ኢትዮጵያ ላይ ተጥለው የነበሩ አንዳንድ ክልከላዎች መነሳታቸው ተቃውሞን አስከተለ

በኢትዮጵያ በሰብዓዊ መብት አያያዞች ላይ መሻሻሎች ታይተዋል በሚል አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ ከጣለቻቸው ክልከላዎች መካከል የተወሰኑት እንዲነሱ ማድረጓ ተቃውሞን አስከተለ።

የዜና ትንታኔ

editors

7/2/2023

በኢትዮጵያ በሰብዓዊ መብት አያያዞች ላይ መሻሻሎች ታይተዋል በሚል አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ ከጣለቻቸው ክልከላዎች መካከል የተወሰኑት እንዲነሱ ማድረጓ ተቃውሞን አስከተለ።

የሰሜን ኢትዮጵያ የእርስ በርስ ጦርነትን ለማስቆም የሰላም ስምምነት ከተደረሰ በኋላ፣ በኢትዮጵያ የተሻለ የሰብዓዊ መብት አያያዝ በመኖሩ አሜሪካ ጥላ ከነበረቻቸው ክልከላዎች የተወሰኑት እንዲነሱ መደረጉን የዋይት ሐውስ የብሔራዊ ደኅንነት ቃል አቀባይ ጆን ኪርቢ ማረጋገጫ ሰጥተዋል።

በሰሜን ኢትዮጵያው የእርስ በርስ ጦርነት ወቅት በሰላማዊ ሰዎች ላይ ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ተፈጽሟል መባሉን ተከትሎ አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ ማዕቀቦችን እና ክልካለዎችን ጥላ እንደነበረ ይታወሳል።

አሜሪካ የፌደራሉ መንግሥት ሠራዊት አባላትን ጨምሮ በጦርነቱ ተሳታፊ የሆኑ ሁሉም ተፋላሚ ወገኖች የጦር ወንጀሎችን ፈጽመዋል ብላ ነበር።

ይሁን እንጂ አሜሪካ ጦርነቱ ለማቆም የሰላም ስምምነት ከተደረሰ በኋላ፣ በአገሪቱ ያለው የሰብዓዊ መብት አያያዝ መሻሻል አሳይቷል ብላለች።

ይህ አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ ይዛ በቆየችው ፖሊሲ ላይ ካሳየችው ለውጥ አንጻር ታዲያ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶችን አላስደሰተም።

አምነስቲ ኢንተርናሽናል እና ሂዩማን ራይትስ ዋች በጋራ ባወጡት መግለጫ “የአሜሪካ መንግሥት በኢትዮጵያ ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እየተፈጸሙ አይደሉም ብሎ ማሰቡ እጅግ አሳስቦናል” ብለዋል።

የመብት ተሟጋች ድርጅቶቹ ከሰላም ስምምነቱ በኋላ በተለይ በምዕራብ ትግራይ አካባቢዎች የዘር ማጽዳት ወንጀሎች እየተፈጸሙ ነው ይላሉ።

የአሜሪካ የአቋም ለውጥ

“የምግብ እርዳታ አቅርቦትን ለጊዜው አቁመን በአንዳንድ ድጋፎች ላይ ተጥለው የነበሩትን ክልከላዎችን እያነሳን ነው” ያሉት የዋይት ሐውስ የብሔራዊ ደኅንነት ቃል አቀባይ ጆን ኪርቢ፤ ክልከላዎቹ መነሳታቸው አሜሪካ በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም እንዲመጣ ለምታደርገው ጥረት አጋዥ ነው ብለዋል።

በሰሜኑ የእርስ በርስ ጦርነት ምክንያት አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ ከምጣኔ ሃብት እና ከደኅንነት ጋር በተያያዘ ከጣለቻቸው ክልካለዎች መካከል የትኞቹ እንደተነሱ ግን በዝርዝር የተባለ ነገር የለም።

ይሁን እንጂ ከጥቂት ቀናት በፊት አንዳንድ የአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ አቅርባ የነበረውን ከሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ጋር የተያያዙ ክሶችን አንስታለች።

‘ፎሬን ፖሊሲ’ የተባለው ጋዜጣ ምንጮቹን ጠቅሶ እንደዘገበው የጆ ባይደን አስተዳደር በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ “ተከታታይ የሆነ የከባድ የሰብዓዊ መብረት ረገጣ እየተፈጸም አይደለም” ብሎ እንደሚያምን ለኮንግረሱ አስታውቋል።

በትግራይ ተቀስቅሶ ወደ አፋር እና አማራ ክልሎች ተዛምቶ ከፍተኛ ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ኪሳራ ባደረሰው ጦርነት ምክንያት፣ ኢትዮጵያ ከአሜሪካ ጋር ያላት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እጅጉን ከመሻከሩ በተጨማሪ ኃያሏ አገር ለኢትዮጵያ ታደርጋቸው የነበሩ ድጋፎችን አቋርጣለች።

ከእነዚህ መካከል የአፍሪካ የእድገትና ዕድል ድንጋጌ (አጎዋ) ተብሎ የሚታወቀው የንግድ መርሃ ግብር ይገኝበታል።

ኢትዮጵያ በዚህ መርሃ ግብር በተለይ የጨርቃ ጨርቅ እና አልባሳት ምርቶችን ከቀረጥ ነጻ ወደ አሜሪካ በመላክ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ከማግኘቷ በተጨማሪ ለበርካ ዜጎች የሥራ ዕድል አስገኝቶላት ነበር።

ይሁን እንጂ አሜሪካ የሰሜኑ ጦርነትን ምክንያት በማድረግ ኢትዮጵያን ከፈረንጆቹ 2022 ጀምሮ ከአጎዋ ሥርዓት ተጠቃሚነት ውጪ አድርጋት ቆይታለች።

የዋይት ሃውስ የብሔራዊ ደኅንነት ቃል አቀባይ አንዳንድ ክልካለዎች መነሳታቸው ይግለጹ እንጂ አሁን ላይ ኢትዮጵያን ወደ የአጎዋ ተጠቃሚነት መመለስን የሚያረጋግጥ አይደለም ብለዋል።

ጆን ኪርቢ የዩናይትድ ስቴትስ የንግድ ተወካዮች ከኤጀንሲዎች ጋር በመሆን ከሰሃራ በታች ያሉ አገራት የአጎዋ ተጠቃሚነትን ዙሪያ በሚያደርጉት ግምገማ በሂደት የሚታይ ይሆናል ብለዋል።

የአሜሪካ ውሳኔ እውነታን የሚቃረን ነው

አሜሪካ በኢትዮጵያ ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እየተፈጸሙ አይደለም ማለቷ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችን አስቆጥቷል።

በዋሽንግተን የሂዩማን ራይትስ ዎች ዳይሬክተር የሆኑት ሳራ ያገር የአሜሪካ ውሳኔ በመላው ኢትዮጵያ የቀጠሉትን የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ችላ ከማለቱ በተጨማሪ፤ ውሳኔው የመብት ጥሰት አድራሾች ከተጠያቂነት ሊያመልጡ ይችላሉ የሚል መልዕክት ያስተላልፋል ብለዋል።

በአሜሪካ የአምነስቲ ኢንተርናሽል ከፍተኛ የሥራ ኃላፊ የሆኑት አማንዳ ክላሲንግ ደግሞ ከጦርነቱ ፍጻሜ በኋላም የኢትዮጵያ መንግሥት ባለስልጣናት በጦርነቱ ወቅት የሰብዓዊ መብት ጥሰት ያደረሱ አጥፊዎችን ለፍትሕ ለማቅረብ ተጨባጭ እርምጃ አልወሰዱም ብለዋል።

"ለፍትሕ እና ተጠያቂነት ቁርጠኝነትን ሳንመለከት፤ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ስለመቀጠላቸው ሪፖርቶችን እየተመለከትን የአሜሪካ መንግሥት ከዚህ ፖለቲካዊ ውሳኔ የደረው ተጎጂዎችን ችላ በማለት ነው" ብለዋል የአምነስቲ ኢንተርናሽል ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዋ።

ከጥቂት ሳምንታት በፊት ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብተ ተሟጋች ሂዩማን ራይትስ ዋች የሰሜን ኢትዮጵያን ጦርነት ለማስቆም የሰላም ስምምነት ከተፈረመ በኋላ በምዕራብ ትግራይ የዘር ማጽዳታ ወንጀል እየተፈጸመ ነው ብሎ ነበር።

የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ የፌደራሉ መንግሥት እና ህወሓት በሰሜን ኢትዮጵያ ሲካሄድ የቆየውን የእርስ በርስ ጦርነት ለማስቆም ጥቅምት 23/2015 ዓ.ም. የሰላም ስምምነት ከፈረሙ በኋላ የአማራ ኃይሎች ከአካባቢው አስተዳደር ጋር በተመተባበር የትግራይ ተወላጆች በኃይል ከምዕራብ ትግራይ እንዲለቁ እያደረጉ ነው ብሏል።