ከአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ ( አብን) ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ በወቅታዊ ጉዳይ ላይ የተሰጠ የአቋም መግለጫ፡

HR REPORTSየዜና ትንታኔ

4/5/20232 min read

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ከመጋቢት 24-26 ቀን 2015 ዓ.ም ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ በተለያዩ ወቅታዊ እና ሃገራዊ ጉዳዮች ላይ ውይይት በማድረግ ውሳኔዎችን አሳልፏል፡፡ ድርጅታችን አብን ከተወያየባቸው አንኳር ጉዳዮች ውስጥ አንዱ የገዥው ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የክልል ልዩ ኃይሎችን በሚመለከት ያሳለፈው ውሳኔ አንዱ ሲሆን ፣ የገዥው ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ ውሳኔ በሁሉም ክልሎች ልዩ ኃይልችች ላይ በእኩል ደረጃ ተፈጻሚ የማይሆን እና የውሳኔው ዋነኛ የትኩረት አቅጣጫ የአማራ ልዩ ኃይልን ትጥቅ ማስፈታት መሆኑን አብን ገምግሟል፡፡ አብን በመርህ ደረጃ ከበቂ የሽግግር ጊዜ በኋላ የክልል ልዩ ኃይሎችን አደረጃጀት ማስተካከል እንደሚገባ የሚያምን ቢሆንም ጉዳዩን ከሕጋዊነት ፣ ከወቅታዊ እና ሃገራዊ ነባራዊ ሁኔታዎች አንጻር በመመርመር ገዥው ፓርቲ ያሳለፈው ውሳኔ ወቅቱን ያልጠበቀ ፣ ነባራዊ ሁኔታዎችን ግምት ውስጥ ያላስገባ እና ለጥቃት ተጋላጭ የሆኑ አካባቢዎችን እና የኅብረተሰብ ክፍሎችን ተገማች እና ቀጥተኛ ለሆነ ጥቃት እና አደጋ የሚዳርግ ውሳኔ ሆኖ አግኝቶታል፡፡

አብን በሃገራችን ኢትዮጵያ እና በሃገረ-መንግስታችን ላይ የተቃጣው ሥርአታዊ እና መዋቅራዊ ጥቃት እንዲከሽፍ እና የሃገራችን ሕዝብ መልከ ብዙ ብዝሃነቶችን እውቅና የሚሰጥ እና የሚያከብር ፣ ለግለሰቦች መሰረታዊ መብቶች መከበር እና መጠበቅ ዋስትና የሚሰጥ ፣ የሃገር ሉዓላዊነትን ፣ ሀገራዊ አንድነትን እና የግዛት አንደነትን የሚያረጋግጥ እውነተኛ ፌዴራላዊ ሥርአት እንዲዋቀር እና በስራ ላይ ያለው ሃሳዊ “ፌዴራሊዝም” በሃቀኛ ፌዴራላዊ ስርዓት እንዲተካ ትግል የሚያደርግ ድርጅት ነው፡፡ አብን ለበርካታ አስርት ዓመታት ሲዳከም የቆየው የማዕከላዊ መንግስት ስልጣን በእውነተኛ ፌዴራላዊ የመንግስት ስርዓት አወቃቅር አግባብ እንዲጠናከር እና መንግስት የመላ ኢትዮጵያውያን መብት እና ደኅንነት የማክበር ፣ የማስከበር እና የመጠበቅ ኃላፊነቱን እንዲወጣ የራሱን ሚና ለመወጣት ቁርጠኛ አቋም ያለው ድርጅት ነው፡፡

በየክልሉ የተደራጁ ልዩ ኃይሎች አፈጣጠር እና አደረጃጀት የራሱ የሆነ ችግር የነበረበት ቢሆንም አሁን ባለው ተጨባጭ እና ነባራዊ ሁኔታዎች የአማራ ክልል ልዩ ኃይልን በድንገት እና ያለበቂ የጸጥታ ዋስትና ማፍረስ በተለይም የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር አመራሮችና ሚዲያዎች ከሰላም ስምምነቱም በኋላ በአማራ ሕዝብ ላይ የተጠናከረ የጥላቻ ቅስቀሳ እያካሄዱ ባለበት እና አጎራባች የአማራ አካባቢዎችን በተለይም ወልቃይትንና ራያን በኃይል ለማስመለስ እየተዘጋጁና እንደሚያስመልሱም ባደባባይ እየተናገሩ ባለበት ሁኔታ ለጥቃት ተጋላጭ የሆኑ የአማራ ክልል አካባቢዎችን ተገማች እና ቀጥተኛ ለሆነ ጥቃት ተጋላጭ የሚያደርግ በመሆኑ አብን አጥብቆ የሚቃወመው ውሳኔ ነው፡፡ የአማራ ሕዝብ ራሱን የትግራይ ሕዝብ ነጻ አውጭ ግንባር (ትሕነግ) እያለ የሚጠራው ቡድን የሚመራው ታጣቂ የከፈተበትን መጠነ ሰፊ የወረራ ጦርነት የመከተው ትጥቅና ስንቅ በራሱ እያደራጀ ፣ ጎን ለጎን የሃገር መከላከያ ሰራዊታችንን እና የክልሉን ልዩ ኃይል እየደገፈና አብሮ እየተዋጋ እና መስዋእትነት በመክፈል ነበር። ሕዝባችን ቀድሞ እዳይደራጅ እና እንዳይዘጋጅ የተደረገበት የፖለቲካ ሴራ ሳይረሳ ፣ አሁንም ስጋቱ በቀጠለበት ሁኔታ የአማራ ልዩ ኃይልን ትጥቅ ለማስፈታት መሞከር የከፋ ስህተት ነው።

በተለይም በፌዴራሉ መንግስት እና በትግራይ ሕዝብ ነጻ አውጭ ግንባር (ትሕነግ) መካከል በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ የተደረገው የሰላም ስምምነት ባግባቡ ተግባራዊ አልተደረገም ፤ አጠቃላይ ሂደቱም ግልፅነትና ተአማኒነት የጎደለው ሁኗል። የትግራይ ህዝብ ነጻ አውጭ ግንባር (ትሕነግ) ያስታጠቀው ኃይል ትጥቁን አልፈታም ፣ እንዲያውም ተጨማሪ ኃይል እያሰለጠነ እና እያደራጀ ይገኛል። በፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት መሰረት የሃገር መከላከያ ሠራዊት የትግራይ ክልል ጸጥታ አልተረከበም ፤ መንግስት የፀጥታ ማረጋገጥ ስራውን ባግባቡ ስላልተወጣ የደኅንነት ማረጋገጫ እና ዋስትና መስጠት የሚችልበት ሁኔታ አልፈጠረም። ከዛ ሁሉ ጦርነት፣ ምስቅልቅልና ውድመት በኋላም የብሔራዊ ደኅንነት ዋስትና እና መተማመን አልተፈጠረም።

የብልፅግና ፖርቲ ያስተላለፈው ውሳኔ በዋናነት ከፈረሱ ጋሪውን ያስቀደመ በመሆኑ ተቀባይነት የለውም። በመሰረቱ ይህ ጉዳይ በብሔራዊ ምክክር ወቅት አብሮ ሊታይ የሚገባው እንጂ በአንድ ፖርቲ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ሊወሰን የሚችል ጉዳይ አይደለም። በተለይ የሰላም ስምምነቱ አንኳር ጉዳዮች ባልተተገበሩበት እና የአማራ ሕዝብ በከፍተኛ ስጋት ውስጥ እያለ የክልሉን ልዩ ኃይል ለማፍረስ መሞከር ሕዝባችን ያለበትን የኅልውና አደጋ የማስቀጠል ጥረት አካል ተደርጎ የሚታይ ነው። በተጨማሪ የአማራ ክልል የተለያዩ የሽብር ቡድኖች የደኅንነት ስጋት የደቀኑበት ክልል ስለሆነ በዚህ ወቅት የጸጥታ ኃይሉን ይበልጥ ማጠናከር እንጂ ማፍረስና ትጥቅ ማስፈታት ህዝባችንን ለጥቃት የሚያጋልጥ ውሳኔ ነው።

ስለሆነም፥

፩. የፕሪቶሪያውን የሰላም ስምምነት ወደ ጎን በተገፋበትና ራሱን የትግራይ ሕዝብ ነጻ አውጭ ግንባር (ትሕነግ) እያለ የሚጠራው ኃይል ትጥቅ ባልፈታበት ፣ ይልቁንም ለሌላ ዙር ጦርነት በግልጽ ዝግጅት እያደረገ ባለበት እና ከፍተኛ ስጋት የተደቀነበት የአማራ ክልል ልዩ ኃይል ትጥቅ ይፍታ ማለት ሕዝባችንን ያለ ተከላካይ ለዳግም ወረራ እና ጥቃት የሚዳርግ ውሳኔ በመሆኑ ውሳኔውን የምንቃወመው ነው፡፡

፪. የአማራን ክልል አንጻራዊ ሰላም እና መረጋጋት እያገኝ ያለው የአማራ ልዩ ኃይል በአሸባሪዎች እና በሰርጎገብ ኃይሎች ላይ ያለው የሰላም እና የኃይል የበላይነት ነው። በአሁኑ ሰዓት የአማራ ልዩ ኃይልን ትጥቅ ማስፈታት ክልሉን ላልተጠበቀ ስርዓት- አልበኝነት እና ለሽብርተኛ ኃይሎች መፈንጫነት የሚያመቻች በመሆኑ የገዥው ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ የወሰነው ውሳኔ ውድቅ ሊደረግ የሚገባው ነው።

፫. የክልል ልዩ ኃይሎችን አደረጃጀት ጨምሮ አጠቃላይ የፌዴሬሽኑ አወቃቀር በሚመለከት በቀጣይ ሊደረግ በታሰበው በብሔራዊ ምክክር መድረክ ስምምነት ሊደረስበት የሚገባ ዋና የውይይት አጀንዳ በመሆኑ የገዥው ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ በሌለው ስልጣን ያሳላፈው ውሳኔ ውድቅ ሊደረግ የሚገባው ነው። በመሆኑም የብልፅግና ስራ አስፈጻሚ ይሄን ጉዳይ በጥድፊያ ለመፈፀም የሚያደርገው ሙከራ ከፍተኛ አደጋ የሚያስከትል መሆኑን እያሳሰብን ፤ በተለይም የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት እንዲህ ያለውን ትጥቅ አስፈቺ ውሳኔ እንዳይተገበር የማድረግ ታሪካዊ ኃላፊነት ያለበት መሆኑን ፓርቲያችን የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ያሳስባል፡፡

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ(አብን)

አዲስ አበባ፣ ሸዋ፣ ኢትዮጵያ

መጋቢት 26 ቀን 2015 ዓ.ም

Related Stories