እናት ፓርቲ፤ ዶ/ር ሰይፈ ሥላሴ አያሌውን ፕሬዝዳንት አድርጎ መረጠ
የዜና ትንታኔ
ለስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ ከፍተኛ ዕጩዎችን በማቅረብ በሶስተኛ ደረጃ ተቀምጦ የነበረው እናት ፓርቲ፤ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤውን ሊያካሄድ የነበረው ከአንድ ወር ገደማ በፊት የካቲት መጨረሻ ላይ ነበር። በአዲስ አበባ አራት ኪሎ አካባቢ በሚገኘው የቅድስት ስላሴ ዩኒቨርሲቲ አዳራሽ ሊካሄድ የነበረው የፓርቲው ጠቅላላ ጉባኤ፤ “ከበላይ አካል መጣ” በተባለ ትዕዛዝ ምክንያት መከልከሉ ይታወሳል።
ይህን ተከትሎ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በሰጠው መግለጫ፤ የእናት ፓርቲ ጠቅላላ ጉባኤ የተደናቀፈው ለጊዜው ስሙን ለይቶ ባላረጋገጠው “የህግ አስፈጻሚ ኃላፊ ትዕዛዝ” መሆኑን አስታውቆ ነበር። ምርጫ ቦርድ በዚሁ መግለጫው፤ የእናት ፓርቲን ጨምሮ የሌሎች የፖለቲካ ፓርቲዎች ጉባኤን ያሰናከሉ የህግ አስፈጻሚ አካላት ላይ ፍትሕ ሚኒስቴር ክስ እንደሚሰርት ይፋዊ ጥያቄ ማቅረቡም አይዘነጋም።
ትላንት በተካሄደው ጠቅላላ ጉባኤ፤ እናት ፓርቲን በፕሬዝዳንትነት እንዲመሩ የተመረጡት ዶ/ር ሰይፈ ሥላሴ የፖለቲካ ተሳትፏቸውን የጀመሩት በዚሁ ፓርቲ ውስጥ ነው። ከመጀመሪያ እስከ ዶክትሬት ዲግሪያቸውን በኢኮኖሚክስ ትምህርት ዘርፍ በሩስያ የተከታተሉት ዶ/ር ሰይፈ ስላሴ፤ አብዛኛውን የስራ ጊዜያቸውን ያሳለፉት በመንግስት መስሪያ ቤቶች ውስጥ ነው።
በኢትዮጵያ ካርታ ስራዎች ባለስልጣን በከፍተኛ ባለሙያነት ስራ የጀመሩት አዲሱ የእናት ፓርቲ ፕሬዝዳንት፤ በመቀጠልም ወደ ኢኮኖሚ ልማት እና ትብብር ሚኒስቴር በመዘዋወር በማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ መምሪያ ውስጥ የቡድን አስተባባሪ ሆነው አገልግለዋል። ዶ/ር ሰይፈ ሥላሴ በጉምሩክ ባለስልጣን የፕላን፣ ሪሰርች እና ስታትስቲክስ መምሪያ ኃላፊ ሆነው ከሰሩ በኋላ፤ ወደ ግል ድርጅቶች ፊታቸውን አዙረዋል።
በግል ድርጅቶች በተለያዩ የኃላፊነት ቦታዎች ተቀጥረው የሰሩት ዶ/ር ሰይፈ ሥላሴ፤ ከሳተላይት ናቪጌሽን እና የካርታ ስራዎች ጋር የተያያዙ ስራዎችን የሚሰራ የራሳቸውን የግል ድርጅት አቋቁመው በስራ አስኪያጅነት ሲመሩ ቆይተዋል። ዶ/ር ሰይፈ ስላሴ ወደ ፖለቲካ እንዲገቡ ምክንያት የሆናቸውን ጉዳይ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ሲያስረዱ፤ “ሀገር ወደ ችግር በምትገባበት ጊዜ የዚያ ችግር መፍትሔ ፖለቲካ እና ፖለቲከኞች ጋር እንደሆነ በመረዳት ነው” ብለዋል።
በትላንትናው የእናት ፓርቲ አንደኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ ፓርቲውን በምክትል ፕሬዝዳንትነት እንዲመሩ የተመረጡት ወይዘሮ ጥሩማር አባተ፤ ላለፈው አንድ ዓመት ከመንፈቅ የፕላን እና ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ሆነው በመስራት ላይ የሚገኙ ናቸው። የእናት ፓርቲ የጎንደር ጽህፈት ቤት ሰብሳቢ የነበሩት ጥሩማር፤ በቢዝነስ አስተዳደር የመጀመሪያ፣ በሊደርሺፕ ደግሞ የማስተርስ ዲግሪ አላቸው።
በቅዳሜው ጠቅላላ ጉባኤ ከሁለቱ ከፍተኛ አመራሮች በተጨማሪ፤ 13 የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት እና 32 የላዕላይ ምክር ቤት እና መመረጣቸውን ከፓርቲው የተገኘው መረጃ ያመለክታል። በዚሁ ጉባኤ ላይ የተሻሻለው የፓርቲው መተዳደሪያ ደንብን ጨምሮ ሶስት ሰነዶች መጽደቃቸው ተነግሯል። ዶ/ር ሰይፈ ሥላሴ በመተዳደሪያ ደንቡ ላይ ስለተደረገው ለውጥ ሲያስረዱ፤ “ባለፉት ሶስት ዓመታት ባደረግናቸው እንቅስቃሴዎች ያየናቸውን ክፍተቶች እና ቢሻሻሉ የተሻለ ውጤት ያመጣሉ ብለን የምንላቸውን መጠነኛ አንቀጾች ላይ ማሻሻያ አድርገናል” ብለዋል።
በየካቲት 2012 በተካሄደው የእናት ፓርቲ መስራች ጉባኤ ላይ የጸደቀው መተዳደሪያ ደንብ፤ የፓርቲው ፕሬዝዳንት የላዕላይ ምክር ቤቱ እና የብሔራዊ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ እንደሚሆን አስቀምጦ ነበር። ትላንት በተሻሻለው የፓርቲው መተዳዳሪያ ደንብ ግን የላዕላይ ምክር ቤቱ የራሱ አፈ ጉባኤ እና ምክትል አፈ ጉባኤ እንዲኖሩት መደረጉን ዶ/ር ሰይፈ ሥላሴ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። የተሻሻለው መተዳደሪያ ደንብ፤ የፓርቲውን የብሔራዊ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ቁጥር ከ11 ወደ 13 ከፍ እንዲል ማድረጉንም አስታውቀዋል።