የቤቶች ፈረሳው መኖሪያ አልባ ዜጎችን እንዳያበራክት ኢሰመኮ አሳሰበ

የዜና ትንታኔ

3/31/20232 min read

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ/ኮሚሽኑ) በአዲስ አበባ ከተማ ዙሪያ የኦሮሚያ ክልል ውስጥ በቅርቡ በአዲስ መልክ በተደራጀው የሸገር ከተማ አስተዳደር የቤቶች ፈረሳ እና በግዳጅ ማስነሳት (Demolition and Forced Eviction) እየተከናወነባቸው ካሉ አካባቢዎች መካከል ቡራዩ፣ ሰበታ፣ ለገጣፎ ለገዳዲ፣ መነ አብቹ እና በዙሪያው ከሚገኙ አካባቢዎች ቤቶቻቸው የፈረሱባቸው ሰዎች በግል እና በቡድን ለኮሚሽኑ ያቀረቡትን አቤቱታ ተከትሎ ከየካቲት 27 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ ክትትልና ምርመራ ሲያደርግ ቆይቷል። በዚህም መሠረት ለኮሚሽኑ ቅሬታ ያቀረቡ ሰዎችን፣ የሚመለከታቸውን የከተማ አስተዳደር እና የጸጥታ አካላት በማነጋገር፤ በከተማዋ የተለያዩ አካባቢዎች በመዘዋወር ቤቶችን የማፍረስ እና በግዳጅ የማስነሳት ሂደቱ የሚከናወንበትን ሁኔታ እንዲሁም ቀደም ሲል የፈረሱ ቤቶችን የመስክ ምልከታ በማድረግ መረጃ እና ማስረጃ አሰባስቧል።

ለኢሰመኮ ቅሬታቸውን ያቀረቡት ሰዎች ለኮሚሽኑ ሲያስረዱ በየአካባቢው ከቀድሞ/ነባር ባለ ይዞታዎች ቦታ ወይም ቤት በመግዛት ኑሮ መሥርተው ሲኖሩ የነበሩ መሆናቸውን፣ በየአካባቢው ከሚገኙ ማኅበራዊ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት የውሃ እና የመብራት አገልግሎት ተጠቃሚ የነበሩ መሆናቸውን፣ ለተለያዩ የአካባቢው የልማት ሥራዎች እንደ ማንኛውም ማኅበረሰብ ክፍያዎችን ሲከፍሉ መቆየታቸውን በመጥቀስ መኖሪያ ቤቶቻቸው ያለ በቂ ቅድመ ማስጠንቀቂያ ከሕግ አግባብ ውጭ እንደፈረሱባቸው ይገልጻሉ።

ኢሰመኮ ያነጋገራቸው የሸገር ከተማ ኃላፊዎች በበኩላቸው የከተማ አስተዳደሩ እንደ አዲስ መመሥረቱን ተከትሎ “ሕጋዊ የይዞታ ማረጋገጫ የሌላቸውን” ግንባታዎች በማፍረስ ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡ እንዲሁም የአየር ካርታን ጨምሮ ሕጋዊ የይዞታ ማረጋገጫ የሌላቸው፣ ከነባር የአርሶ አደር ይዞታ ውጪ የሆኑ እና በተለይም ከ2005 ዓ.ም. በኋላ የተገነቡ ቤቶች እንዲፈርሱ በተወሰነው መሠረት የተከናወነ መሆኑን፣ ቤቶቹን የማፍረስ ሂደቱን በተመለከተም ከቤቶቹ ባለቤቶች ጋር በክፍለ ከተማ፣ በወረዳ እና በቀበሌ ደረጃ ውይይት ተደርጎ በቂ ግንዛቤ እንዲፈጠር በማድረግ እና በሚፈርሱ ቤቶች ላይ በቅድሚያ ምልክት ከተደረገ በኋላ እራሳቸው ግንባታውን እንዲያፈርሱ ጊዜ የሚሰጣቸው መሆኑን፣ በተሰጣቸው ጊዜ ውስጥ ግንባታውን ሳያነሱ የቀሩ ሰዎች ካሉ ግንባታዎችን በአፍራሽ ግብረ ኃይል እንደሚያፈርሱ፣ የፈረሰውን የግንባታ ቁሳቁስም በሕግ የተቀመጠውን አሠራር በመከተል ወደ ከተማ አስተዳደሩ ተወስዶ ውሳኔ የሚሰጥበት መሆኑን የከተማ አስተዳደሩ ኃላፊዎች ለኮሚሽኑ ጨምረው አስረድተዋል።

ኢሰመኮ በጉዳዩ ዙሪያ በለገጣፎ ለገዳዲ፣ በሰበታ አካባቢ ፉሪ እና ለቡ ተክለሃይማኖት እንዲሁም በቡራዩ ገፈርሳ ኖኖ አካባቢዎች በመዘዋወር ቀደም ሲል የፈረሱ እና የማፍረስ ተግባሩ እየተከናወነ የነበረባቸውን አካባቢዎች ተመልክቷል፡፡ ኮሚሽኑ በለገጣፎ ለገዳዲ ክፍለ ከተማ በመገኘት እየፈረሱ የነበሩ ቤቶችንም ለመመልከት ችሏል። በምልከታው የቤት ማፍረሱ እና በግዳጅ ማስነሳቱ በግብረ ኃይል እየተከናወነ እንደነበረ እና በቦታው ከፖሊስ፣ ልዩ ኃይል እና ሚሊሻ አባላት በተጨማሪ ሌሎች ዱላ የያዙ ሲቪል ሰዎች እንደነበሩም ተመልክቷል።

የክትትልና የምርመራ ሥራው ሙሉ በሙሉ ባይጠናቀቅም እስካሁን በተገኙት መረጃዎች እና ማስረጃዎች መሠረት የቤት ማፍረስ እና በግዳጅ የማንሳት እርምጃው ከሰብአዊ መብቶች አኳያ የታዩበትን ክፍተቶች እና ሊወሰዱ የሚገባቸውን የማስተካከያ እርምጃዎች በተመለከተ ኢሰመኮ የሚከተለውን ይገልጻል።

በዓለም አቀፍ ሕግ እና የሰብአዊ መብቶች መርሆች መሠረት በግዳጅ ማንሳት (Forced Eviction) ማለት አንድን ሰው ወይም ቤተሰብ ወይም ማኅበረሰብ ከሚኖርበት ቤት ወይም ቦታ ላይ ያለ ፈቃዱ፣ አማራጭ መፍትሔ ሳይሰጠው ወይም ሕጋዊ ጥበቃ ሳይደረግለት በጊዜያዊነት ወይም በዘላቂነት በኃይል አስገድዶ ማንሳትን የሚመለከት ነው።

እርምጃው ተገቢ ልየታ ያልተደረገበት ስለመሆኑ

የቤት ፈረሳውና በግዳጅ ማንሳቱ የሚመለከተው የከተማውን መሪ ዕቅድ በሚጥሱ እና የመንግሥት ይዞታን በመውረርና ከአርሶ አደሩ ጋር በተደረገ ሕገ ወጥ የመሬት ግብይት የተገኙ ይዞታዎች ላይ የተደረጉ ግንባታዎችን ነው ቢባልም ሁሉም ቤቶች ግን በተመሳሳይ ሥሪት ላይ የተመሠረቱ ባለመሆናቸው የሚገዛቸውም ሕጎች እና አሠራሮች በዚያው ልክ የተለያዩ ሊሆኑ ይገባ ነበር። ኢሰመኮ ባደረገው ክትትልና ምርመራ እየፈረሱ ያሉ ቤቶች በተለያየ አይነት ክፍል የሚመደቡ መሆኑን ተገንዝቧል።

የመጀመሪያው ክፍል ከ2005 ዓ.ም. በፊት የተገነቡ ቤቶች ሲሆኑ እነዚህን ቤቶች በተመለከተ በሀገሪቱ የከተማ ቦታን በሊዝ ስለመያዝ በወጣው አዋጅ ቁጥር 721/2004 አንቀጽ 6(4) እና (5) እንደተደነገገው አዋጁ ከመውጣቱ በፊት በኢመደበኛ መልኩ የተገነቡ ቤቶች የከተሞችን ፕላን እና የሽንሻኖ ስታንዳርድ ሲያሟሉ ወደ መደበኛ ሥሪት እንደሚዞሩ ደንግጓል። ነገር ግን ኮሚሽኑ ባደረገው ማጣራት እነዚህን ቤቶች ሕጉ በደነገገው መሠረት በወቅቱ ወደ መደበኛ ሥሪት እንዲዘዋወሩ የሚያስችላቸውን መስፈርቶች ማሟላታቸውን በማረጋገጥ የማዘዋወር ሥራ ሳይሠራ እንዲሁ እንዲፈርሱ መደረጋቸውን ለመረዳት ችሏል።

ሁለተኛው ክፍል በግዢ የተገኙ ቤቶች ሲሆኑ፤ ከእነዚህ ቤቶች ውስጥ መደበኛ ካርታ፣ የአየር ላይ ካርታ እና አረንጓዴ ደብተር ያላቸው እንዲሁም እንዳይፈርሱ የፍርድ ቤት እግድ ያለባቸው ቤቶች ከከተማ ፕላን ጋር የማይሄዱ ናቸው ከተባለ፤ በሕግ አግባብ በተደነገገው መሠረት ተለዋጭ የቤት መሥሪያ ቦታ እና ተገቢው ካሳ ተከፍሏቸው መነሳት የሚገባቸው ነበሩ። ቤቶቹ በገጠር መሬት ላይ የተሠሩ ናቸው የሚባል ቢሆን እንኳ በኦሮሚያ የገጠር መሬት አስተዳደር እና አጠቃቀም አዋጅ ቁጥር 130/1999 አንቀጽ 6(8) መሠረት በቂ ጊዜ ተሰጥቶ ንብረቶቻቸውን እንዲያነሱ ይደረጋል እንጂ በድንገት ማፍረስ አይገባም ነበር።

ሦስተኛው እና አራተኛው ክፍል ከአርሶ አደሮች ጋር በተደረገ ሕገ ወጥ የመሬት ሽያጭ በተገኘ ቦታ ላይ የተሠሩ ቤቶች እና ከ2005 ዓ.ም. በኋላ ያለሕጋዊ ፈቃድ በመንግሥት ይዞታዎች ላይ የተገነቡ ቤቶች ናቸው።

ስለሆነም እንዲፈርሱ የተደረጉት ቤቶች በተለያየ አይነት ሥሪት ላይ የተመሠረቱ ስለሆነ እንደየነገሩ ሁኔታ ተገቢው መለየት እና ማጣራት እየተደረገ ሊፈጸም ይገባው ነበር፡፡ ሕገ ወጥ ግንባታ ማፍረስና የመንግሥት ይዞታ የሆነን ቦታ መልሶ መውሰድ ሕጋዊ እርምጃ ቢሆንም እንኳን፤ የመኖሪያ ቤት ማፍረስና በግዳጅ ማስነሳት ዜጎችን መኖሪያ ቤት አልባ በሚያደርግ መልኩ መደረግ እንደሌለበት እና በሕግ የተፈቀደ እና ለቅቡል አላማ የተደረገ መሆኑ ብቻ በቂ ምክንያት ሊሆን እንደማይችል ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ሕግ ይደነግጋል። ዜጎች የመኖሪያ ቤት መብት እንዳላቸው ኢትዮጵያ ያጸደቀችው ዓለም አቀፍ የኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ እና ባህላዊ መብቶች ቃልኪዳን በአንቀጽ 11 የደነገገ ሲሆን ኢመደበኛ በሆነ መንገድ እንኳን የተገኙ የመኖሪያ ቤቶችን በሚመለከት መኖሪያ ቤት አልባነትን ለመከላከል ሲባል ሕጋዊ የይዞታ ዋስትና ሊሰጣቸው ወይም አማራጭ መፍትሔ ሊመቻች እንደሚገባ የኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ እና ባህላዊ መብቶች ኮሚቴ በግዳጅ ማንሳትን በተመለከተ ባወጣው አጠቃላይ አስተያየት ቁጥር 7 ላይ አስቀምጧል።

እርምጃው ያለ በቂ የቅድመ ማስጠንቀቂያ (ቀድሞ የማሳወቅ ግዴታ) የተከናወነ ስለመሆኑ

እንዲፈርስ የተፈለገው ቤት ያለበት የመሬት ይዞታ ዓይነት በሕግ ሊሰጥ የሚገባውን የቅድመ ማስጠንቀቂያ ጊዜ መጠን የተለያየ የሚያደርገው ቢሆንም፤ ነገር ግን በማናቸውም ዓይነት ይዞታና ሁሉም ዓይነት ቤቶች (በመደበኛም ሆነ በኢመደበኛ መንገድ በተያዙ መሬቶች ላይ የተሠሩ ቤቶች) የቅድመ ማስጠንቀቂያ ሳይሰጥ የመኖሪያ ቤት እንዲፈርስ ሊደረግ አይችልም። ይህም ለሕዝብ ጥቅም ሲባል የመሬት ይዞታ የሚለቀቅበት፣ ካሣ የሚከፈልበት እና ተነሺዎች መልሰው የሚቋቋሙበትን ሁኔታ ለመወሰን በወጣው አዋጅ ቁጥር 1161/2011 አንቀጽ 8(8) እና የከተማ ቦታን በሊዝ ስለመያዝ በወጣው አዋጅ ቁጥር 721/2004 አንቀጽ 26(4) ላይ በግልጽ ተደንግጓል።

የከተማው አስተዳደር ቤቶቹን ከማፍረሱ በፊት በቂ የቅድሚያ ማስጠንቀቂያ መሰጠቱን እና ከነዋሪዎች ጋር ውይይት መደረጉን በዚህም ንብረቶቻቸውን በታዘዙት መሠረት ቀድመው ያነሱ ሰዎች ያሉ መሆኑን የገለጹ ቢሆንም በአንዳንድ አካባቢዎች ይህ መሠረታዊ ቅድመ ሁኔታ ተግባራዊ አለመደረጉን ማወቅ ተችሏል፡፡ ኢሰመኮ ያነጋገራቸው ቤቶቻቸው የፈረሱባቸው በርካታ ሰዎች ቤታቸው እንደሚፈርስ አስቀድሞ ያልተነገራቸው መሆኑን እና አፍራሽ ግብረ ኃይሉ በድንገት መጥቶ እንዳፈረሰባቸው ተናግረዋል። ለምሳሌ በተለምዶ ለቡ ተክለ ሃይማኖት ተብሎ በሚጠራ ስፍራ ወደ ሥራ ገበታቸው ከሄዱ በኋላ ሀብት ንብረታቸውን ሳይሰበስቡ ቤቶቻቸው የፈረሱባቸው ቤተሰቦችን ኮሚሽኑ አነጋግሯል፡፡ በተመሳሳይ በለገጣፎ ለገዳዲ ክፍለ ከተማ ቄስ ሰፈር እየተባለ በሚጠራው አካባቢ ቤታቸው የፈረሰባቸው ሰዎች ቤታቸው ውስጥ እንዳሉ አፍራሽ ግብረ ኃይሉ ድንገት መጥቶ ቆርቆሮ መንቀል እንደጀመረ ተናግረዋል።

አድሎአዊ እርምጃ ስለመኖሩ

መንግሥት የሚወስዳቸው ማናችውም እርምጃዎች ከአድሎ የጸዱ መሆን እንደሚገባቸው በዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ሰነዶች እና በሀገር አቀፍ ሕጎች እውቅና ከተሰጠው የሰብአዊ መብቶች መርሆች መካከል አንዱ ነው። ኢሰመኮ ክትትል እና ምርመራ ባደረገባቸው አንዳንድ ቦታዎች ላይ አድሏዊ እርምጃዎች እየተወሰዱ እንዳሉ ለመመልከት ተችሏል። ለምሳሌ በለገጣፎ ለገዳዲ ክፍለ ከተማ ቄስ ሰፈር እየተባለ በሚጠራው አካባቢ ተያይዘው ከተሰሩ ቤቶች ውስጥ ሁለት ቤቶችን በማስቀረት ሌሎች ቤቶች እንዲፈርሱ ተደርገዋል። ቤቶቻቸው የፈረሱባቸው ሰዎች አድሎው ብሔር ተኮር እንደሆነ እምነት እንዳላቸው የገለጹ ሲሆን የመንግሥት ኃላፊዎች ግን ይህ እንዳልሆነ አስረድተዋል።

እስር፣ የአካልና ሥነ-ልቦና ጉዳት እና እንግልት ስለመድረሱ

በአንዳንድ ቦታዎች የማፍረስ እና በግዳጅ የማስነሳቱ ሂደት ለሁከት፣ እንግልት፣ ለአካልና ሥነ ልቦና ጉዳት እና ለእስር ምክንያት ሆኗል፡፡ ሰዎች በከፍተኛ ድካም እና ጥረት ያፈሩት ንብረት ሲወድምባቸው ስሜታዊ መሆናቸው የሚጠበቅ መሆኑን ከግንዛቤ በማስገባት የመንግሥት ጸጥታ ኃይሎች ምላሽ የተቆጠበ እና በትዕግስት ላይ የተመሠረተ ሊሆን ይገባል። ይሁንና በአንዳድ አካባቢዎች ቤታቸው እንዳይፈርስባቸው የተቃወሙ፣ መንገድ የዘጉ፣ ጩኸት ያሰሙ ሰዎች በጸጥታ አስከባሪዎች ተመጣጣኝ ያልሆነ የኃይል እርምጃ መደብደባቸውን፣ የተወሰነ መጠን የአካል ጉዳት መድረሱን፣ በቤተሰብና ሕፃናት ልጆች ላይ የሥነ ልቦና ጉዳት መድረሱን እንዲሁም የተወሰኑ ሰዎች ደግሞ ለተለያየ የጊዜ መጠን እስር መዳረጋቸውን ኢሰመኮ ተረድቷል።

የከተማ አስተዳደሩ በበኩሉ በተለይም በተለምዶ ለቡ ተክለሃይማኖት እና መነ አብቹ ተብለው በሚጠሩ አካባቢዎች ሥራውን ለማደናቀፍ በቡድን ተደራጅተው በመንቀሳቀስ በጸጥታ ኃይሎች ላይ ጉዳት ለማድረስ ሙከራ ያደረጉ ሰዎች መኖራቸውን ገልጾ ይህንን ለመቆጣጠር ፖሊስ በወሰደው እርምጃ መጠነኛ የአካል ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች ሊኖሩ የሚችሉ መሆኑን በመግልጽ የሞተ ሰው ግን አለመኖሩን አስረድቷል፡፡ ነገር ግን ፊሊዶሮ በተባለ ቦታ ላይ በተደረገው የቤት ፈረሳ የሰው ሕይወት ማለፉን ኢሰመኮ መረጃ የደረሰው ሲሆን ይህን በተመለከተ ክትትል እያደረገ ይገኛል። የከተማ አስተዳደሩ በጊዜያዊነት በቁጥጥር ስር የዋሉ ሰዎች የነበሩ መሆኑን ገልጸው ሁሉም በአጭር ጊዜ ውስጥ የማጣራት ሥራ ተከናውኖ ከእስር መለቀቃቸውን ያስረዱ ቢሆንም ይህ መግለጫ እስከ ተሰጠበት ጊዜ ድረስ የታሰሩ ሰዎች እንዳሉ ለማወቅ ተችሏል።

ኢሰመኮ ከአቤቱታ አቅራቢዎች እና ተገቢነት ካላቸው የመንግሥት አካላት ባሰባሰበው መረጃ እና ማስረጃ መሠረት የማፍረስና በግዳጅ የማንሳት እርምጃው በርካታ ቤተሰቦችን ለከፍተኛ የኢኮኖሚ እና የማኅበራዊ ቀውስ ዳርጓል፤ ተማሪዎች ከትምህርታቸው ለማቋረጥ ተገደዋል፤ በርካታ ቤተሰቦች የእለት ተእለት ተግባራቸውን ማከናወን የማይችሉበት ሁኔታ ተፈጥሯል፤ በርካታ ቤተሰቦች ተፈናቅለው ወደ ሌሎች ቦታዎች ለመሄድ ተገደዋል፤ ከፊሎቹም መንገድ ላይ ወድቀዋል ወይም በተለያዩ የሀገር ውስጥ መጠለያ ጣቢያ በመሰብሰብ የመንግሥት እርዳታ ለመጠባበቅ ተገደዋል።

የክልሉ መንግሥትና የከተማ አስተዳደሩ የማፍረስና በግዳጅ የማንሳት እርምጃውን ተግባራዊ ከማድረግ በፊት ቤቶቹ እንደተገነቡበት የይዞታ ዓይነትና ሁኔታ፣ ለብዙ ዓመታት የመብራት እና የውሃ እንዲሁም ሌሎች ማኅበራዊ አገልግሎቶችን እየሰጠ እና ነዋሪዎቹ የማኅበራዊ ሕይወት እንዲመሠርቱ ሲያደርግ የቆየ መሆኑን ከግምት ውስጥ በማስገባት አማራጭ መፍትሔዎችን በማመቻቸት የሰብአዊ መብቶች መከበራቸውንና መጠበቃቸውን ሊያረጋግጥ ይገባ ነበር።

ለወደፊትም ተመሳሳይ ኢመደበኛ ይዞታዎች እንዳይስፋፉ ተገቢ የሆኑ የቅድመ መከላከል ሥራዎችን አስቀድሞ መሥራቱ እንደተጠበቀ ሆኖ፤ የማፍረስና በግዳጅ ማስነሳት እንደ መጨረሻ አመራጭ የሚተገበርና አፈጻጸሙም ሰብአዊ መብቶችን ባከበረ መንገድ፣ እንዲሁም ቅሬታዎች በሚጣሩበት ሕጋዊ ሥርዓት ብቻ ሊሆን ይገባል፡፡

ስለሆነም በዚህ የማፍረስና በግዳጅ ማንሳት እርምጃ ለተጎዱ ሰዎች በሕጋዊ መንገድ የመኖሪያ ቤት ሊያገኙ የሚችሉበት መንገድና ለደረሰባቸው የንብረት ውድመት ሊካሱ የሚችሉበት መንገድ በአፋጣኝ ሊመቻች ይገባል።

የኢሰመኮ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ መብቶች ሥራ ክፍል ዳይሬክተር ዶ/ር ብራይትማን ገብረሚካኤል “ኢመደበኛ ይዞታዎቸን መከላከል የመንግሥት ኃላፊነት ቢሆንም የማፍረስና በግዳጅ የማንሳት እርምጃዎች ሰዎች ሕይወታቸው እንዲናጋ እና ቤተሰብ እንዲበተን የሚያደርግ መሆን የለበትም፤ ይልቁንም ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ መብቶች የተከበሩበት አሠራር መሆኑን ማረጋገጥ ይገባል” ብለዋል፡፡

የከረዩ አባ ገዳ በድብደባ መገደላቸውን ነዋሪዎች ገለፁ

በምሥራቅ ሸዋ ዞን የፈንታሌ ወረዳ ነዋሪ የኾኑ የከረዩ አባ ገዳ፣ በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ተደብድበው መገደላቸውን፣ ነዋሪዎች እና የቅርብ ዘመዶቻቸው ተናገሩ። ሌሎች 18 የሚደርሱ አዛውንቶችም ድብደባ እንደተፈጸመባቸው ነዋሪዎቹ ጨምረው ገልጸዋል።

በምሥራቅ ሸዋ ዞን የፈንታሌ ወረዳ ነዋሪ የኾኑ የከረዩ አባ ገዳ፣ በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ተደብድበው መገደላቸውን፣ ነዋሪዎች እና የቅርብ ዘመዶቻቸው ተናገሩ። ሌሎች 18 የሚደርሱ አዛውንቶችም ድብደባ እንደተፈጸመባቸው ነዋሪዎቹ ጨምረው ገልጸዋል።

ስለ ድርጊቱ፣ የኢትዮጵያን መንግሥት አስተያየት ለማካተት ቢሞከርም የተገኘ ምላሽ የለም። ጉዳዩን ያውቀው እንደኾነ የተጠየቀው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን፣ መረጃው ቢደርሰውም ማስረጃ አሰባስቦ አለማጠናቀቁን አስታውቋል።

ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ፣ የሟቹ አባ ገዳ የቅርብ ዘመድ መኾናቸውን በስልክ የገለጹ ግለሰብ፣ በምሥራቅ ሸዋ ዞን ፈንታሌ ወረዳ ውስጥ ነዋሪ የኾኑት የከረዩ አባ ገዳዎች አመራር አባል አቶ ጎቡ ሀዌሌ፣ ባለፈው ቅዳሜ፣ በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች በደረሰባቸው ድብደባ ሕይወታቸው ማለፉን ተናግረዋል፡፡

እኚኹ አስተያየት ሰጪ መንሥኤውን በግልጽ ባልጠቀሱት የኀይል ድርጊት፣ ወደ 18 የሚኾኑ አዛውንቶች መደብደባቸውን ገልጸው፣ በአባ ገዳ ጎቡ ላይ የደረሰው ጉዳት ግን ከባድ ስለነበር ለኅልፈት መዳረጋቸውን እማኝነታቸውን ሰጥተዋል፡፡

ሟቹ ጎቡ ሀዌሌ፣ በገዳ ሥርዐት ስያሜ፣ “አባ ሰበታ” በመባል ነበር የሚታወቁት፡፡ ይኸውም፣ “አባ ቦኩ” በሌለበት የገዳ ሥርዓትን የሚመራ ማለት መኾኑን አስተያየት ሰጪው አስረድተዋል።

Related Stories