በውሸት ክስ ሽብርተኛ ተብዬ ተከስሼ ስደተኛ ሆኜ መቅረት አልፈልግም” አቶ ልደቱ አያሌው

የኢትዮጵያ መንግሥት በውጭ አገራት ሆነው ግጭት በመፍጠር የክልል እና የፌደራል መንግሥትን በኃይል ለመጣል ተንቀሳቅሰዋል በሚል ተላልፈው እንዲሰጡት ጥያቄ ከቀረበባቸው ግለሰቦች መካከል አንዱ የሆኑት አቶ ልደቱ አያሌው ክስ ከተመሠረተባቸው ወደ ኢትዮጵያ እንደሚመለሱ ለቢቢሲ ገለጹ።

የዜና ትንታኔ

editors

5/11/20231 min read

የኢትዮጵያ መንግሥት በውጭ አገራት ሆነው ግጭት በመፍጠር የክልል እና የፌደራል መንግሥትን በኃይል ለመጣል ተንቀሳቅሰዋል በሚል ተላልፈው እንዲሰጡት ጥያቄ ከቀረበባቸው ግለሰቦች መካከል አንዱ የሆኑት አቶ ልደቱ አያሌው ክስ ከተመሠረተባቸው ወደ ኢትዮጵያ እንደሚመለሱ ለቢቢሲ ገለጹ።

በዚህ ዝርዝር ውስጥ ከተካተቱት 11 ግለሰቦች መካከል አንዱ የሆኑት ታዋቂው ፖለቲከኛ አቶ ልደቱ እስካሁን ክስ እንዳልተመሠረተባቸው በጠበቃቸው እንደተነገራቸውና፣ ክስ ከተመሠረተባቸው ግን ከአሜሪካ ወደ ኢትዮጵያ እንደሚመለሱ ከቢቢሲ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ገልጸዋል።

“. . .ከጠበቃዬ ጋር እየተነጋገርኩ ነው። እስካሁን ክስ አልተመሠረተብኝም። ዝም ብሎ በራድዮ እና በቴሌቪዥን ይነገራል እንጂ የቀረበ ክስ የለም። ክስ ሲመሠረት ነው የምሄደው” ብለዋል።

ለልብ ሕመም አሜሪካ የሕክምና ክትትል እያደረጉ ያሉት አቶ ልደቱ፣ ክስ ከተመሠረተባቸው የሕክምና ቀጠሯቸውን አቋርጠውም ቢሆን ወደ አገር ቤት እንደሚመለሱ ተናግረዋል።

“ክስ ከመመሥረቱ በፊት መሄዴ ጥቅም የለውም። በጊዜ ቀጠሮ መጉላላት ነው እንጂ ምንም ፋይዳ የለውም። እስከዚያ ድረስ ሕክምናዬን እከታተላለሁ” ብለዋል።

አክለውም “ክስ ሲመሠረት ግን፣ ዳኞቹ የሚቀጥለው ሕክምናዬ ድረስ እንድቆይ የሚፈቅዱ ከሆነ እቆያለሁ። የማይፈቅዱ ከሆነም የሕክምና ቀጠሮዬን አቋርጬ እሄዳለሁ” ሲሉም አስረድተዋል።

የፀጥታ እና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይል ከሳምንት በፊት ባወጣው መግለጫ፣ አቶ ልደቱን ጨምሮ “ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን በኃይል ለማፍረስ እና በሽብር ወንጀል ቡድን ውስጥ በሕቡዕ ሲንቀሳቀሱ ነበር" የተባሉ ግለሰቦችን ሀብት የመቆጣጠር እርምጃ እንደሚወሰድ አሳውቋል።

ጨምሮም “በአማራ ክልል ሕገ መንግስታዊ ሥርዓቱን በማፍረስ ክልላዊ ሥልጣንን በኃይል ለመያዝ በአገር ውስጥ እና በውጭ አገራት በሕቡዕ ተደራጅተው እና ተቀናጅተው በሚንቀሳቀሱ ጽንፈኛ ኃይሎች ላይ የማያዳግም ሕጋዊ እርምጃ” እንደሚወስድ ገልጿል።

አቶ ልደቱን ጨምሮ 11ዱ ግለሰቦች “በፈፀሙት የሽብር ተግባር እንደሚፈለጉ እና ከዓለም አቀፉ የፖሊስ ድርጅት (ኢንተርፖል) ጋር በመተባበር በቁጥጥር ሥር በማዋል ለሕግ እንደሚቀርቡ” ተገልጿል።

አቶ ልደቱ በበኩላቸው፣ የሽብርተኛነት ክሱን ከሰሙ በኋላ ወደ አገር ቤት ለመመለስ መወሰናቸውን ለቢቢሲ ገልጸዋል።

“የሕክምና ቀጠሮ ስለነበረኝ ነው እንጂ መጀመሪያም የመጣሁት እዚህ ለመኖር አይደለም። በቅርብ ጊዜ ወደ አገሬ እመለሳለሁ ብዬ እያሰብኩ ነበር። የዘገየሁት ያልተቋጨ የሕክምና ቀጠሮ ስለነበረኝ ነው። የሽብርተኛነት ክስ ሲመጣ ካሰብኩት ጊዜ ፈጥኜ ነው የምሄደው አልኩ” ብለዋል።

አሜሪካ የሚያቆያቸው የሕክምና ቀጠሮ ቢኖራቸውም የሕግ ተፈላጊ ከሆኑ ወደ ኢትዮጵያ መመለሳቸው እንደማይቀር ገልጸዋል።

“የሕግ ተፈላጊነት ካለ፣ በሽብርተኛነት የመጠየቅ ጉዳይ ካለ፣ እኔ ከፍርድ ቤት ውሳኔ እና ጥያቄ ርቄ መኖር ስለማልፈልግ ነው ለመሄድ የወሰንኩት” ብለዋል።

በመግለጫው ከተካተቱ ግለሰቦች መካከል የተወሰኑት በቁጥጥር ሥር ውለው በተጠረጠሩበት የሽብር ወንጀል ፍርድ ቤት መቅረባቸው ባለፉት ቀናት ሲዘገብ ነበር።

አቶ ልደቱም ሊታሰሩ እንደሚችሉ ቢረዱም ወደ አገር ቤት ግን እንደሚመለሱ አስረግጠዋል።

“. . .አገሪቱ ካለችበት ሁኔታ አንጻር ተመልሼ ለመውጣት ችግር ሊገጥም ይችላል ብዬ ነው እስካሁን የዘገየሁት። አሁንም የሕክምና ቀጠሮ አለኝ። ግን የሕግ ተጠያቂነት ከመጣ ምንም ማድረግ አይቻልም” ብለዋል።

ወደ አገር ቤት ለመመለስ የወሰኑበትን ምክንያት ሲያስረዱም “አንደኛ የተከሰስኩበት ወንጀል በፍጹም ከእኔ ታሪክ እና ማንነት ጋር የማይሄድ ነው። ሥርዓቱ ደግሞ ይሄንን ያደረገበት የራሱ ምክንያት አለው። አንደኛው ምክንያት፣ እንደዚህ ዓይነት ክስ ፈርቼ ወደ አገሬ እንዳልመለስ ለማድረግ ስለሆነ ይሄንን በፈቃደኛነት ለመቀበል ዝግጁ አይደለሁም።”

ያለባቸው የልብ ሕመም “ከፍተኛ ጥንቃቄ እና ክትትል” የሚጠይቅ ቢሆንም ወደ አገር ቤት መመለስ “የትግሉ አካል” እንደሆነ ያምናሉ።

“ሰላማዊ ታጋይ ነኝ። ሁልጊዜም በሕግ ነው የምተማመነው። ካሁን ቀደምም አምስት ስድስቴ ታስሬ በፍርድ ቤት ነው ነጻ የሆንኩት። አሁንም በዚያ መንገድ ሄጄ የግድ ሥርዓቱን መጋፈጥ አለብኝ በሚል ነው የምመለሰው” ሲሉ አስረድተዋል።

አቶ ልደቱ ከቢቢሲ ጋር ባደረጉት ቆይታ “ማናችንም ላለመታሰር፣ ዋጋ ላለመክፈል የየራሳችን ምክንያት ይኖረናል። ትግል ሲባል ግን እነዚህን ሁሉ ነገሮች ጥሶ መከፈል የሚገባውን ዋጋ መክፈል ነው” ሲሉ አቋማቸውን ገልጸዋል።

ወደ አገር ቤት ሲመለሱ ሊገጥማቸው የሚችለውን ችግር ቢገነዘቡም ለመጋፈጥ ዝግጁ እንደሆኑም አስምረውበታል።

“. . .ስሄድ የሚገጥመኝ ችግር ቀላል ነው ብዬ አይደለም። ከባድ እንደሚሆን አምናለሁ። ያ ችግር ምናልባት ሕይወቴንም ጭምር የሚያሳጣ ሊሆን ይችላል” ብለዋል።

“ግን ኢትዮጵያ ያለችበት ሁኔታ፣ ሕዝቡ ያለበት ሁኔታ፣ ሰዎች በዚህ ደረጃ ዋጋ ለመክፈል ካልተዘጋጀንና ካልከፈልን ይለወጣል የሚል እምነት የለኝም። በእኔ ደረጃ ያለ ሰው ያን ዋጋ መክፈል እና ለትግሉ አርአያ መሆን አለበት ብዬ አምናለሁ” ሲሉም አክለዋል።

ኢትዮጵያ ሲገቡ በፖሊስ ወደ እስር ቤት ሊወሰዱ እንደሚችሉ እያወቁ ወደ አገር ቤት ለመመለስ እንዴት ወሰኑ? ተብለው በቢቢሲ የተጠየቁት አቶ ልደቱ ሲመልሱ፣ “ልምዱ አለኝ። መታሰር የመጀመሪያዬ አይደለም። በዚህ ዓይነት ትግል ውስጥ ላለፉት 31 ዓመታት ቆይቻለሁ። ወደ ስድስት ጊዜ ስለታሰርኩ ለእኔ አዲስ ነገር አይደለም” ሲሉ መልሰዋል።

ከእሳቸው ጋር በተመሳሳይ መግለጫ ውስጥ የተጠቀሱት ሰዎች “እየታደኑ እያተሰሩ እንደሆነ አውቃለሁ” ያሉት አቶ ልደቱ፣ “ኤርፖርት የሚጠብቀኝ ፖሊስ እንደሚሆን እና እንደምታሰር አውቃለሁ። የሥነ ልቦና ዝግጅት አለኝ” ሲሉ ገልጸዋል።

“. . .እንኳንስ አሁን መከሰሴን አውቄና ባልተከሰስኩበትም ሁኔታ፣ መቼውንም ጊዜ እንዲህ ዓይነት ነገር ሊገጥመኝ እንደሚችል በሥነ ልቦና ሁልጊዜም ዝግጁ ነኝ። እኔ ላይ ምንም ዓይነት መረበሽ የለም” ሲሉ አሁን ስላላቸው ስሜት ለቢቢሲ ገልጸዋል።

እስርን ለመቀበል ዝግጁ እንደሆኑ የገለጹት ፖለቲከኛው “የምጠብቀው የለመድኩት ነገር ነው። ሥርዓቱ እስካለ ድረስ ከዚህም በላይ የሆነ ዋጋ የሚያስከፍል ነገር ሊኖር እንደሚችል እጠብቃለሁ” ብለዋል።

ይኖሩበት በነበረው አሜሪካ ጥገኝነት መጠይቅ ቢችሉም ይህ ግን ከእሳቸው አቋም ጋር የሚጻረር እንደሆነም አልሸሸጉም።

“ጥገኝነት መጠየቅ አቅቶኝ አይደለም። ብጠይቅ፣ ካለብኝ የፖለቲካ ችግር አንጻር በቀላሉ ተቀባይነት ላገኝ እችላለሁ። ግን ፍላጎቴ አይደለም። በምንም ተአምር ተሰድጄ መኖር አልፈልግም። ታጋይ ነኝ። ለትግሉ ደግሞ የወጣትነት ጊዜዬን አሳልፌያለሁ። 31 ዓመት ነው የታገልኩት። ከዚህ በኋላ ምንም የምሳሳለት እና አልከፍለውም የምለው ነገር የለም። የሚጠብቀኝ ነገር ከባድ እንደሆነ በሚገባ እረዳለሁ።”

ወደ ኢትዮጵያ እንደሚመለሱ ሲያሳውቁ ከወዳጅ ዘመዶች ምን ምላሽ እንደተሰጣቸው ተጠይቀውም ሲመልሱ “ዘመዶቼ፣ ጓደኞቼ፣ የትግል ጓደኞቼ፣ የሐሳብ ደጋፊዎቼ ሁለት ዓይነት አመለካከት አላቸው። ያለብኝን የጤና ችግር በመገንዘብ መመለሴ አደጋ እንዳለው በማወቅ እንዳልመለስ የሚፈልጉና ግፊት የሚያደርጉብኝ አሉ። የአላማ ሰው መሆኔን በማወቅ ትክክለኛ ውሳኔ ነው የወሰንከው ብለው እየደገፉኝ ያሉ አሉ። ዞሮ ዞሮ ውሳኔዬን ሊያስቀይር የሚችል ነገር የለም” በማለት ነው።

አቶ ልደቱ አክለውም ወደ አገር ቤት የመመለሳቸውን ነገር ለሰብአዊ መብት ድርጅቶች እንዳሳወቁም ጠቅሰዋል።

አገሪቱ ከፍተኛ ውጥረት ውስጥ ከመሆኗ አንጻር ወደ አገር ቤት ከተመለሱ በኋላ የትግል ስልት ሊቀይሩ ይችላሉ? በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ መልሳቸው “የሚቀየር ነገር አይኖርም” የሚል ነው።

“በኢትዮጵያ ፖለቲካ አንዳንድ ሰዎች የያዙትን አቋም እንደኔ ዓይነት ጫና ሲገጥማቸው የሚለውጡበት ሁኔታ በተደጋጋሚ ይታያል። እኔ ላይ ብዙም እንደዚህ ዓይነት ነገር አይሠራም” ብለዋል።

አቶ ልደቱ እንደሚሉት፣ “እኔ የያዝኳቸውን አመለካከቶች እንዲሁ ዝም ብዬ በስሜት ወይም በጊዜያዊነት ሳይሆን አስቤባቸው እና አምኜባቸው የያዝኳቸው አቋሞች ናቸው።”

የፖለቲካ አሰላለፍ ይቀይሩ እንደሆነ ተጠይቀው፣ “ሰላማዊ ትግልንም ሆነ ሌላ ዓይነት የፖለቲካ ኃይል አሰላለፍን በሚመለከት ድሮ ከነበረኝ የተለየ ነገር የለም። ይኖራል ብዬም አላምንም” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።

“እንዲህ ዓይነት ጫና ሲመጣ ያሉበት ቦታ ጠንክሮ መቆም ነው እንጂ በሁኔታዎች አስገዳጅነት ተገፍቶ ወደሌላ አቅጣጫ የመሄድ ፍላጎት የለኝም። ስለዚህ ከነበረኝ አስተሳሰብ ብዙም የተለየ አዲስ ነገር አይኖርም” ሲሉም አቋማቸውን አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ከኢንተርፖል እገዛ ከመጠየቁ ጋር በተያያዘም “ኢንተርፖል የአፋኞች ተባባሪ አይደለም። ሕግ እና ሥርዓትን ተከትሎ የሚሠራ ተቋም ነው” በማለት፣ የአሜሪካ መንግሥት እንደሳቸው ያሉ ሰዎችን አሳልፎ እንደማይሰጥም እምነታቸውን ገልጸዋል።

“እዚህ ያለው መንግሥት ኢትዮጵያ ውስጥ ምን ዓይነት ሁኔታ እንዳለ ያውቃል። አሜሪካ ውስጥ [የሌላ አገር] መንግሥት እንደዚህ ብሎ ሰዎችን ስለፈረጀ ሰዎች ተይዘው ዲፖርት አይደረጉም[አይባረሩም]” ብለዋል አቶ ልደቱ።

ወደ አገር ቤት ለመመለስ የወሰኑት “በኢንተርፖል ላለመያዝ” ወይም “የአሜሪካ መንግሥት አሳልፎ እንዳይሰጣቸው” በመስጋት እንዳልሆነም ፖለቲከኛው ገልጸዋል።

“የ27 ዓመቱ ሥርዓት ብዙ ሰዎችን በሽብርተኛነት ፈርጆ ነበር። አንድም ሰው ግን አሳልፈው አልሰጡም። በዚህ ረገድ ስጋቱ አልነበረኝም። እኔ የምሄደው ከእሱ ጋር በተያያዘ አይደለም።

“ወደ አገሬ መሄድ ባልፈልግ እዚህ አገር ሆኜ ምንም እንደማይደርስብኝ አውቃለሁ። የእኔ ጉዳይ እሱ አይደለም። በውሸት ክስ ሽብርተኛ ተብዬ ተከስሼ ውጭ አገር ስደተኛ ሆኜ መቅረት አልፈልግም። አላማዬ አይደለም። በልጅነቴ የገባሁት ቃልኪዳን ነው።”

ወደ ኢትዮጵያ የሚመለሱት ከሕዝቡ ጋር ያለውን ችግር ለመካፈል እንደሆነም አቋማቸውን ለቢቢሲ ገልጸዋል።

“ከሕዝቡ ጋር፣ አገሪቱ ውስጥ ያለውን መከራ እና ችግር ሁሉ መካፈል ነው የምፈልገው። እስከ ሕይወቴ ፍጻሜ ድረስ እዚያው ሆኜ መታገል ነው የምፈልገው። ለዚያ ደግሞ ዋጋ ለመክፈል ለራሴ የገባሁት ቃል ስለሆነ ይሄን ለማክበር ነው የምሄደው እንጂ ከተጠያቂነት አንጻር ፖሊስ ይይዘኛል ብዬ ከመስጋት አይደለም።”

አቶ ልደቱ አያሌው ከሁለት ዓመት በፊት ሕገ ወጥ የጦር መሣሪያ መያዝ እና አመጽ ማነሳሳትን ጨምሮ የተለያዩ ክሶች ከቀርበውባቸው ከአዲስ አበባ ውጪ ቢሾፍቱ ውስጥ ታስረው መቆየታቸው ይታወሳል።

እዚያም ሳሉ የጤና ችግራቸው ተባብሶ ለሕይወታቸው አስጊ ደረጃ ላይ መድረሱ ተነግሮ የነበረ ሲሆን፣ ጉዳያቸውን ሲከታተል የነበረው ፍርድ ቤት በዋስ ከእስር እንዲወጡ ቢፈቅድም ለተወሰነ ጊዜ በእስር ላይ ቆይተው ነበር።

ታዋቂው ተቃዋሚ ፖለቲከኛ አቶ ልደቱ ከእስር ከወጡ በኋላ የሕክምና ክትትል ለማድረግ ወደ ውጪ ለመጓዝ በሞከሩበት ጊዜ ተከልክለው መጉላላታቸውን በወቅቱ ለቢቢሲ ተናግረው ነበር።

በተደጋጋሚ ከአገር እንዳይወጡ መከልከላቸውን በመግለጽም ድርጊቱ በሕክምና እጦት “ሕይወቴን እንዳጣ የሚደረግ ሙከራ ነው” ሲሉ ተናግረው ነበር።

በመጨረሻም ከአገር መውጣት ችለው በአሜሪካን አገር ሕክምናቸውን በመከታተል ላይ ሳሉ ነው ከሌሎች ግለሰቦች ጋር በሽብር ድርጊት ተጠርጥረው እንደሚፈለጉ መንግሥት ይፋ ያደረገው።