “የወልቃይት ጠገዴ አማራ ሕዝብ ለዘመናት ከፍተኛ ግፍ ሲፈጸምበት አይተው እንዳላዩ ሲያልፉ ኖረው፣ አሁን የራሳቸው አጀንዳ ሲሆን ግን ግለሰብ እስከ መወንጀል መድረሳቸውን ስመለከት የህወሓት ቃል አቀባይ እንጂ የመብት ተሟጋች ሆነው አልመጡም” በማለት የመብት ተቆርቋሪ ድርጅቱን በወገንተኝነት ይከሳሉ።

ተቋሙ በአካባቢው ተፈጽመዋል ለተባሉት የመብት ጥሰቶች በግለሰብ ደረጃ እርሳቸውን መክሰሱን የተቹት ኮ/ሌ ደመቀ፣ ከዚህ አንጻር የሚቀርብባቸውን ክስ ፍርድ ቤት ቆመው እራሳቸውን ለመከላከል ፈቃደኛ ናቸው?

“እኔ ግለሰብ ነኝ፣ መንግሥትም አለኝ። ይህ መንግሥት ያየኛል፣ ካጠፋሁ በሕግ አግባብ እከሰሳለሁ። ነገር ግን የሚያስከስስም፣ የሚያስወነጅልም ሥራ ሰርቻለሁ አልልም” ይላሉ።

ሕዝበ ውሳኔ ወይስ ፖለቲካዊ ውሳኔ?

ደም አፋሳሹን ጦርነት ያስቆመው ስምምነት ደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ ላይ በፌደራሉ መንግሥት እና በህወሓት መካከል ከተፈረመ በኋላ፣ ሁኔታዎች ቀስ በቀስ ወደ ነበሩበት እየተመለሱ ቢሆንም የይገባኛል ውዝግብ ያለባቸው አካባቢዎችን በተመለከተ ግን እስካሁን በይፋ የተሰማ ነገር የለም።

በተለይ በሰሜን ምዕራብ ኢትዮጵያ ከሱዳን እና ከኤርትራ ጋር የምትዋሰንበት የወልቃይት/ምዕራብ ትግራይ አካባቢ በአማራ እና በትግራይ ክልሎች መካከል ያልተቋጨ የይገባኛል ጥያቄ ሆኖ እንዳለ ነው።

በትግራይ በኩል አካባቢው በአገሪቱ ሕገ መንግሥት የታወቀ የክልሉ ይዞታ መሆኑን በመጥቀስ ከጦርነቱ በፊት ወደ ነበረበት እንዲመለስ አጥብቀው እየጠየቁ ይገኛሉ።

አሁን ወልቃይት ጠገዴ በሚል ቦታውን እያስተዳደረ የሚገኘው ወገን ደግሞ፣ አካባቢው ከሦስት አስርት ዓመታት በፊት ከጎንደር ክፍለ አገር ያለአግባብ ተወስዶ ወደ ትግራይ የተካለለ በመሆኑ እና ሕዝቡም የማንነት ጥያቄ ስላለው አከላለሉ መልሶ እንዲታይ ይፈልጋል።

ታዲያ የዚህ ምናልባትም የሌላ ዙር ውዝግብ ከከፋም ግጭት ምክንያት ሊሆን የሚችለው አካባቢ ቀጣይ የወልቃይት ዕጣ ፈንታው ምን ሊሆን ይችላል? ሕዝበ ውሳኔ ወይስ ፖለቲካዊ ውሳኔ?

ሕዝበ ውሳኔ “ተገቢም፣ እውነትም ነው ብለን አናስብም” የሚሉት ኮሎኔል ደመቀ “ወልቃይት ጠገዴ በጉልበት ወደ ትግራይ የተጠቃለለ በመሆኑ፣ በሕግም በታሪክም ተጣርቶ ሕጋዊ ምላሽ ይሰጠናል ብለን ነው የምንጠብቀው” በማለት፣ “ዘላቂ መፍትሄ የሚገኘው የተፈጸሙ በደሎችን እና ታሪካዊ እውነታዎችን ታሳቢ ያደረገ” ፖለቲካዊ ውሳኔ ይጠብቃሉ።

አክለውም “እኛ ሕግን መሠረት አድርገን ነው የጠየቅነው፣ ከሕግ አንጻር ጉዳዩ ተዘርዝሮ መታየት አለበት። እንዲሁም እየጠየቅን ያለነው፣ የማንነት ጥያቄያችን ምላሽ እንዲያገኝ ብቻ ሳይሆን፣ እስካሁን ለደረሰብን በደልም ካሳ እንጠይቃለን” ይላሉ።

የተፈጸሙ ግፎች እና ተጠያቂነት

የትግራይ ክልል ባለሥልጣናት እና የተለያዩ የመብት ድርጅቶች እንደሚሉት ባለፉት ሁለት ዓመታት በአካባቢው በነበሩ የትግራይ ተወላጆች ላይ ከፍተኛ የመብት ጥሰት ተፈጽመዋል።

በተመሳሳይ የወልቃይት ማንነት አስመላሽ ኮሚቴ በአስርታት ውስጥ በነዋሪው ላይ የተለያዩ አይነት በደሎች መፈጸማቸውን በመጥቀስ፣ እነዚህ ሁኔታዎችን የሚያሽሩ እርምጃዎች መወሰድ አለባቸው ይላሉ።

ሁለቱም ወገን ለተፈጸሙ የመብት ጥሰቶች ተጠያቂነት እንዲኖር የሚጠይቁ ሲሆን፣ ኮሎኔል ደመቀም “እኛ ከማንነት ጥያቄው በተጨማሪ በሕዝባችን ላይ የዘር ፍጅት የፈጸሙ እና የሥነ ልቦና ጫና ያሳደሩ ሰዎች መጠየቅ አለባቸው” ይላሉ።

ለዚህ ጥያቄ ዘላቂ መፍትሔ የሚገኘው “አንድን ወገን ለማስደሰት ሲባል በአቋራጭ በሚሰጥ ውሳኔ ሳይሆን፣ የአገሪቱን ሕገ መንግሥት እና የፌደሬሽን ምክር ቤት ሕግን በተከተለ መልኩ” እንዲሆን ይፈልጋሉ።

በተጨማሪም “ፖለቲካዊ ውሳኔ ተሰጥቶ እንደ ኢትዮጵያዊ ግን የትግራይ እና የአማራ ሕዝብ እንዴት አብረው መኖር መቻል አለባቸው ለሚለው መፍትሄ ቢፈለግ ነው የተሻለ የሚሆነው” በማለት የሁለቱን ሕዝቦች ግንኙነትን የመጠገን አስፈላጊነትን ይጠቅሳሉ።

የጦርነቱን መቀስቀስ ተከትሎ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የትግራይ ተወላጆች ከአካባቢው ተፈናቅለዋል። ጦርነቱን ያስቆመው ስምምነትም በግጭቱ ምክንያት ከተለያዩ ስፍራዎች የተፈናቀሉ ሰዎችን ወደ ቀያቸው የመመለሱ ጉዳይ ትኩረት ከሰጣቸው መካከል አንዱ ነው።

ኮሎኔል ደመቀም “የተፈናቀለ ኢትዮጵያዊ መመለስ የለበትም ብለን አንሟገትም፤ ነገር ግን የትኛው ተፈናቃይ ነው? የሚለው ጉዳይ መታየት ይገባዋል” ይላሉ።

ነገር ግን ለተፈናቃዮች መመለስ ቀድመው መፈጸም አለባቸው ያሏቸውን “ለወልቃይት ሕዝብ ጥያቄ እውቅና መስጠት እና በደል የፈጸሙ ተጠያቂ መሆን" ወደ እርቅ ሊወስድ እንደሚችል በማመልከት፣ ከዚህ በፊት የሚወሰድ ውሳኔ ግን ሌላ ደም አፋሳሽ ግጭት ይፈጥራል የሚል ስጋት አላቸው።

ለውይይት ዕድል ይኖር ይሆን?

ፕሪቶሪያ ላይ ስምምነት ከተደረሰ በኋላ አካባቢውን በሚመለከት ከአማራ ክልልም ሆነ ከፌደራል መንግሥቱ የቀረበላቸው ጥያቄም ሆነ የመፍትሄ ሃሳብ እንደሌለ የሚገልጹት ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ፣ አካባቢው በአስተዳደሩ ሥር እንደሚቆይ ይናገራሉ።

ጉዳዩ በሕግ መቋጫ እንዲያገኝ እንደሚፈልጉ አጥብቀው የሚጠይቁት ኮሎኔል ደመቀ፣ በዋናነት አካባቢው በማን ሥር ነበር? እንዴትስ ነበር የተካለለው? የሚለው መመርመር እንዳለበት ያምናሉ።

የፌደራሉም ሆነ በሁለቱ የክልል መንግሥታት [አማራ እና ትግራይ] መካከል የወልቃይት ጉዳይ ሕጋዊ ምላሽ እስኪሰጠው ድረስ፣ በሕገ መንግሥቱ መሠረት በትግራይ አስተዳደር ሥር ይቆይ የሚል ውሳኔ ቢያሳልፉ ይቀበሉት እንደሆነ የተጠየቁት ኮሎኔሉ “የማይሆን አማራጭ ነው” በማለት ውድቅ ያደርጉታል።

“በፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት መሠረት የወልቃይት ጠገዴ አስተዳደር በአማራ ክልል ሥር እንደሚቆይ ነው የምንረዳው። የማንነት ጉዳዩ ነው እንጂ በሕገ መንግሥቱ የሚመለሰው፣ አስተዳደሩ ባለበት ነው የሚቀጥለው። እኛ በገባን ልክ ስምምነቱ ውዝግብ የሚነሳባቸው አካባቢዎች ባሉበት አስተዳደር መቆየት እንዳለባቸው ነው” ብለው ያምናሉ።

ከመነሻው ህወሓት አካባቢውን ከጎንደር ክፍለ አገር በኃይል በመውሰድ ከትግራይ ጋር ቀላቅሎታል የሚሉት ኮሎኔል ደመቀ፣ አሁን ደግሞ እነሱ በተራቸው የጦርነቱን መቀስቀስ ተከትሎ በቁጥጥራቸው ሥር አስገብተውታል። ታዲያ ይህ የኃይል አዙሪት ሊያበቃ የሚችልበት መንገድ ይኖር ይሆን? በሚል ከቢቢሲ ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ ሰጥተዋል።

“እውነት ነው ህወሓት በኃይል ይዞት ቆይቷል።ሕዝብ መብቱን ሲጠይቅ ደግሞ ሲያጠፋ እና ሲገድል ቆይቷል። እኛም በኃይል ይዘነዋል። ነገር ግን በኃይል እንደያዝነው እንቀጥል አላልንም። ጉዳዩ በሕግ ይዳኝ ብለን እየጠየቅን ነው ያለነው” ይላሉ።

ስለዚህም ያለው ችግር በእርቅም ይሁን በሌላ መንገድ ቢፈታ “የአካባቢው የአስተዳደር እና የማንነት ጉዳይ ግን በሕግ ማለቅ አለበት” በማለት በጦርነት የሚገኝ ነገር እንደማይኖር እምነታቸውን ገልጸዋል።

ለዚህም ከትግራይ ክልል አስተዳደር ጋር ለመነጋገር ፍላጎት እንዳላቸው በቢቢሲ የተጠየቁት ኮሎኔል ደመቀ፤ “ጉዳያችን ሊያልቅ የሚችለው በመነጋገር እና በመወያየት ነው። በጉልበት የሚያልቅ ነገር የለም። እኛ ብቻ አይደለንም መላው የወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ፣ መላው የአማራ ሕዝብ ሊነጋገር ይገባል” ብለዋል።

እንዲሁም የትግራይ እና የአማራ ሕዝብም ተገናኝቶ መነጋገር እንደሚገባው የሚጠቅሱት ኮሎኔሉ፣ “ጉዳያችን ከውይይት ውጪ በሆነ መልኩ ይፈታል ብለን አናስብም፣ ከየትኛውም አካል ጋርም ለመነጋገር ዝግጁ ነን” ሲሉ ለመነጋገር ያላቸውን ፍላጎት ለቢቢሲ ገልጸዋል።