የክልል ልዩ ኃይሎችን ወደ ፌደራልና የክልል ጥታ መዋቅር ውስጥ ማስገባትን በተመለከተ የኢዜማ መግለጫ

HR REPORTS

4/6/20232 min read

የክልል ልዩ ኃይሎችን ወደ ፌደራልና የክልል ህጋዊ የፀጥታ መዋቅር ውስጥ የማስገባት በጎ ጅምር አላስፈላጊ ውዥንብር ፈጥሮ ሌላ ሀገራዊ አደጋ እንዳይጋብዝ ጥንቃቄ ይፈልጋል!

የፌደራል መንግሥት የክልል ልዩ ኃይሎችን ወደ ፌደራልና የክልል ህጋዊ የፀጥታ መዋቅር ሥር እንዲጠቃለሉ ውሳኔ ማሳለፉን ከተለያዩ ምንጮች አረጋግጠናል፡፡ ትላንት መጋቢት 28 ምሽት ላይ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት የሰጠውን መግለጫም ተመልክተናል፡፡ ይህ ውሳኔ በእርግጥም ከመዘግየቱ በስተቀር ተገቢነቱ ላይ ጥያቄ ሊነሳበት አይገባም፡፡ባለፉት ጥቂት የማይባሉ ዓመታት ከሕጋዊ አሠራር ውጪ እንዲቋቋሙ የተደረጉ የክልል ልዩ ኃይሎች በፌደራል መንግሥት የፀጥታ ዕዝ ሥር እንዲገቡ መደረጉ ተገቢም ልክም ነው፡፡

ፓርቲያችን የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) የዘውግ ፖለቲካ ነፀብራቅ የኾኑ የክልል ልዩ ኃይሎች እየፈጠሩ ከነበረው ሀገራዊ አደጋ አንፃር ከስመው ወደ ህጋዊ የፀጥታ መዋቅር ውስጥ እንዲገቡ፤ በተለያዩ የትንታኔ ሰነዶቹ እና በምርጫ ክርክር መድረኮች ጭምር ሲሟገት እንደነበር ይታወቃል፡፡ ይህ የኢዜማ አቋም እና ስጋት ትክክለኛነት የትግራይ ክልል ልዩ ኃይሎች የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ላይ በከፈቱት ጦርነት በገሃድ ተረጋግጧል፡፡

ለአንድ ዘውግ ወይም ክልል ብቻ ጠባቂ ኾኖ የሚቋቋም ልዩ ኃይል ሀገር እና ሕዝብ ላይ አደጋ እንደሚፈጥር የታየው በትግራይ ክልል ታጣቂዎች ብቻ ሳይኾን በኹሉም የሀገራችን አካባቢዎች ተመሳሳይ ዝንባሌ እያስተዋልን ነው፡፡ በአስተዳደር ወሰን ይገባናል ጥያቄ መነሻ የኦሮሚያ ፣ የሶማሌ፣ የአማራ፣ የሲዳማ፣ የአፋር እና የቤንሻንጉል ልዩ ኃይሎች አንዳቸው ከሌላኛው ጋር መጋጨታቸው የአደባባይ ምሥጢር ነው፡፡ ይህ ሁኔታ አሁንም ድረስ በአንዳንድ ክልሎች መካከል እየቀጠለ ነው፡፡ ይህም ንፁሀን ዜጎችን ከመጉዳቱም ባሻገር የሀገር ሉዓላዊነት ላይ አደጋ ደቅኗል፡፡ በመኹኑም፤ ከሕግ አግባብ ውጪ በአንድ ክልል ወይም ዘውግ ጠባቂነት የተቋቋሙ የክልል ልዩ ኃይሎች ከስመው በህጋዊ የፀጥታ መዋቅር ሥር መጠቃለላቸውን የምንደግፈው ተገቢ ውሳኔ ነው፡፡

አፅንኦት ሰጥተን የምናሳስበው ጉዳይ ቢኖር የክልል ልዩ ኃይሎች ወደ ህጋዊ የፀጥታ መዋቅር ሥር መግባታቸውን ከልባችን የምንደግፈው ውሳኔ ሆኖ እያለ ፤ አተገባበሩ ፈንጅ የማምከን ያህል ከፍተኛ ጥንቃቄ እንደሚፈልግ ግን ለሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ኹሉ ለማሳሰብ እንወዳለን፡፡ በተለይም በሀገራችን ሥር ከሰደደው የዘውግ ፖለቲካ ጡዘት አኳያ አፈጻጻሙ በተጠና መልኩ መኾን አለበት፡፡

እንደምሳሌ የምናነሳው በቅርቡ ከአሸባሪነት መዝገብ እንዲፋቅ የተደረገው የህወሓት ቡድን በሚቆጣጠራቸው መገናኛ ብዙኃን በኩል በአሁኑ ወቅት በአማራ ክልል ሥር ያሉ አካባቢዎችን ስለማስመለስ እንደሚሠራ በስፋት እያስተጋባ ባለበት በዚህ ወቅት፤ ይህንን ውሳኔ በጥድፊያ እና በድብቅ ተግባራዊ ለማድረግ መሞከር አደገኛ ውጤት እንደሚያመጣ የፌደራል መንግሥት ሊገነዘበው ይገባል፡፡ ህወሓት የታጠቃቸውን መሣሪያዎች መፍታቱ በግልጽ ባልታወቀበት ሁኔታ የትግራይ አዋሳኝ ክልሎች ዳግም የመወረር ስጋት ቢያድረባቸው የሚያስወቅስ አይደለም ፡፡ ስለዚህም የውሳኔውን አፈጻጸም ቅደም ተከተል በተመለከተ ጥንቃቄ መደረግ እንዳለበት ኢዜማ ያምናል፡፡

ከላይ በጠቀስነውና ይህን በመሰሉ ሌሎች ምክንያቶች የተጀመረው በጎ እርምጃ አላስፈላጊ ውጥንቅጥ ፈጥሮ ሌላ ሀገራዊ አደጋ እንዳይጋብዝ የሚከተሉት ጥንቃቄዎች እንዲደረጉ እናሳስባለን፡፡

1) መንግሥት የክልል ልዩ ኃይሎችን ወደ ህጋዊ የፀጥታ መዋቅር ውስጥ ለማካተት የወሰነውን ውሳኔ እስካመነበት እና ሌላ ድብቅ የፖለቲካ ሴራ ከሌለ በስተቀር፤ ውሳኔውን በድብቅ ለማስፈጸም የሚያደርገው እንቅስቃሴ አላስፈላጊ ውዥንብር እንዱሁም ግጭት ከመፍጠር ያለፈ ፋይዳ እንደሌለው መገንዘብ አለበት፡፡ ሰለሆነም ልዩ ኃይሉን ወደመደበኛነት ለመቀየር የሚከተለውን ፍኖተካርታ ደረጃ በደረጃ አካሄዱን ለህዝብ በተደጋጋሚና ግልፅ በሆነ መልኩ በተለያዩ ቋንቋዎች ማብራሪያ መሰጠት አለበት። ይህ በማህበረሰቡ ውስጥ የሚፈጠረውን ውዥንብር ከማጥፋቱም በላይ በመንግስት እና በሂደቱም ላይ ያለውን ጥርጣሬ ይቀንሳል ብለን እናምናለን።

2) የሁሉንም ክልሎች ልዩ ኃይሎች ወደ ህጋዊ የጸጥታ ተቋማት ውስጥ ማካተት የሚኖረውን ሀገራዊ ጠቀሜታ እና አፈጻጸም በተመለከተ ከኹሉም የክልል መንግሥታት ኃላፊዎች እና የፀጥታ ተቋማት ጋር ተነጋግሮ መግባባት ላይ መድረስ በቅድሚያ ሊኾን እንደሚገባ ለማስታወስ እንወዳለን፡፡

3) የጉዳዩን ሀገራዊ ፋይዳ ለሚመለከታቸው የሀገራችን የፖለቲካ ልሂቃን ከማስረዳት ጀምሮ፤ ይህንን ውሳኔ ሰበብ በማድረግ ሊሸረቡ ከሚችሉ ፖለቲካዊ ደባዎች መታቀብም በከፍተኛ ደረጃ ሊታሰብበት ይገባል፡፡ ከአንዳንድ የፖለቲካ ተዋንያን እየተሰማ እንዳለው “የአንዱን ክልል ልዩ ኃይል አፍርሶ ሌላኛውን በድብቅ የማጠናከር ሴራ” እንዳይኖር ማድረግ እንደሚገባም ውሳኔውን ለሚያስፈጽሙ የሀገር መከላከያ እና የፌደራል ፖሊስ አዛዦች በጥብቅ እናሳስባለን፡፡

4) የክልሎች ልዩ ኃይሎች ወደ ፌደራል እና የክልል የፀጥታ መዋቅር ውስጥ በሚገቡበት ይሁን የሲቪል ማህበረሰቡን በሚቀላቀሉበት ጊዜ አስተማማኝ የግንዛቤ ማስጨበጫ መርኃግብር ወይም ተሃድሶ ሊከናወን ይገባል፡፡ የክልል ልዩ ኃይሎች አባላት ወደ ህጋዊ የፀጥታ መዋቅር ዕዝ ሥር እንዲገቡ የተደረገበትን ሀገራዊ ፋይዳ ማሳወቅ፤ የሚኖራቸውን የግልፅነት ጥያቄ መመለስ እና የወደፊት ዕጣ ፈንታቸውን በተመለከተ ማስተማመኛ መስጠትም በውዥንብር ምክንያት ሊፈጠሩ የሚችሉ ተግዳሮቶችን እንደሚያስቀር መገንዘብም ከመንግሥት አካላት ይጠበቃል፡፡

5) በብልፅግና ፓርቲ ውስጥ ያለውን ሽኩቻ ከፍ ሲል ወደ መንግስት ብሎም ወደ ህዝብ ውስጥ ተሰራጭቶ ለሀገር ስጋት እንዳይፈጥር፤ የፌደራሉ መንግሥት ይህንን ውሳኔ ለማስፈጸም የሚያደርገው ተግባራዊ እንቅስቃሴ በጥድፊያ እንዲሁም በማንአለብኝነት ሳይኾን በመግባባት፤ በመተማመን እና በግልጸኝነት መንፈስ ሊኾን ይገባል፡፡ ይህን ባለማድረግ ለሚፈጠር ውዥንብር፤ ግጭት እና ውድመት የፌደራሉ መንግሥት ተጠያቂ መኾኑን ተገንዝቦ ውሳኔውን በጥንቃቄ እንዲያስፈጽም እናሳስባለን፡፡

ለኹሉም የፖለቲካ ተዋንያን በሙሉ የምናስተላልፈው መልዕክት የክልል ልዩ ኃይሎችን የፈጠረው መዋቅራዊ አሠራር ጭምር በጥልቀት እንዲታሰብበት ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት በሀገራችን ክልሎች፤ መገናኛ ብዙኀን፤ የንግድ ተቋማት፤ ባንኮች፤ የስፖርት ቡድኖች፤ የሙያ ማኅበራት፤ የምሑራን ስብስብ እና ሌሎችም መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልኾኑ ተቋማት በአንድ ዘውግ ስም ተቋቁመው የኢትዮጵያ ሕዝብ ተባብሮ ወደ ልማት ሳይኾን ተከፋፍሎ ወደ እርስ በእርስ ግጭት እንዲገባ እንደሚያደርጉት ለአፍታም መዘንጋት የለበትም፡፡

ይህ የዘውግ ክፍፍል ወደ ሰማያዊዎቹ የሃይማኖት ተቋማት ጭምር ገብቶ ችግር ፈጥሯል፡፡ አንድ ተቋም ለአንድ ዘውግ ጥቅም ብቻ ሲቋቋም በአንድ ሀገር ሕዝብ መካከል “እኛና እነሱ” የሚል ክፍፍል እና አሉታዊ ፉክክር በመፍጠር የግጭት መንስኤ እንደሚኾን መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ የክልል ልዩ ኃይሎችም የዚሁ የዘውግ ፖለቲካ ነፀብራቅ እንደኾኑ መታወቅ አለበት፡፡ ስለዚህም፤ የዚህ ሕጋዊ እና መወቅራዊ የዘውግ ክፍፍል መነሻ ምክንያት የኾነው የዘውግ ፖለቲካ ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ ከሀገራችን ሊወገድ ይገባል፡፡

ፓርቲያችን ኢዜማ ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ እንደወተወተው፤ የዘውግ ፖለቲካ ካልተወገደ ኢትዮጵያ አትድንም፡፡ ስለኾነም፤ ሀገራችን በዘላቂነት እፎይታ እንድታገኝ ከዘውግ ፖለቲካ ወደ ዜግነት ፖለቲካ መሸጋገር ምርጫ ሳይኾን ግዴታ ነው፡፡ ይህ እንዲሳካም መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ከፓርቲያች ጎን ቆሞ የፖለቲካ ተሳትፎ እንዲያደርግ ጥሪ እናቀርባለን፡፡

#የዜግነት_ፓለቲካ

#ማኅበራዊ_ፍትህ

#ኢዜማ

Related Stories