አማራን በስልጣን ልታሸማቅቁት አትችሉም!

ነፃ ሃሳብ

4/4/20232 min read

በ ጌታቸው ሽፈራው

አማራ ስልጣን እንደማይገባው አድርገው ራሳቸውን ካሳመኑ ቆይተዋል። አማራን ምኒልክ፣ አጤ ምኒልክን ደግሞ በሀሰት "ሂትለር" እያሉ ሙዚቃ ሁሉ እንዲወጣ አድርገዋል። አማራን በሀሰት እንደ ናዚ ቆጥረው ስልጣን የማይገባ ብለው ራሳቸውን በኦነግ ትርክት አለማምደዋል። አማራ ስልጣን ፈልጓል ብለው መወንጀያ፣ ማሸማቀቂያ እያደረጉት ነው። የሆነው ግን ሌላ ነው፥

1) ኦርቶዶክስ ከትርክታችን ጋር አትመችም ብለው የራሳቸውን ቡድን ሲያዋቅሩ ያልተጠበቁት ተቃውሞ ገጠማቸው። ይህን ተቃውሞ አቅጣጫ አስቀይረው "አማራ ወደ ስልጣን ሊመጣ ነው" ብለው ጫካም ውጭ አገር ያለውንም ተገንጣያቸውን አብረን እንስራ ብለው ለመሰባሰብ ጣሩ። አማራ፣ከኤርትራ ጋር ሆኖ መፈንቅለ መንግስት ሊያደርግብን ነው እንዳላሉ የኤርትራ ባለስልጣናት አዲስ አበባ ሰንብተዋል።

2) ይህ ፍረጃ የተለመደ ነው። ሀጫሉን ራሳቸው በኦሮሞ አስገድለው አማራን አስረዋል። ከአስራት ሚዲያ በህዳር የለቀቀን ሰራተኛ ሰኔ በተፈፀመ ወንጀል አስረውታል። ስራ ላይ ያልነበረን፣ ቀጥታ ስርጭት አስተላልፎ የማያውቅን አስራት ሚዲያ በቀጥታ ስርጭት ግጭት ቀሰቀሰ ብለው ጋዜጠኞቹን አስረዋል። በምርጫው ወቅት "ዐንድ አማራ የሚባህ ድርጅት ለሽብር ያሰማራቸው" ብለው ምንም የሌሉበትን ሰዎች ስም በዶክመንተሪ አንስተዋል። በወቅቱ ሀሰታቸውን በሚገባ አጋልጠናል። የራሳቸውን ደህንነት ሰራተኞች የሽብር ቡድን አባል ብለው በሚዲያ አቅርበዋል።

3) ሰሞኑን አማራን ከስልጣን ድርሽ ማለት የሌለበት ብለው በጥላቻ ለያዙት አቋም ሰበብ አግኝተዋል። ክርስቲያን ታደለ ከጥያቄው በፊት ከህዝብ ጋር እንዳያያይዙት፣ የመፈንቅለ መንግስት ወዘተ እንዳይሉት አስጠንቅቆ ያነሳውን ጥያቄ የስልጣን ንጥቂያ አድርገው አማራን ፈረጁበት። ቀሰቀሱበት። ይህ ግን አልበቃቸውም።

4) ዛሬ "ባለስልጣናትን ለመግደል" በሚል አዲስ ክስ አምጥተዋል። አማራ ክልል ላይ ብቻ ሳይሆን ሌሎች አካባቢዎችም መሰል እንቅስቃሴ ያለ አስመስለው አቀረቡት። ይህን ጉዳይ የሴራ እንደሆነ የሚያሳየው ሰሞኑን የጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካሪ የሆነው አዲሱ አረጋና ሌሎችም ሲያነሱት የሰነበቱት ነው። "ስልጣን ልቀቅ" የሚለውን አንስተው የዘር ፍጅት ቅስቀሳ ላይ ናቸው። እነ አዲሱ አረጋ ትናንት "ስልጣን ለእኛ ነው የሚገባን" የሚሉ አሉ ብለው የፃፉትን ዛሬ ሚዲያዎች በወንጀልነት አምጥተው አሰርናቸው ለሚሏቸው ሰዎች ሰጥተዋቸዋል። አካሄዱ የተቀናጀ ፕሮፖጋንዳ ተደርጎበታል። በባዶ ላደረባቸው ፍርሃት "ይሄው" የሚሉት ጉዳይ ለማቅረብ ይመስላል።

5) እነዚህ አማራን ስልጣን እንደማይገባው ባልታወጀ ህግ የመፈረጅ አካሄድ ሰንብቷል። መንገደኞችን ጭምር ወደ አዲስ አበባ ስልጣን ፍለጋ የሚሄዱ፣ መንግስትን የሚገለብጡ ተደርጎ መጀመርያ በፌስቡከኛ፣ ቀስ እያለ በኦነግ ሚዲያ፣ ከዛም በእነ አዳነች አቤቤ፣ ከዛም በጠቅላይ ሚኒስትሩ ተነግሯል።

6) አዲስ አበባ ውስጥ የሚገኘውን አማራ ለስልጣናችን ስጋት ነው ተብሎ ተነግሯል። የባጃጅ አሽከርካሪዎችን ጨምሮ ሌላው ለአመፅ መጠቀሚያ ይሆናልና እናባረዋለን ብለዋል። ከሸገር ከተማ ጀምረው እስከ አዲስ አበባ የሚሰሩት ከዛ የተሳሳተና የጥላቻ ውሳኔ የተነሳ ነው። ክርክር ተደርጎበታል። አይጠቅምም ያሉ ሰዎችም አሉ። ከዚህ ቀደም ብሎ ላለፉት አራት አመታት ሆን ብለው ባዋቀሩት ታጣቂ ጭምር አማራውን ከኦሮሚያ አፈናቅለዋል። አሁን አዲስ አበባ ደረሰ። ለዚህ የዘር ፍጅታቸው ሰው እየፈለጉለት ነው።

በግሌ በግድያም ሆነ በሌላ ወንጀል የተሳተፈ ሰው ካለ ልከላከል አልችልም። እየሆነ የከረመው፣ እየሆነ ያለው ግን የዘር ጭፍጨፋው አካል ነው። "ስልጣናችን ንኩና ህዝብ ያልቃል፤ አገር ይፈርሳል" ከሚለው የዘር ጭፍጨፋ ቅስቀሳ ጀምሮ፣ ሰሞኑን "ስልጣን ነጠቃ" ወዘተ የሚለው በራሳቸው የጥላቻ ህግ "አማራ ስልጣን አይገባውም" ብለው ያወጁት የጥላቻቸው ውጤት ነው። አማራ ስልጣን ይገባዋል። ያን በሰላማዊ መንገድ ይጠይቃል። ስልጣኑን ሌላውንም ይዞ በወንጀል ስም፣ አገር ይፈርሳል፣ ህዝብ እጨርሳለሁ እያሉ ማሸማቀቅ አይቻልም። አማራ ህግ አዋቂ፣ በራሱ ደም በምትታጠብ ኢትዮጵያ እንኳን ስክነትን የመረጠ ህዝብ ነው። በስልጣን ልታሸማቅቁት አትችሉም። እንደ ናዚ "ከስልጣን ድርሽ እንዳይል" የምትሉበት የጥላቻ ህጋችሁም ተቀባይነት የለውም።

7) ሰዎች ተሰባስበው ስልጣን እንፈልጋለን ቢሉ፣ ለግድያ ቢሰማሩ ኖሮ እንኳን የሚቀርበው በዚህ መልክ ሊሆን እንደማይገባ ግልፅ ነው። አሁን እየሆነ ያለው በባዶ ስጋት ሲሰራ ለነበረው ፕሮፖጋንዳና ወንጀል ማረጋገጫ ለማስመሰል፣ በሰበቡ የዘር ፍጅት ለመፈፀም፣ "ስልጣን ልትነጥቅ" የሚባል አዲስ ማሸማቀቂያ ህዝብን ማጥቃትና አንገት ማስደፋት ነው።

ይህ ሰበብ ተፈልጎ የሚደረግ አደገኛ የዘር ጭፍጨፋ ቅስቀሳ እጅግ አውዳሚ ነው። አገር ፈርሶ የሚድን የተወሰነ አካባቢ የለም። የዘር ፍጅት ተፈፅሞ የሚቆይ ስልጣን የለም። ህዝብን "ስልጣን ልትወስድ" እያሉ አሸማቅቆ የሚፀና ስልጣን የለም።

አማራው ለዘመናት በህገ ልቦና የኖረ ህዝብ ነው። ቅሬታ በቀረበብህ ቁጥር "ስልጣኔን ልትወስድ" እያልክ አታሸማቅቀውም። "ወንበሩ" ዛፍ ቆርጠህ የጠረብከው የዘመዳዝማድ፣ ለዘላለም የምትጎለትበት አይደለም። በሰላማዊ መንገድ ለማንም ትለቃለህ፣ ካላወቅክበት እንደ ህዝብ ሳይሆን ከጎንህ ያለውም ሊቀማህ ይችላል። ባንቀላፉህ፣ አቅም ባጣህ፣ በቃዠህ ቁጥር ግን አማራን አታሸማቅቅበትም!

Related Stories