አሁን ያለችው ኢትዮጵያ እንድትመጣ ከነበረ ትግሉ ህወሀት በስልጣን ቢቆይ ከዚህ በላይ ምን ይመጣብን ይሆን?

አበይት ጉዳይነፃ ሃሳብ

4/8/20232 min read

አሁን ያለችው ኢትዮጵያ እንድትመጣ ከነበረ ትግሉ ህወሀት በስልጣን ቢቆይ ከዚህ በላይ ምን ይመጣብን ይሆን?

መሳይ መኮንን

የጄ/ል አበባውን ቃለመጠይቅ አዳመጥኩት። በመርህ ደረጃ ያነሱትን እሳቸው ህገመንግስቱ በሚፈቅደው መሰረት ያሉትን የክልል ልዩ ሃይሎችን የተመለከተው መከራከሪያቸው ስንለው ስንጮኸው የነበረው ጉዳይ ነው። ጥያቄው አሁን ለምን? ይሄን ሁሉ ዘመን ተቀምጣችሁ፡ ህወሀት ሰሜን ዕዝን እስኪፈጅበት ጠብቃችሁ፡ በመሀል በመከላከያ ሰራዊት ቁመት ልክ የኦሮሚያ ብልጽግና ልዩ ሃይል ሲያደራጅ ዝም ብላችሁ አልፋችሁ፡ ዘንድሮ ያውም ብርቱ የደህንነት ስጋት በተደቀነበት ጊዜ ላይ ድንገት መጥታችሁ ''ልዩ ሃይል ይፍረስ'' ምን ማለት ነው? ይሄን ጉዳይ ጄ/ል አበባው ሊናገሩት አልቻሉም። ጋዜጠኛዋም አልጠየቀቻቸውም።

ጄ/ል አበባው አንድ ያልተረዱት ነገር የመታመን ቀውስ የገጠመው ስርዓት የትኛውንም የተቀደሰ ሀሳብ ይዞ ቢመጣ ህዝቡ በበጎ ሊመለከተው እንደማይችል ነው። እንደውሸታሙ የበጎች እረኛ በውሸት ቀበሮ መጣ እያለ ጎረቤቶቹን ሲያስደንግጥ ከረመና የእውነት ቀበሮ ሲመጣ የሚያድነው አጥቶ በጎቹን እንዳስበላ ሁሉ ይሄን በስልጣን ላይ ያለው መንግስት ሲዋሽና ሲቀጥፍ የከረመ መሆኑ ከእንግዲህ እውነት እንኳን ቢናገር የሚያምነው እንደሌለ ለጄ/ል አበባው እንዴት እናስረዳቸው? ብልጽግና ፓርቲ የሚባል የውሸት ቁናን ወክሎ ወይም ለዚህ ስርዓት አገልጋይ ሆኖ ምስክርነትን እንደመስጠት አሳፋሪ ተግባር የለም። ጄ/ል አበባው ስለሰላም አብዝተው ይናገራሉ። ቃለመጠይቁን ከሰጡበት መከላከያ ሚኒስቴር አጥር ብዙም ሳይርቅ ኮልፌ አከባቢ ትርምስ አለ። እዚያው አዲስ አበባ ኢትዮጵያውያን የቤት እቃቸውን ተሸክመው በረጅም ሰልፍ ሀገር እየለቀቁ መዳረሻ በሌለው ጉዞ ይታያሉ። ከጫንጮ እስከ ደራ ስርዓት አልበኝነት ነግሶ አፍኖ ሚሊዮን ብሮችን መጠየቅ ፍቃድ የማይወጣለት ስራ ከሆነ ሰንብቷል። ብልጽግና/ሸኔ አዲስ አበባን ዙሪያዋን እንደታቦት ይዞራት ከጀመረ ከራርሟል። ሌላም ሌላም። ጄ/ል አበባው ስለየትኛው ሰላም እንዲህ ጥርሳቸውን ገጥመው፡ ረገጥ አድርገው እንደሚነግሩን ሊገባኝ አልቻለም።

የኢትዮጵያ አሁናዊ ሁኔታ እንዲህ ደረትን ገልብጦ የሚያስነግር አይደለም። በፍጹም። እውነት ለመናገር አንዳንዴ አሁን ያለንበትን አስፈሪ ሁኔታ እመረምርና ብልጽግና ኢትዮጵያን ሲረከብ ወደነበረችበት ቦታዋ ቢመልስልን ትልቅ ውለታ ነው እስከማለት ደርሼአለሁ። የኢትዮጵያ ዋና ችግር ራሱ በስልጣን ላይ ያለው አገዛዝ መሆኑን ጄ/ሉ አያውቁትም ማለት አይቻልም። በዚህም ቢባል በዚያ የኢትዮጵያ የሰላም እጦት መነሻው ከኦሮሚያ ብልጽግና መራሹ መንግስት የሚመነጩ አደገኛ ትርክቶችና እርምጃዎች ናቸው። እዚህም እዚያም የሚታዩት ቀውሶች በስርዓቱ አቅም ማነስና የራዕይ እጦት እንዲሁም ሌብነት ምክንያት የተከሰቱ ናቸው። የሌሎች ቡድኖች አስተዋጽኦ ቢኖረውም ሁሉን ነገር ካልጠቀለልኩ፡ ካላግበሰበስኩ የሚል ለከት ያጣ ስግብግብነት ውስጥ ዘው ብሎ በገባው የኦሮሚያ ብልጽግና የተነሳ የተዘፈቅንበት አረንቋ መሆኑን በግልጽ መነጋገር ያስፈልጋል። ጄ/ል አበባውን ፈልጌ ያጣኋቸውም እዚህ ጉዳይ ላይ ነው። እስቲ ቀና ብለው አዲስ አበባ ዙሪያዋን ይመልከቱ። እውነት እንዲህ በፉከራና በልበ ሙሉነት የሚያናግር ቁመና ላይ ደርሰናል ማለት ይቻላልን?

ጄ/ል አበባው ስልጣን የሚገኘው በምርጫ ብቻ እንደሆነ ነግረውናል። አንድ የዘነጉት ነገር ግን ቃሉን ያላከበረ፡ ምረጡኝ ብሎ ድምጽ ላገኘበት ቃልኪዳን ያልተገዛ ስርዓትም እኮ በህዝብ ተቃውሞ ሊወገድ ይችላል። ይህ ሀጢያት አይደለም። ወንጀልም አይደለም። ቃሉን ያላከበረውና የህዝብን ፍላጎት ደፍጥጦ እየዘረፈ ያለውን ስርዓት ከጊዜው በፊት እንዲወርድ የሚያደርግ የህዝብ ንቅናቄን እንደሀጢያትና ወንጀል መቁጠር ለጄ/ል አበባው ለህገመንግስቱ ታማኝነትን የማረጋገጥ ያህል መወሰዱ ያሳዝናል። ህገመንግስቱን እኮ የጣሱት አለቆችዎ ናቸው። ህዝብ እያፈናቀሉ፡ አይን ባጣ፡ ሀገርን በአጥንቷ ባስቀረ ዘረፋ ውስጥ የተዘፈቁት እኮ እርስዎ የሚጠብቋቸው የፖለቲካ አመራሮች ናቸው?! ህገመንግስቱን እነሱ ሲያፈራርሱት ተፈቅዶላቸው ነው ማለት ነውን? ጄ/ል አበባው ጌታ ለመቀየር ዋጋ አልከፈሉም። ህወሀቶች በዚያ ልክ አዋርደው በጡረታ ስም ሲያሰናብቷቸው ለእውነትና ለእምነታቸውና ለሀቅ በመቆማቸው የከፈሉት ዋጋ በመሆኑ ምንጊዜም ከህሊና እዳ ነጻነት ይሰማቸዋል ብዬ አምናለሁ። ታዲያ አሁንስ? ጌታ ተቀየረ እንጂ ኢትዮጵያ እኮ ያው ማጥ ውስጥ ናት። እንደውም ከምንጊዜውም የከፋ ማጥ።

ብልጽግና ፓርቲ የኢትዮጵያ እዳ ሆኖ ታሪክ ላይ ሰፍሯል። ኣውነት ለመናገር ያቺን ከአምስት አመት በፊት የነበረችዋን ኢትዮጵያ ብትመለስልን ይበጃል የሚል ድምዳሜ ላይ እየደረስኩ ነው። አሁን ያለችው ኢትዮጵያ እንድትመጣ ከነበረ ትግሉ ህወሀት በስልጣን ቢቆይ ከዚህ በላይ ምን ይመጣብን ይሆን? ለጄ/ል አበባው አግኝቼ ብጠይቃቸው ደስ የሚለኝ ጥያቄ።

Related Stories