በምሥራቅ ጎጃም ደብረ ኤልያስ ስለተከሰተው እስካሁን የምናውቀው

በአማራ ክልል ምሥራቅ ጎጃም ዞን፣ ደብረ ኤልያስ ወረዳ ሥላሴ ገዳም መሽገው ነበር የተባሉ 200 ታጣቂዎች መደምሰሳቸውን የኢትዮጵያ መንግሥት የፀጥታ እና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይል ቅዳሜ ምሽት ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

የዜና ትንታኔ

editors

6/4/2023

በአማራ ክልል ምሥራቅ ጎጃም ዞን፣ ደብረ ኤልያስ ወረዳ ሥላሴ ገዳም መሽገው ነበር የተባሉ 200 ታጣቂዎች መደምሰሳቸውን የኢትዮጵያ መንግሥት የፀጥታ እና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይል ቅዳሜ ምሽት ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

በመከላከያ ሠራዊት እና በአማራ ክልል የፀጥታ ኃይሎች ተወሰደ በተባለው እርምጃ፣ በቅርቡ የአማራ ሕዝባዊ ግንባር የተባለ እንቅስቃሴ መጀመሩን የገለጸው መግለጫው፤ በእስክንድር ነጋ የሚመራ ታጣቂ ቡድን በአካባቢው ይንቀሳቀስ እንደነበር ግብር ኃይሉ ገልጿል።

ቢቢሲ ከአካባቢው ባሰባሰበው መረጃ እንደተረዳው የመንግሥት ኃይሎች ይህንን ዘመቻ የጀመሩት ከግንቦት 18/2015 ዓ.ም. ሲሆን፣ ከአራት ቀናት በላይ ለሚሆን ጊዜ ከባድ ግጭት ሲካሄድ ቆይቶ በመቶዎች በሚቆጠሩ ሰዎች ላይ ጉዳት ደርሷል።

በገዳሙ አቅራቢያ ባሉ አካባቢዎች ያሉ ነዋሪዎች ለቀናት በቆየው ግጭት የከባድ መሳሪያ ጨምሮ ከባድ ተኩስ ሲካሄድ ሲሰሙ እንደነበር፣ ነገር ግን ምክንያቱ ምን እንደሆነ ሳያውቁ መቆየታቸውን ሐሙስ ዕለት ለቢቢሲ ተናግረው ነበር።

ከቀናት በፊት የደብረ ኤልያስ ወረዳ ሰላም እና ፀጥታ ጽሕፈት ቤት ባስተላለፈው መልዕክት፣ በደጎልማ ቀበሌ የሚገኘው የሥላሴ አንድነት ገዳም “በሃይማኖት ሽፋን ገዳሙን መሸሸጊያ አድርገው የሃይማኖት አባቶችን፣ የአገር ሽማግሌዎችን እና የመንግሥት አመራሮችን እየገደሉ በሕግ ላለመጠየቅ የሚጥሩ የታጠቁ ሰዎች የሚኖሩበት ገዳም ሆኗል” ብሎ ነበር።

የፀጥታ እና የደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይል ባወጣው መግለጫ ላይ በምሥራቅ ጎጃም ዞን ደብረ ኤልያስ ወረዳ በሚገኘው የሥላሴ ገዳም “መንግሥትን በትጥቅ ትግል ለመጣል ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ጽንፈኛ ኃይሎች” ባላቸው ላይ እርምጃ ተወስዷል ብሏል።

ከሳምንት በፊት ተጀምሮ ለቀናት የመከላከያ እና የአማራ ክልል የፀጥታ ኃይሎች ወሰዱት በተባለው እርምጃ “በእስክንድር ነጋ እና በግብረ አበሮቹ ለውጊያ ሲውል የነበረ ምሽግ መሰበሩን እና 200 ታጣቂዎች መደምሰሳቸውን” ግብረ ኃይሉ ገልጿል።

አስክንድር ነጋ ቀድሞ ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ የተባለው ፓርቲ መሥራች እና መሪ የነበረ ሲሆን፣ ባለፈው ዓመት ከፓርቲው አመራርነት እና አባልነት በመልቀቅ ከባልደራስ መለየቱን በይፋ ማስታወቁ ይታወሳል።

በቅርቡም “በአማራ ሕዝብ ላይ ይደርሳሉ ያሏቸውን በደሎች ለማስቆም እና አገሪቱ ገጥሟታል የሚሏቸውን ፈተናዎች ለመቋቋም” በሚል በአገር ውስጥ እና በውጭ የሚንቀሳቀስ የአማራ ሕዝባዊ ግንባር የተባለ እንቅስቃሴ መጀመሩን ይፋ አድርጓል።

የፀጥታ እና የደኅንነት ግብረ ኃይሉ እንዳለው እርምጃ ተወስዶበታል የተባለው የታጣቂ ቡድን መሪ እና አስተባባሪው አስክንድር ነጋ መሆኑንም አመልክቷል።

እርምጃ በተወሰደበት ወቅት “እስክንድር ነጋ እና ጥቂት ግብረ አበሮቹ ከአካባቢው መሰወራቸውን” ነገር ግን በመከላከያ ሠራዊት እና በአማራ ክልል የፀጥታ ኃይሎች ክትትል እየተደረገባቸው መሆኑን ጠቅሷል።

ጨምሮም “መንግሥትን በኃይል ለመጣል በማቀድ የአማራ ሕዝባዊ ግንባር የተባለ አደረጃጀት በመፍጠር ሽመልስ ስማቸው፣ ሰውመሆን ወረታው እና መንበሩ ካሴ ጋር በመሆን” በአካባቢው በህቡዕ በመንቀሳቀስ ታጣቂዎችን ሲመለምል፣ ሲያደራጅ እና ሲያሰማራ ነበር ብሏል።

ይኸው የአማራ ሕዝባዊ ግንባር የተባለው ቡድን ባለፈው ሰኞ ግንቦት 21/2015 ዓ.ም. ባሰራጨው መግለጫ፣ የመንግሥት ወታደሮች በደብረ ኤሊያስ ወረዳ ውስጥ በሚገኙ ታሪካዊ አብያተ ክርስቲያንት ላይ በከባድ መሳሪያ የታገዘ ጥቃት መክፈታቸውን በመግለጽ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ እንዲያወግዝ ጥሪ አቅርቦ ነበር።

በተጨማሪም ተፈጸመ ባለው መጠነ ሰፊ ወታደራዊ ጥቃት በሥላሴ ገዳም ውስጥ የሰላማዊ ሰዎች ሕይወት መጥፋቱን፣ በአብያተ ክርስቲያናቱ እና በውስጣቸው ባሉ ጥንታዊ ቅርሶች ላይ ጉዳት ሊደርስ እንደሚችል ገልጿል።

የደብረ ኤልያስ ወረዳ ሰላም እና ፀጥታ ጽሕፈት ቤት “በገዳሙ ውስጥ. . .ወታደራዊ ሥልጠና እየሰጡ ምሽግ በመሥራት፣ መሳሪያ በመግዛት እንዲሁም ከመንግሥት ያፈነገጡ ሰዎችን” በመሸሸጋቸው “መንግሥት ችግሩን ለመፍታት መከላከያን አስገብቶ በእምነት ተቋሙ ላይ ምንም አይነት ውድመት ሳያደርስ አስፈላጊው ሥራ ሰርቷል” ብሏል።

ለቀናት የቆየ ግጭት የተካሄደበት እና መንግሥት እንዳስታወቀው በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የተጎዱበት የምሥራቅ ጎጃም የደብረ ኤልያስ ብሔረ ብፁዓን መልክዓ ሥላሴ አንድነት ገዳም ባለቤት የሆነችው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ስለክስተቱ የሰጠችው ዝርዝር መረጃ የለም።

ነገር ግን የቤተ ክርስቲያኗ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት የገዳማት አስተዳደር መምሪያ ከአገረ ስብከቱ ጽሕፈት ቤት ጋር በመገናኘት የተከሰተውን ችግር በተመለከተ የማጣራት ሥራ እያከናወነ እንደሆነ እና ተጣርቶ የተደረሰበት ውጤት የሚገለጽ መሆኑን አሳውቋል።

ቢቢሲ በምሥራቅ ጎጃም ዞን ደብረ ኤሊያስ ወረዳ የተከሰተውን ሁኔታ ለማጣራት ካለፈው ሰኞ ጀምሮ ከሚመለከታቸው የአካባቢው እና የአማራ ክልል ኃላፊዎች ዝርዝር መረጃ ለማግኘት ጥረት ቢያደርግም ሳይሳካለት ቆይቷል።

ነገር ግን ማንነታቸው እንዲጠቀስ ያልፈቀዱ የአካባቢው ሁለት ነዋሪዎች በግጭቱ “እጅግ ብዙ” ያሏቸው ሰዎች ላይ የሞት እና የመቁሰል ጉዳት መድረሱን እንደሚያውቁ ገልጸው ነበር።

ለቀናት በተካሄደው ወታደራዊ ግጭት የደረሰው ጉዳት የመንግሥት የፀጥታ ኃይል አባላትን የሚያካትት መሆኑን እና ቁጥሩን ለመገመት እንደማይችሉም ተናግረዋል።

የፀጥታ እና ደኅንነት ግብረ ኃይሉ በታጣቂዎቹ ላይ የመከላከያ ሠራዊት እና የአማራ ክልል ፀጥታ ኃይሎች ወሰዱት ባለው እርምጃ፣ ተደመሰሱ ከተባሉት 200 የቡድኑ አባላት በተጨማሪ የተማረኩ እና ከአካባቢው የሸሹ አሉ ብሏል።

እንዲሁም የተለያዩ ከባድ እና ቀላል መሣሪያዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ጠቅሶ፣ በመንግሥት መገናኛ ብዙኃን ላይ የተያዙ የተባሉ ሰዎች እና የጦር መሳሪያዎች ምስል ታይተዋል።

የአማራ ሕዝባዊ ግንባር መንግሥት ወስድኩ ስላለው እርምጃ እና ተደመሰሱ ስለተባሉት ታጣቂዎች ወዲያው ያለው ነገር የለም።