መንግስት “ያለምንም የህግ አግባብ” ያሰራቸውን ጋዜጠኞች “በአስቸኳይ እንዲፈታ” የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ማህበር ጠየቀ

የዜና ትንታኔ

4/14/20232 min read

መንግስት “ያለምንም የህግ አግባብ” ያሰራቸውን የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎችን “በአስቸኳይ እንዲፈታ” የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ማህበር ዛሬ አርብ ሚያዝያ 6፤ 2015 ባወጣው መግለጫ ጠየቀ። መንግስት በመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ላይ የሚያደርሰውን ማሸማቀቅ እንዲያቆምም ማህበሩ ተመሳሳይ ጥያቄ አቅርቧል።

ማህበሩ በዛሬው መግለጫው፤ በኢትዮጵያ ከጊዜ ወደ ጊዜ የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች የሚሰሩበት “አውድ እየጠበበ” መምጣቱን ገልጿል። ጋዜጠኞች ስራቸውን በነጻነት እንዳይሰሩ፤ “በመንግስት የጸጥታ አካላት እየተሸማቀቁ እንግልት እየደረሰባቸው” መሆኑን መታዘቡንም አመልክቷል። ለዚህም በማሳያነት የማህበሩ መስራችና የስራ አስፈጻሚ አባል የሆነውን ጋዜጠኛ ዳዊት በጋሻውን ጨምሮ ስድስት ጋዜጠኞች በአሁኑ ወቅት በመንግስት ኃይሎች ቁጥጥር ስር መዋላቸውን ጠቅሷል። የማህበሩ የህዝብ ግንኙነት ክፍል ኃላፊ እና የ“አራት ኪሎ ሚዲያ” መስራች ከሆነው ዳዊት በተጨማሪ መግለጫው በስም የዘረዘራቸው ጋዜጠኞች፤ አራጋው ሲሳይ፣ ገነት አስማማው፣ ጌትነት አሻግሬ፣ በየነ ወልዴ እና ቴዎድሮስ አስፋውን ነው።

የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች “በስራቸው ላይ ስህተት በሚሰሩበት ወቅት በህግ አግባብ መጠየቅ እና የህግ የበላይነት መከበር እንዳለበት” በጽኑ እንደሚያምን የገለጸው ማህበሩ፤ ሆኖም ከእስር ጋር በተያያዘ በአዋጅ የተቀመጠላቸውን ድንጋጌ “ተግባራዊ አለመደረጉ ያሳስበኛል” ብሏል። ማህበሩ በመግለጫው የጠቀሰው ድንጋጌ፤ በመጋቢት 2013 ዓ.ም. በጸደቀው የመገናኛ ብዙኃን አዋጅ አዋጅ የሰፈረ ነው።

ይኸው አዋጅ “በመገናኛ ብዙኃን አማካኝነት የወንጀል ድርጊት በመፈጸም የተጠረጠረ ማንኛውም ሰው ወይም አካል፤ በወንጀል ስነ ስርዓት ሕግ ድንጋጌዎች መሰረት ለተጨማሪ ምርመራ በእስር እንዲቆይ ሳይደረግ ክሱ በቀጥታ በዐቃቤ ህግ አማካኝነት ለፍርድ ቤት መቅረብ አለበት” ሲል ይደነግጋል። ማህበሩ በዛሬው መግለጫው፤ ከታሰሩት ጋዜጠኞች አንዳንዶቹ “ያሉበት ሁኔታ እና ምን ሁኔታ ላይ እንዳሉ” እንኳን ቤተሰቦቻቸው ጭምር “በቂ መረጃ” እንደሌላቸው ጠቁሟል። “ጋዜጠኞች ያለፍርድ ቤት ማዘዣ እየታሰሩ፣ እየታፈኑና ቤታቸው እና ቢሯቸው እየተበረበረ መሆኑ፤ ባለሙያዎች ስራቸውን በነጻነት እንዳይሰሩ፤ የፕሬስ ምህዳሩ የበለጠ እንዲጠብ እያደረገ ነው” ያለው የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ማህበሩ፤ እንዲህ አይነት እርምጃዎችን “በጽኑ እንደሚያወግዝ” አስታውቋል። መንግስት “የፕሬስ ነጻነት እንዲረጋገጥ ያጸደቃቸውን ሕገ-መንግስታዊና ዓለም አቀፋዊ ህጎች እንዲያከብር” እንዲሁም “ውስጡን እንዲፈተሽ” ማህበሩ ጠይቋል።

በአሁኑ ወቅት የተያዙት የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች የታሰሩት “ያለ ምንም የህግ አግባብ” መሆኑን የገለጸው ማህበሩ፤ መንግስት ጋዜጠኞቹን “በአስቸኳይ እንዲፈታ” ጥያቄ አቅርቧል። መንግስት በመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ላይ የሚያደርሰውን “ማሸማቀቅ እና እንግልት” እንዲያቆምም ማህበሩ በተጨማሪነት ጠይቋል። ማህበሩ ባለፈው ዓመት የካቲት ወር ላይ ባወጣው መግለጫ ለመንግስት ተመሳሳይ ጥያቄ አቅርቦ እንደነበር ይታወሳል።

Related Stories