በሃገራችን ህልውና እና የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ላይ ያንዣበቡ አደጋዎች እና የመውጫ መንገዶች - ክፍል 1

ነፃ ሃሳብ

አንዳርጋቸው ጽጌ

3/26/20232 min read

ይህን ጽሁፍ የሚያነብ ሰው ጽሁፉ የተጻፈበትን በዛን ወቅት በኢትዮጵያ የነበረውን ሁኔታ ግምት ውስጥ አስገብቶ ሊያነበው ይገባል። ከዛ በኋላ የተቀያየሩ ብዙ ጉዳዮች አሉ። በተለይ ከኢህአዴግ ውስጥ ወጥቷል ብለን ስናስበው ከነበረው “የለውጥ ሃይል” ጋር የተሳሰስሩ፤

አንዳርጋቸው ጽጌ

በሃገራችን ህልውና እና የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ላይ ያንዣበቡ አደጋዎች እና የመውጫ መንገዶች - ክፍል 1

1. መግቢያ

ዛሬ ሃገራችን ኢትዮጵያና ዜጎቿ እጅግ ፈታኝ በሆኑ ሁለንተናዊ ቀውሶች ውስጥ ይገኛሉ። የቀውሶቹ ምክንያቶች ብዙ ናቸው፤ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና የሞራል ተብለው ሊዘረዘሩ ይችላሉ። ከእነዚህ ቀውሶች በሙሉ የከፋው፣ ለተቀሩት ቀውሶች መባባስ ምክንያት የሆነው፣ የመፍትሄውን መንገድም ውስብስብ የሚያደርገው ግን የፖለቲካችን ቀውስ ነው። ሃገራችን ከዚህ የፖለቲካ ቀውስ ነጻ መሆን እስካልቻልች ድረስ ለሌሎች ቀውሶች መፍትሄ ማግኘት አትችልም።

የፖለቲካችን ቀውስ በቀጥታ በሰላምና መረጋጋት እጦት፣ በመልካም አስተዳደር መጥፋት፣ በህግ የበላይነት አለመኖር፣ በፍትህ መደፍጠጥ፣ በነጻነት ረሃብ፣ የህይወት የንብረትና የስራ ዋስትና ማጣት በመሳሰሉት ችግሮች ራሱን ይገልጻል። እነዚህን ችግርች መገለጫዎቹ ያደረገውን የፖለቲካ ችግር በተወሰነ ደረጃና ባስቸኳይ መቅረፍ ካልተቻለ የኢኮኖሚና ማህበራዊ ቀውሱ እየከፋ፣ የሞራልና የባህል ዝቅጠቱ እየጨመረ መሄዱ የማይቀር ነው። ይህ ሂደት ደግሞ እንደገና ተመልሶ፣ የፖለቲካ ቀውሱ ይበልጥኑ እንዲጦዝ የራሱን አስተዋጸኦ ያደርጋል። መጨረሻው ደግሞ ከቁጥጥር ውጭ የሚወጣ የቀውስ አዙሪት ውስጥ መውደቅ ይመጣል። ውሎ አድሮም ከዚህ የፖለቲካ ቀውስ መውጫ አድርገን የወሰድነው ሃገራዊ የዴሞክራሲያዊ የፖለቲካ ስርአት ግንባታ በተግባር ላይ መዋል የማይችልበት ሁኔታ ይፈጠራል። ይህን ክሽፈት ተከትሎ ዴሞክራሲ ብቻ ሳይሆን የሃገር ህልውና ከፍተኛ አደጋ ላይ ይወድቃል።

ዛሬ በሃገራችን የሚታየው ተጨባጭ ሁኔታ ከዚህ በላይ የጠቀስኩትን አስከፊ እውነታ እውን ለማድረግ የሚንደረደር ሆኗል። የሚገርመውና የሚደንቀው ነገር ይህን እያስፈራ የመጣ እውነታ ከምር ተገንዝቦ እስትራቴጂካዊ መፍትሄ እያሰበና ለመተግበር እየሞከረ ያለ የፖለቲካ ሃይል በሃገሪቱ አለመገኘቱ ነው። የፖለቲካ ሃይል ስል ገዥውን ፓርቲና ሁሉንም ተቃዋሚ ነኝ ባይ እኛንም አግ7 ድርጅት ይመለከታል።

ከፖለቲካ ሃይሉ ውጭም ፖለቲካን ማህበረሰብን፣ ሃገርንና ሌላውንም ሃገራዊና ህዝባዊ ጉዳይ አጠናለሁ፣ እመረምራለሁ፣ የሚለው በአካዳሚያውና በተለያዩ ብዙ ነዋይ በሚፈስባቸው የምርምርና የጥናት ተቋማት ውስጥ ተቀጥሮ የሚሰራው የሃገሪቱ ልሂቅም ዝምታን መርጧል። የየራሱን ህልም ወይም ቀቢጸ ተስፋ የሚያሳድደው በዝቷል። በየጊዜው የሚቀጣጠለውን እሳት ለማጥፋት መንደፋደፉን እንደ ዘላቂ መፍትሄ የማየቱ አደገኛ አካሄድ በሰፊው ተይዟል። በወጉ ያልታሰበባቸውን ግልብ አሰተያየቶች፣ እውነተኛ ነጻነትንና ገለልተኛ ጋዜጠኛነትን በቅጡ የተረዱ በማይመስሉ የሚዲያ ተቋማት አማካይነት በሰፊው ይነዛል። በቅጡ ያልታሰበባቸው ሀገርና ህዝብን የሚጎዱ ድርጊቶች በሁሉም አካላት ይፈጸማሉ። “እነ እገሌ ይሰሩታል” በሚል የተለመደ የጠባቂነት ባህል ታስሮ ከላይ የመፍትሄ መና አንጋጦ የሚጠብቀው ይበዛል። ወቅቱ ረጋ ብሎ አይንን ወደ ትልቁ ስእል መልሶ ስትራተጂያዊ የፖለቲካ አኪያሄድ የሚጠይቅ ሆኖ ሳለ ሁሉም በታክቲካዊ ስሌት ተጠምዷል። ቀኖች ይነጋሉ ይመሻሉ። ቀውሱ ይጦዛል።

ዜጎች በዘር ተቧድነው አሸናፊና ተሸናፊ ወደማይኖርበት፣ ለሺ አመት መብረድ ወደ ማይችል አንዱ በሌላው ላይ ወደተነሳበት እልቂት እያዘገሙ ነው። ዜጎች በየቀያቸው በተደራጁ ከልካይ በሌላቸው የማፊያ ቡድኖች እየተዘረፉ፣ እየተዋረዱ፣ እየተሸማቀቁ እየኖሩ ነው። የሚያስደነግጥ ስርአት አልበኛነትና ህገ-ወጥነት በሁሉም አካባቢ በመላው ሃገሪቱ እየተስፋፋ ነው። ይህ ሁኔታ ሃገሪቱን የሚገልጽ አይደለም ለሚሉት መገንዝብ የሚገባቸው በሁሉም ዘርፎች ሃገሪቱ የምትገኝበት ሁኔታ ከላይ የተገለጸውን ሁኔታ አበረታች እንጂ አዳካሚ እንዳልሆነ እስከተስማሙ ድረስ በስጋት፣ በዘረፋ፣ በመፈናቀልና በግድያ ስታትስቲክ ዙሪያ መከራከሩ ትርጉም አይኖረውም። እውነት እንነጋገር ከተባለ የመረጃ ችግር የለም።

ወደ ታችኛዎቹ መንግስታዊ አስተዳደሮች ሲወረድ የመንግስት መዋቅር ነገረ-ስራ አደናጋሪ ብቻ ሳይሆን እጅግ አሳሳቢም እየሆነ ነው፡፡ የታችኛው እና መካከለኛው የመንግስት መዋቅር አመራሮች እጅግ አደገኛ የሆነ የዘረኝነት ዝንባሌ ይታይባቸዋል፡፡ በሚያስተዳድሩት አካባቢ የተሾሙት ዘራቸው ብቻ ተቆጥሮ በመሆኑ በአካባቢው ለሚነሳው የዘር ግጭት ምንግዴ ከመሆን እስከ ማባባስ እና ማቀናበር የሚደርሱት አብዛኛዎቹ ናቸው። በውጤቱም ሃገር እንደዋዛ (by default ) ለማንም ወደማይበጅ ዜጎቿ ሁሉ በዘረኝነት ቢላዋ የሚመታተሩባት ሲኦል እንዳትሆን ያሰጋል፡፡ የዚህ መንገድ ማክተሚያው ደግሞ ሃገር ከመኖር ወደ አለመኖር ተቀይራ ህልውናዋ እንዲያከትም አድርጎ ማረፍ ብቻ ነው፡፡

ይህ ፅሁፍ እንዲፃፍ ያደረገው ምክንያትም ይኸው በሃገር ላይ ያንዣበበው አስፈሪ አደጋ ስጋና ደም ለብሶ መተኪያ የሌለንን ሃገራችንን እንዳያሳጣን ቀድሞ በችግሩ እና በመፍትሄው ላይ ለመነጋገር የሚያስችል ሃሳብ ለማጫር ነው፡፡ የጽሁፉ ዋነኛ አላማዎች ሶስት ናቸው። የመጀመሪያው ሃገሪቱን እየናጧት ያሉትን መሰረታዊ የፖለቲካ ቀውሶች ለይቶ ማሰቀመጥ ነው። ሁለተኛው ለነዚህ ችግሮች መንስኤ የሆኑትን ምክንያቶች መደርደር ነው። ሶስተኛው ከገባንበት ቀውስ መውጫ መፍትሄ የሚሆኑትን ሃሳቦች ማቅረብ ነው።

2. ዋና ዋናዎቹ ቀውሶች

2.1. በዘር ላይ የተመሰረተ ግጭትና ውጥረት

በሁሉም የሃገሪቱ ክፍሎች ውጥረት ነግሷል። በተጨባጭ እየተከስተ ያለውን አሳዛኝ የህዝብ ስቃይ በሃዘን መመለከት ከጀመርን ቆይተናል። ዜጎች በዘር ተለይተው እንዲፈናቀሉ እየተደረገ ነው። በዘር ተለይተው እየተገደሉ ነው። ከዚህ መፈናቀልና መገደል ደግሞ እራሱን ማዳን የቻለ ዘር የለም። ዘረኛነትን በሃገራችን ሆን ብለው የዘሩት ውያኔዎች ሳይቀሩ የዘሩትን ማጨድ ጀመረዋል። ይህ አሳዝኝ ትእይንት (ትራጀዲ) የሃገሪቱ የቀን ተቀን ገጽታ ከሆነ ውሎ አድሯል።

በዘር ላይ የተመሰረተው ክልላዊ መሰተዳደር የክልሉ የዘር ባለቤቶች ናቸው ከሚባሉት በስተቀር ቀድሞውኑ ሌሎችን ዝርያዎች አግላይ እንደነበር ይታወቃል። ከተሞች የከተማው ኗሪዎች በሙሉ መሆናቸው ቀርቶ የተወሰኑ ዘሮች ከተሞች እንደሆኑ ተደርጎ በፐርሰንቴጅ እያሰሉ % የኦሮሞ % በመቶ የሱማሌ በሚል ስሌት እንደ ድሬዳዋና እንደ ሃረር በመሳሰሉ ከተሞች የተዘረጋ አግላይ የዘር አስተዳደራዊ መዋቅር አንስቶ፣ በአንድ ከተማ ውስጥ ከሌሎች የከተማው ኗሪዎች አንድ ዘር ለይቶ የተለየ ጥቅም ለመስጠት እንደ አዲስ አበባ በመሰሉ ከተሞች ውስጥ የሚሰራው ስራ፣ ክልሎች፣ ዞኖች በውስጣቸው የተለያዩ ብሄረሰቦች/ዘሮች እንዳሉ እየታወቀ ክልሉንና ዞኑን የአንድ ዘር ክልል በማድርግ ሌሎችን የክልሉን ዘሮች በሙሉ ከፖለቲካ

ከማህበራዊና የኢኮኖሚ ተሳታፊነት ያገለለ ዘረኛ አስተዳደር ወያኔ ባለፉት 27 አመታት ዘርግቶ ስር እንዲሰድ እንዳደረገው ይታወቃል።

ወያኔ ይህን ለምን እንዳደረገ መግለጽ የዚህ ጽሁፍ አላማ አይደለም። ቢሆንም ይህን በማድረግ ወያኔ በተከፋፋለ ህዝብ ላይ ፍጹማዊ የሆነ የስልጣንና የጥቅም ባለቤት እንዲሆን ያስቻለው መሆኑ ከሃቅም በላይ ሃቅ ነው። ይህ ከአፍንጫ እልፍ ያላለ እይታ ከአመታት በፊት ለራሱ ለወያኔ እንደጠቆምኩት፣ የዘር ፖለቲካው በስተመጨረሻ እነሱንም ከመብላት አልተመለሰም። ዋናዎቹን ዘረኞች ባይበላም ዳፋው ለደሃው የትግራይ ተወላጅ መትረፉ አልቀረም።

ሰውን በሰውነቱ የማያየው ዘርን መሰረቱ ያደረገ የፖለቲካና አስተዳደራዊ አደረጃጃት ሰዎች የአንድ ሃገር ዜጎች ሆነው ሳለ በዘራቸውና በመኖሪያ ክልላቸው የተነሳ በአስር ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያንን መብት አልባ፣ ሃገር አልባ አድርጎ አሰቀምጧቸው ነበር። እነዚህ ኢትዮጵያውያን ከተለያዩ ዘሮች የተፈጠሩ፣ በደማቸው ወስጥ የሚፈሰው የተለያዩ ዘሮች ደም አንዱን ዘር ለመምረጥ፣ ራሳቸውን በዘር መነጽር ማየት የማይችሉ ሌላውንም ወገናቸውን በሰውነቱ እንጂ በዘሩ ማየት የሚከብዳቸው ዜጎች ናቸው። ሌሎቹ በዘር በተደራጁ ክልሎች ወስጥ ደማቸው ሲመረመር ክልሉ ከተዋቀረበት ዘር ጋር በደም የማይተሳሰሩ በዚህም የተነሳ በየክልሎቹ መብት አልባ የተደረጉ ናቸው። አሁን ባለንበት ወቅት ችግሩ ከመገለልና መብት አልባ ከመሆን አልፎ እነዚህ ዜጎች ሰብአዊና ፖለቲካዊ መብታቸው ተገፎም እንኳን ተራ የቀን ተቀን ህይወታቸውን ሳይቀር ተረጋግተው በሁለተኛ የክልል ኗሪነት ደረጃ መኖር የማይችሉበት ሁኔታ ውስጥ ወድቀዋል። እነዚህ ዜጎች ቤት ንብረታቸውን እየሸጡ፣ ስራቸውን እየለቀቁ፣ ትንሽ ሰላምና እርጋታ ይገኝበታል ብለው ወደሚያስቡት አዲስ አበባ ከተማ ቀሰ በቀስ እየፈለሱ ነው። አዲስ አባባም እንደሌሎች ከተሞች ሰላምና እርጋታዋ በሃገሪቱ በተዘረጋው ዘረኛ አስተዳደር እንደማይናጋ ግን ዋስትና ያላት እንዳልሆነ እየተመለከትን ነው።

በድሬደዋ፣ በሃረር፣ በበርካታ የኦሮሚያ ከተሞች፣ በበርካታ የአማራና የደቡብ ህዝቦች ክልል ከተሞች፣ በቤንሻንጉል፣ ዘርን ለይቶ ለሚመጣ መዘረፍ፣ መፈናቀልና መገደል ዜጎች ራሳቸውን አዘጋጅተው እጣቸውን በስጋት ተውጠው በመጠበቅ ላይ ናቸው። በዘር ላይ የተመሰረተው አስተዳደራዊ ስርአት የወረደበት አዘቅት አንድ አይንት ቋንቋ እምነትና ባህል የሚጋሩ ማህበረሰቦች ጥንታዊ የዝርያቸውን ምንጭ እየጎረጎሩ አንዱ የተለየ መሆኑን በማስረገጥ በልዩነት ላይ የተመሰረተ ግጭት ውሰጥ እንዲገቡ እያደረገ ነው። የአማራና የቅማንት ግጭት ሌላ ትርጉም ሊሰጠው የሚችል አይደለም። ይህን ጽሁፍ እየጻፍኩ ባለሁበት ሰአት ከጎንደር የሚመጣው መረጃ ብብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ ቅማንቶች የዘር ማጽዳት ስራ ከፊል ህጋዊና ህገ ወጥ በሆኑ ሃይሎች እየተፈጸመባቸው እንዳለ በማመን፤ ወይንም ይህን ስሜት በመፍጠር ግጭቱን ለማጦዝ በሚፈልጉ ኃይሎች በመገፋፋት ይህን ፍርሀት ለመቋቋም ለግጭት ራሳቸውን እያዘጋጁ እንደሆነ ነው። ግጭቱ በተወሰነ ደረጃ ጀምሯል። ቆየት ብሎም አማራና አገው በሚል ልዩነት ሽኩቻ ቢቀሰቀስ አያስገርምም።

በየክልሉ በቋንቋና በባህል የማይመሳሰሉ የተለያዩ በአንድ ተጨፍልቀው በአንድ ዘር በሚጠራ ክልልና ዞን ወስጥ የሚኖሩ ማህበረሰቦች ውለው አድረው ለምን በዚህ ወይም በዚያ ዘር ስም በሚጠራ ክልል ወስጥ እንኖራለን ማለታቸው እንደማይቀር የታወቀ ነበር። አሁን እየሆነ ያለው ይህ ነው። ትንሽም እንሁን ትልቅ የራሳችን ክልል ይገባናል የሚሉበት ሁኔታ እያደገ ነው። ትግራይ ራሱን የቻለ ክልል ከሆነ ሲዳማ፣ ከምባታ፣ ሃድያ፣ ወላይታ፣ ጉራጌ ወዘተ ክልል የማይሆኑበት ምክንያት አይኖርም። እስከዛሬ ክልል እንሁን የሚል ጥያቄ ያላነሱት ወያኔን ፈርተው እንጂ ትግራይን ክልል ያደረጉት ምክንያቶች በነሱ ዘንድ ጠፍተው አልነበረም።

ከትግራይ ኩናማውንና ኢሮቡን አካቶ፣ በጋምቤላ ስም የተጨፈለቁትን ከ4 በላይ ማህበረሰቦችን ጨምሮ፣ በደቡብ ክልል ስም የተጨፈቁ ገና በውል ቁጥራቸው ያልለየላቸውን ማህበረሰቦችን ይዞ፣ በአማራ በኦሮሚያ ክልሎች ውስጥ ልዩ ዞንና ወረዳ የተባሉትን አካቶ፣ የጎሳ ልዩነቶቻቸውን በወጉ አስወግደው ገና አንድ ፖለቲካዊ ማህበረስብ መሆን ያልቻሉትን የምስራቅ ኢትዮጵያ ወንድሞቻችንና እህቶቻችንን አካቶ ሁሉም የራሴ ክልል ግዛት ይገባኛል የሚልበት ጊዜ ሩቅ የሚመስለው ካለ አውቆ የተኛ ብቻ ነው።

የቋንቋና የእምነት ተመሳሳይነት ያላቸው ማህበረሰብ አባላት በአለባባስ ልዩነት ብቻ የተለየ ማንነት እንዳላቸውና የራሳቸው በማንነት ላይ የተመሰረቱ ወረዳዎች እንደሚያስፈልጋቸው እየተናገሩ ነው። በቅርቡ ራያን አስመልክቶ እየተነሳ ያለው ጥያቄ በዚህ መንገዱ ሲገለጽ ሰምተናል። በቋንቋ ሳይሆን በአለባበስ እንለያለን መባል ተጀምሯል። በቋንቋ ተናጋሪነት አማርኛ ተናጋሪዎች የሆኑ ራያዎች በአለባበስ የተለየን በመሆናችን አማሮች አይደለንም ብለው እንደሚያስቡ “ተወካያቸው ነኝ” የሚል ግለሰብ በሚድያ ነግሮናል። የአለባበስ ልዩነት የማንነት ፖለቲካ ለማራመጃነት ስራ ላይ መዋል ጀመሯል ማለት ነው። ይህ በመላው ሃገሪቱ ባሉ ማህበረሰባት ሲመነዘር ምን አይነት እብደት ሊያስከትል እንደሚችል ግልጽ ነው።

በአንድ ዘር መሃከልም አውራጃና ዞን እየለዩ መናናቅና መፋጠጥ በብዙ ክልሎች የሚታይ ሲሆን፣ ዘረኝነት ወደ ከፍተኛ ደረጃ ሲደርስ አሁን በሃገሪቱ አሉ ከሚባሉት ከ80 ብሄረሰቦች በላይ በአስር እጥፍ የራሳችን ማንነት አለን የሚሉ ቡድኖች እንደአሸን የሚፈሉበትና የሚናቆሩበት ሁኔታ መፍጠሩ አይቀሬ ነው። በአንዳንድ ክልሎች የማንነት ጥያቄ ከቋንቋ በላይ ተሻግሮ በእምነቶች ዙሪያ አንድን ዘር ወደ መክፈል ሊሄድ የሚችልበት ፍንጭ እየታየ ነው። በአንድ እምነት ወስጥ የሺያና የሱኒ ሙስሊሞች እየተባባሉ የቅርብ ጎረቤቶቻቸን ሲፋጁ እያየን ነውና፣ እኛም ሃገር እምነቶች፣ የክርስትና ይሁን የእስልምና እምነቶች ጥቃቅን ልዩነቶቻቸውን የመቧደኛና የመጋደያ ምክንያቶች ሊያደርጓቸው የሚፈለጉ ሃይሎች ላለመነሳታቸው ምንም ዋስትና የለንም።

የሰው ልጅ ማንነቱ የሚገልጻባቸው እንደ አለባበስ፣ የባህል ምግብ፣ ጌጣ ጌጥ፣ የሙዚቃ መሳሪያ፣ ውዝውዜ፣ እምነት ወዘተ ማለቂያ የላቸውምና ማለቂያ የሌለው የማንነት የፖለቲካ ድርጅትና የፖለቲካ ማህበረሰብ እየፈጠሩ መቀጠል እንደማይቻል ማንኛውም ጤነኛ ሰው ያውቀዋል። እየሆነ ያለው ነባራዊ የፖለቲካ ሁነት የሚመሰክረው ሃቅ ጤናው የተናጋ ማህበረስብ ውስጥ መገኘታችንን ነው፡፡ የፖለቲካችን ጤንነት በፍጥነት የሚሻሻልበትን መንገድ ካልፈለግን ዘረኝነት የሃገራችንን ፖለቲካዊ ሴል ሁሉ እንደ ካንሰር ወርሮ በአስፈሪ የሞት ጥላ ስር እንደሚጥለን ማወቅ አለብን፡፡

ከዚህ በላይ በተባለው ላይ የሃገራችንን ድህነት እያሰብን እንቀጥል። ሃገራችን ድሃ በመሆኗ የተነሳ ለሁሉም የሃገሪቱ ልሂቅ የሚበቃ በቂ ብሄራዊ ሃብት የላትም። እድሜ ለወያኔ፣ ለፕሮፓጋንዳ ሲል ያለምንም የትምህርት ጥራት መቆጣጠሪያ ከከፈታቸው በርካታ ዩኒቨርስቲዎች ያመረታቸው ራሳቸውን በልሂቅ ደረጃ የሚመድቡ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ወጣቶች ይህን ለራሳቸው የሰጡትን የልሂቅነት ደረጃ የሚመጥን የተደላድለ ኑሮ መኖር የሚችሉበት ኢኮኖሚያዊ አቅም ቢያንስ ባጭር ጊዜ ሃገሪቱ ሊኖራት ኣይችልም። ይህ ልሂቅ አናሳ ከሆነው የሃገሪቱ ብሄራዊ ሃብት የቻለውን መቦጨቅ የሚያስችለው በፖለቲካ መስኩ በመሰማራት ብቻ እንደሆነ አውቆታል። በተለይ ጥሮ ግሮ በእውቀትና በብቃት ከመተዳደር ይልቅ የተንደላቀቀ ኑሮ መኖሪያ የፖለቲካ ድርጅት አባልና አመራር ሆኖ መቀመጥ መሆኑን የተረዳው የተለያዩ ዘሮች ልሂቅ ይህን የቁስ ሰቀቀኑን በህዝብ ኪሳራ ለማርካት ሲል በህዝብ ላይ ለመፈጸም የማይከጀለው ሃላፊነት የጎደለው የዘር ፖለቲካ ፈሊጥ/ዘየ አይኖርም። እንኳን ስልጣን ተይዞ ቀርቶ ስልጣን ሳይያዝ፣ በተቃዋሚ ድርጅት መሪነት ስንቶቹ በህልማቸው አስበውት የማያውቁትን ጥቅምና አንቱታ አግኝተው ተንደላቀው እንደኖሩ የተቃዋሚውን ገመና በደንብ የምናውቀው እናውቃለን።

ዛሬ እንዲህ አይነቱ የልሂቁ የፖለቲካ ስልጣንና የግል ጥቅምን አቆራኝቶ የሚያይ በከፍተኛ ደረጃ አግድም ያደገ ንቃተ-ህሊና ለሁሉም ህዝብ መከራ አምራች ሆኗል። በአሁኑ ወቅት ህዝብ በዘር ፖለቲካ ሳቢያ የከፈለው የስቃይ ተመክሮ እንደ ሰሜን ተራራ ገዝፎ እየታየ ነው። ዋንኛው የሃገሪቱ የዘር ፖለቲካ አርክቴክት ወያኔ ዛሬ ከአጥቂነት ወደ ተከላካይነት ተሸጋግሯል። ይህም ሆኖ ከመቼውም በላይ አዳዲስ የዘር ድርጅቶች በሃገሪቱ እየተበራከቱና በዘረኛነታቸውም ከዚህ ቀደም ካየናቸው በዘር ከተደራጁ ድርጅቶች እጅግ አክራሪ ሆነው እየታዩ ነው።

እነዚህ ድርጅቶች ለመፈጠራቸው የሚሰጡት ምክንያት የፈለገው ይሁን፣ ህዝብ በዘረኛነት መስፋፋት ጉዳት እንጂ ጥቅም እንደማያገኝ እውነታው ከብዥታ በጠራበት ሰአት አክራሪ ዘረኛ ድርጊታቸውን “ህዝባችን ለመጥቀም” ስንል ነው የምንገፋው ሊሉን አይችሉም። በእርግጠኛነት መናገር የሚቻለው እየተስፋፋ ያለው ዘረኛነት ከፍ ብዬ ከላይ ከጠቀስኩት ራሱን በፖለቲካ ሰብብ የከፍተኛ ስልጣንና ከዚህ ስልጣን ለሚገኝ ከፍተኛ ተጠቃሚነት ያጨ የልሂቅ ክሊክ ሴራ ነው። በተመሳሳይ ምክንያት ነው በአሁኑ ወቅት በዝቀተኛ ደረጃ ላይ የሚገኙ የአስተዳደር እርከኖች ከፍ ወዳለ የአስተዳደር እርከን ለመሸጋገር ሁሉን ድንጋይ በመፈንቀል ላይ የሚገኙት።

በተለያዩ ቦታዎች በአስተዳደር እርከን ከፍ ማለት ከፍተኛ ስልጣንና ጥቅም እንደሚያስገኝ የተረዳው የየዘውጌው ማህበረሰብ ልሂቅ ቀበሌውን ወረዳ፣ ወረዳውን ዞን፤ ዞኑን ክልል፣ ክልሉን ከተቻለ ራሱን የቻለ ሃገር ለማድረግ ሌት ተቀን እየሰራ ነው። ሌላም ችግር ልጥቀስ። ከማእከላዊ መንግስት ቁጥጥር ወጭ እስከ አንገታቸው የታጠቁ የዘር ክልል መንግስታት እርስ በርሳቸው በተለያዩ ጊዚያት ሲጋጩ ኖረዋል። እንደ ተለያዩ ሃገራት መንግስታት፣ ክልሎች በየሚሊሻቸውና በልዩ ሃይላቸው ሲዋጉ ታዝበናል። አንዱ ክልል የሌላውን ክልል ጥቃት ለመከላከል በሚል ሚሊሻውንና ልዩ ሃይሉን ሲያሰለጥን፣ አቅሙ የፈቀደውና መንገዱ ያለው ከነፍስ ወከፍ መሳሪያ እስከ ሚሳይል እያስታጠቀ እንደሆነ ይታወቃል። ዝርዝር ወስጥ ሳልገባ በአንዳንድ ክልሎች የሚከናወኑ ድርጊቶች፣ በዚህ ድርጊት የሚሳተፉ ግለስቦችና ቡድኖች በጊዜ የሚቆጣጠራቸው አካል ካልተገኘ በከፍተኛ መስዋእተነት የተጀመረውን የለውጥ እንቅስቃሴ አደጋ ውስጥ ሊጥል የሚችል በክልሎችና በህዝቦች መሃከል የሚካሄድ ግጭት ሊቀሰቅሱ ይችላሉ።

እውነታውን ለመግለጽ ያህል ይህን ካልኩ በብዙ መቶዎችና ሽዎች ገጾች የተደገፈ መረጃ መንግስት ስላለው ያልኩት እውነት ለመሆኑ አልጠራጠርም። ከሁሉም አቅጣጫ የሚጨሰው ጭስ የሚያመላክተው የክልል መንግስታት በራሳቸው በሚቆጣጠሯቸው ወይም በማይቆጣጠሯቸው ሃይሎችና በአጎራባች ክልሎች መሃከል ግጭት ሊነሳ የሚችልበት እድል እያደገ መምጣቱን ነው። በአንዳንድ ክልሎች የመጣበት ሁኔታ አለ። በሌላ በኩልም በክልሎች ወስጥ ዘረኛ በሆነ መንገድ የተደራጁ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ የፖለቲካ ሃይሎች፣ “ከኔ በላይ የኔን ዘር ሊወክል የሚችል ንጹህ ዘር የለም” በሚል መናናቅ ወደ እርስበርስ ግጭት አምርተዋል። በኢህአዴግ ውስጥ ባሉ ዘርን መሰረት ባደረጉ ድርጅቶችና ከኢሃዴግ ውጭ ባሉ በዘር ላይ በተደራጁ ድርጅቶች መሃከል የሚታየው ግጭትና ፍጣጫ የዚህ ውጤት ነው።

ባንጻሩ ደግሞ ያንድን ዘር ህዝብ ከሌላው ዘር ጥቃት ለመጠበቅ መሰባሰብ ይገባል በሚል ከዘር ውጭ በሌላ በምንም መርህ የማይገናኙ የተለያዩ ድርጅቶች “በዘር አንድነት” መርህ ብቻ ለመሰባሰብ ሲጥሩም ይታያል። በራሱ በተቃዋሚው ውስጥም በዘር ላይ የተመሰረቱ ድርጅቶች መሃከል ያለው መፋጠጥ ጥላቻና ግጭት “ከኔ በላይ ለዘሬ ላሳር” በሚሉ ቡድኖች መሃከል ነው።

ይህ ግጭት እየከፋ እንጂ እየከሰመ የሚሄድ አይሆንም። በመርህ ላይ ያልተመሰረተ የዘር ቡድኖች መሰባስቦች በሚታዩባቸው ክልሎችም ሁሉንም ሊያረካ የሚችል የጥቅም ድልድል መሸከም የሚችል ኢኮኖሚ ስለሌለ ውሎ አድሮ በመርህ አልባ ተሰብሳቢዎቹ መሃከል የስልጣንና የጥቅም ግጭትን ማስከተሉና መልሶ መሰነጣጠቁ አይቀርም። ይህ ብቻ አይደለም፤ በሁሉም ክልሎች ሁሉንም የክልሉን ልሂቃን ያካተተ ስልጣንና ጥቅም መስጠት ስለማይቻል ከዚህ ጥቅም ተቋዳሽ ያልሆነው ልሂቅ አዲስ የዘር አጀንዳ የሚያነሳ ድርጅት መፍጠሩ አይቀርም። የሚፈጠረው ድርጅት አድማጭ የሚያገኘው ከሌሎች ድርጅቶች የከረረ ዘረኛንት በማራመድ ስለሆነ የዘረኛነት የፖለቲካ ዑደት የህዝብ እርግማን እንደሆነ ይቀጥላል።

በሁሉም በዘር በተደራጁ ቡድኖች መሃል እየታየ ያለው ፉክክር “እኔ ለዘሬ ካንተ በላይ ተቆርቋሪ ነኝ” የሚል በመሆኑ፣ በየክልሉ የሚታየው ሁኔታ፣ በኢህአዴግ ወስጥ የበቀለው የለውጥ ሃይል ሊያረግበው የፈለገውን የዘር ውጥረት እንዲቀንስ እያደረገው አይደለም። በተቃራኒው እየከረረ የሚሄድ ዘረኛነት የለውጥ ሃይሉ ፈተና መሆኑን የሚጠቁም ነው። በሚፎካካሩ የዘር ድርጅቶች መሃል በሁሉም ክልሎች እየከረሩ ለሚሄዱ ዘረኛ ድርጅቶች እየተሰጠ ያለው ምላሽ ባላንጣ ተደርገው ከሚታዩ ድርጅቶች የበለጠ ዘረኛ ሆኖ መታየትና በዚህም ድጋፉን በሚሹት ህዝብ ዘንድ ተቀባይነት ማግኘት እንጂ የዘረኛነትን አደገኛነት በማመላከት ለጤነኛና ከዘር ቆጠራ ነጻ ለሆነ ፖለቲካ ህዝብን ማስተማርና ማደራጀት አይደለም። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሁለቱ ትልልቅ የዘር ክልሎች ወስጥ እየተስፋፋ ያለው አመለካከት፣ ኦሮሞውም ሆነ አማራው “እርስበርሱ በመከፋፈል ጠንካራ ብሄረተኛ አንድነት እንዳይኖረው ይሆናል ስለዚህም ልዩነታቸን ትተን በአንድ እንቁም” የሚል እንጅ “የዘር ፖለቲካው ለማናችንም አይበጀነምና ሃገራዊ እይታ ይኑረን” የሚል አይደለም።

የዘር ፖለቲካ አደገኛነቱን የተረዱት በኢህአዴግ ወስጥ የተነሱ የለውጥ ሃይሎች ራሳቸው የቆሙበት የስልጣን መሰረት ዘር ላይ የተደራጀ በመሆኑ፣ ከዚህ ዘረኛ መሰረት ላይ ከቆመ ኢህአዴጋዊ አደረጃጃት ጋር ሳይጋጩ ከዘር ፖለቲካ ምርኮኛነት ራሳቸውን እንዴት ነጻ ማድረግ እንደሚችሉ መገመት አስቸጋሪ ነው። ይህ የዘር ፖለቲካ በትንሹ እንኳን ከተነካካ ኢህአዴግ ራሱ እንደ አንድ ስብስብ እንዴት ሊቀጥል እንደሚችል ግልጽ አይደለም። የትግራይ ክልል ከዚህ ጋር በተገናኘ የሀገሪቱ ፓርላማ ጥናት እንዲያደርግና የመፍትሄ ሀሳብ እንዲያመነጭ ያቋቋመውን ኮሚሽን ከወዲሁ “ሕገ መንግሥቱን የሚጥስ ስለሆነ አልቀበለውም” የሚል ኦፊሴላዊ መግለጫ ማውጣቱ ኢህአዴግ እንደ ድርጅትና የለውጡ ኃይል እንዴት አብረው ሆነው ይህን ለውጥ ከዳር ያደርሱታል የሚለውን ጥያቄ ከመቼውም በላይ አስቸኳይ መፍትሄ የሚሻ ጥያቄ አድርጎታል።

የለውጡ ሃይሎች ፈረንጆቹ እንደሚሉት “ኬኩን ማስቀመጥ ኬኩንም መብላት” አይነት አጣብቂኝ ወስጥ ገበተዋል። ኢህአዴግን አሁን ባለው ቁመናውና ድርጅታዊ እምነቱ አትርፎ የሃገር ህልውናን መጠበቅ፤ ኢህአዴግን አትርፎ ዴሞክራሲያዊ ስርአት መዘርጋት በአንድ ላይ ሊሄዱ የማይችሉ ተቃራኒ ነገሮች መሆናቸው እየታየ ነው። በለውጥ ሃይሉ ውስጥ ያለው አመለካካት ግን ኬኩን መብላትም ማስቀመጥ የመፈለግ ቅርቃር ውስጥ የወደቀ ይመስላል።

ኢህአዴግን ከዘር ፖለቲካ ውጭ ማሰብ አይቻልም። የለውጡ ኃይል ለውጡን ለማካሄድ የሚያስችለውን መዋቅራዊ የሥልጣን መሰረቱን ያገኘውና የሚጠብቀው ባብዛኛው በዚሁ ድርጅት መዋቅር ክልል ውስጥ ሆኖ ነው። አሁንም ለሃገሪቱ ህልወናና ዴሞክራሲያዊ ስርአት በሃገሪቱ መፈጠር አደገኛ የሆነው የኢህአዴግ መሰረታዊ ባህሪ በዘር ፖለቲካ ላይ የተገነባ ድርጅትነቱ ነው። ይህ የድርጅቱ ባህሪ በሃገሪቱ መምጣት ለሚገባው ለውጥ እንቅፋት ብቻ ሳይሆን ለውጥ ፈላጊውንም የኢህአዴግ ሃይል ጭምር ሊበላ የሚችል ነው። የለውጥ ኃይሉ ለውጥ ለማምጣት ያለውን ፍላጎት በከፍተኛ ደረጃ የሚደግፍለት ከኢህአዴግ ውጭ ያለው አብዛኛው ማህበረሰብ ከለውጥ ኃይሉ የለውጥ አተገባበር ሥራ ጋር ምንም ግንኙነት የለውም። በስልጣን እርከን ወደታች እየተወረደ ሲሄድ የለውጥ ኃይሉን ውሳኔዎች የሚያስፈጽመው (ወይንም አውቆ እንዳይፈጸም እንቅፋት የሚፈጥረው) ይኅው በኢህአዴግ ውስጥ የነበረው ሀይል በመሆኑ በማህበረሰቡ ውስጥ በከፍተኛ ጥርጣሬ የሚታይ ነው።

2.2. ከህግ የበላይነት መጥፋትና ከብልሹ አስተዳደር ጋር የተያያዙ ችግሮች

በሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች ዜጎች በነጻነት መስራት፣ መነገድ፣ መማር፣ ሃሳባቸውን መግለጽ፣ መሰባሰብና መደራጀት የሚችሉበት ሁኔታ እየጠፋ ነው። ከቦታ ቦታ በነጻነት የመጓጓዙ፣ የመነገዱና የመሰባሰቡ ሂደት በዘር በተደራጁ ፖለቲካ ለበስና ፖለቲካ ለበስ ባልሆኑ ህጋዊና ህገ ወጥ ሃይሎች ክፉኛ እየተሰተጓጎለ ነው። ግለስቦችንና ቡድኖችን በዘር፣ በፖለቲካ አመለካከት፣ በሃብት ልዩነት የፈረጀ፣ አፈና ግድያ በየቀኑ እየተስፋፋ ነው።

በአጭር ጊዜ ውስጥ ከቁጥጥር ውጭ ሊወጣ እንደሚችል መረጃዎች ይጠቁማሉ። ይህንን አይነቶችን በዜጎች ላይ የሚደረሱ የመብት ጥሰቶች መከላከል ይገባቸው የነበሩ የየክልሉ መንግስት አካላት በአንዳንድ ቦታዎች ራሳቸው የመብት ጥሰት አሰፈጻሚዎቹ ሲሆኑ፣ በሌሎች ቦታዎች ከነሱ ለባሱ ጉልበተኞች አሰተዳደራዊ ስልጣናቸውን ለቀው ለመንጋ አሰተዳዳሪዎች እጅ እየነሱ መኖሩን መርጠዋል።

የመንግስት ጥበቃ እንደማያገኝ የተረዳው ማህበረሰብ የየሰፈሩን ጉልበተኞች ጥበቃ በገንዘቡ፣ በአድርባይ ጠባዩና በምልጃ እያገኘ በሰላም ለመኖር እየሞከረ ነው። ይህ ሂደት በሁሉም ክልሎች እየተስፋፋ ነው። ይህ ሂደት በጊዜ ሳይቆም ቀርቶ ዜጎች ከመንግስት ይልቅ ለደህንነታቸው ሲሉ ለማፊያ ቡድኖች መገበር ከጀመሩ ህዝብን መልሶ በመንግስት ላይ እምነት እንዲኖረው ለማድረግ በጣም ከባድ ይሆናል። የማፊያ ቡድኖቹ እንደ አሸን የሚፈሉበት፣ ከህዝብ በሚሰበስቡት ሃብት መንግስትን መገዳደር የሚችሉበት ጉልበት ማደራጀት የሚችሉበት ደረጃ ላይ ይደርሳሉ። በሽህ የሚቆጠሩ የመንደር የሽፍቶች አለቆች በጀሌዎቻቸው አማካይነት የግዛት ማስጠበቅና የማስፋት ውጊያ ውስጥ መግባታቸው አይቀርም።

ይህ ኢ-ፖለቲካዊ የሆነ የማፊያ አይነት አደረጃጃት በዘር ፖለቲካው ዙሪያ እየታየ ባለው ማፊያ መሰል የባንክ፣ የህዝብና የሸቀጦች መጓጓዣ መኪናዎች ዘረፋ፣ የግለሰቦች እገታና አፈና፣ የነዳጅና የጥሬ እቃ አቅርቦት ጋር የተያያዙ ችግሮች በሚፈጥሩ የመንገድ መዝጋትና በዘር ልዩነት ጋር ተያያዞ በሚታየው ውጥረትና መሳሳብ ላይ ሲጨመር ሰይጣን ቢመኘው እንኳን ሊፈጠረው የማይችለው ሃገራዊ ገሃነም መፍጠሩ አይቀሬ ነው። በተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎች መንግስታዊ አገልግሎቶች ከተራ አስተዳደራዊ አገልግሎት አንስቶ እስከ መሰረታዊ የትምህርት የጤና የፍትህ አገልግሎቶች የውሃ የኤሌትሪክ አቅርቦቶች እየተሰተጓጎሉ ነው። ሌላው ቀርቶ በአዲስ አበባ ከተማ ወስጥ፣ ከለውጡ በፊት የውሃ አቅርቦት ችግር ያልነበረባቸው አንዳንድ የከተማ ክፍሎች ለወራት አንዲት ጠብታ ወሃ ያላዩበት ሁኔታ ተፈጥሯል።

ባልተረጋጋ ሁኔታ ውስጥ የሚዳክረው የሃገሪቱ ኢኮኖሚ ቀድሞውኑ ተገንብቶበት የነበረው አሸዋ ከስሩ እየከዳው በመሄድ ላይ ነው። በሚሊዪኖች ለሚቆጠሩ ስራ አጥ ወጣቶች ስራ መፍጠሩ ቀርቶ በስራ ላይ ለነበሩትም የስራ ዋስትና መስጠት የማይችልበት ሁኔታ እየተፈጠረ ነው። ያለምንም ገደብ የተዘረፈን የሕዝብ ሀብት ለማጠብ ሲባል ካለበቂ ያዋጭነት ጥናት የተቆለሉት ህንጻዎችና በነኝህ ጥቂት ሙሰኞች ሲበተን የነበረው ማለቂያ የሌለው ብር ተጠቃሚ የነበሩ ያገልግሎት ተቋማት እንኳን አዲስ ስራ ሊፈጥሩ ለራሳቸውም ችግር ውስጥ ገብተው ከባንክ የተበደሩትን ገንዘብ መክፈል የማይችሉበት ደረጃ ላይ ደርሰዋል። ስራ ላይ ውለው ከሚያመጡት ትርፍና ሀገራዊ ጥቅም ይልቅ በሂደቱ ከሚገኝ ሙስና የሚገኘውን ጥቅም በማስላት ተጀምረው ማለቅ ያቃታቸው ትላልቅ ፕሮጀክቶችና ለነኝህ ፕሮጀክቶች በራሱ ያዋጭነት ግምገማ ተነስቶ ሳይሆን በኮሚሽኑ ጥቅም በሚያገኙ የመንግሥት ባለሟሎች ቀጭን ትዕዛዝ ያለገደብ ገንዘብ ሲያበድሩ የነበሩ የመንግሥት የፋይናንስ ተቋማት ያበደሩትን ገንዘብ በትክክለኛ የኢኮኖሚ ስሌት ሊመልሱ እንደማይችሉት እየታወቀም በሂሳብ ደብተራቸው ብድሩን እንደ ንብረት እየቆጠሩ አሁንም ትርፋማ ነን እያሉ በሀሰት ፕሮፓጋንዳ ማህበረሰቡን ያወናብዳሉ። ግን የሚያበድሩት በቂ ገንዘብ እንደሌላቸው ሁሉም ያውቀዋል። ለነኝህ ችግሮች ሀገሪቱን የዳረጓት ባብዛኛው ኢህአዴጋውያን ወይንም ከድርጅቱ ጋር የተጣመሩ አድርባዮች አሁንም ከተቋም ተቋም፤ ከስልጣን ስልጣን እየቀየሩ የፈጠሩትን የኢኮኖሚ ችግር እንዲፈቱት ይጠበቃል። በዚህ ላይ ደግሞ ከአቅም ማነስም ባሻገር እነኝሁ ኃይሎችና ለውጡን ለማኮላሸት ብሎም የለውጥ ሃይሉን ተአማኒነት ለማሳጣት በኢኮኖሚው ላይ የሚያኪያሂዱትን ያልተቋረጠ አሻጥር ስናክልበት የቀውሱን ሙሉ ሰእል ለማየት እንችላለን።

በኢህአዴግ ውስጥ የተነሱት የለውጥ ኃይሎች “ይሆናል” ያሉት አዲስ አስተዳደራዊ ባህል በመካከለኛውና ዝቅተኛው የመንግስት የአስተዳደር እርክኖች ፈጽሞ ተቀባይነት አላገኘም። በዘመድ አዝማድ፣ በዘር ውገና፣ በጉቦ የሚሰራው ስራ ከመቼውም በላይ ተጠናክሮ እየሄደ ነው። ህዝብን ማገልገል፣ ለአገልግሎት ጥራትና ተደራሽነት መጨነቅ፣ የመሳሰሉት የለውጥ ሃይሉ የስራ እሴቶች ከመሪዎች ምኞት አልፎ መሬት ላይ በተግባር እየታዩ አይደለም። እንዲያውም በነዚህ የአስተዳደር እርከኖች ላይ የተቀመጡ የመንግስት ባለስልጣናትና ሰራተኞች “ወደፊት የሚመጣው አይታወቅም” በሚል ስሌት ህገ ወጥ በሆነ መንገድ የሚችሉትን ሁሉ ሃብት በማግበስበስ ላይ ናቸው።

የቆየው መንግስታዊ መዋቅር ሹማምንት በኢህአዴግ ውስጥ የተነሳው የለውጥ ሃይል የለውጥ ፍላጎቱን ለማስፈጸም እነሱን ከመጠቀም ውጭ ሌላ አማራጭ እንደሌለው በመገንዘባቸው አግባብበነት የሌላቸውን ድርጊቶች በከፍተኛ እብሪት እያከናወኗቸው ይገኛሉ። በኦሮሚያ ክልል የሚታየው የበርካታ ባንኮችና በመጓጓዝ ላይ የነበረ የመንግስት ገንዘብ ዘረፋ እውን የህገ-ወጥ ታጣቂዎች ለብቻቸው ያደረጉት ወይንም የአካባቢው ሹማምንት እና የተቋማቱ ሰራተኞች እጅ የገባበት ዘረፋ ነው? የሚል ጥያቄ የሚያስነሳ ነው።

እንዲህ አይነቱ ተመሳሳይ ዘረፋ በሁሉም ክልሎች ቀሰ በቀስ እየተሳፋፋ ነው። በቅርብ ጊዜ ውስጥ የሁሉም ክልሎች ህይወት መገለጫ መሆኑ አይቀርም። ህጋዊ በሆነ መንገድ ህገ-ወጥ በሆነ ሁኔታ የተለያዩ ዘረፋዎች ያኪያሄዱ አካላት ከጥቂቶቹ በስተቀር ያለ ምንም ስጋት በህዝብ መሃከል በሚምነሽነሹበት ሃገር፣ ባንክ መዝረፍ እንደ ልጆች ጨዋታ ቀላል ሆኖ መታየቱ አይቀርም። አስከፊ ህይወታቸውን በዘረፋ ለመቀየር የሚመኙ፣ ምኞታቸውንም ወደ ተግባር የሚቀይሩ ዜጎችና ቡድኖች በብዛት ማየት የሚያስገርም አይሆንም። ለውጡ በጠቅላላው ከኢህአዴግ ውስጥ ብቅ ያሉት የለውጥ አመራሮች እንደ ተመኙት በማህበረሰቡ ወስጥ የሞራልና የባህል ተሃድሶ እያመጣ አይደለም የሚታየው፤ የበለጠ ዝቅጠት ነው።

የመሳሪያ ንግድን እንቅስቃሴ ከመቸውም በከፋ መልኩ እየተካሄደ ነው። ከተወሰኑ አመታት በፊት ኢትዮጵያ እስክ ቻድና ሞዛምቢክ የሚደርስ የመሳሪያ ንግድ አሰራጭ የሆነችበት ሁኔታ አብቅቶ ዛሬ በግለባጩ ከሁሉም አቅጣጫ መሳሪያ በገፍ የሚገባባት፣ በጣም በከፍተኛና ወድ ዋጋ የሚሸጥባት ሃገር ሆናለች።

ክልሎች እስከ አፍንጫቸው የታጠቁ ሚሊሻዎች፣ ልዩ ሃይሎች፣ ፖሊሶች፣ ደህንነቶች መያዛቸው አንሶ ማንኛውም በክልሎች ውስጥ የሚኖር የዘር ታማኝነቱ አጠያያቂ ያልሆነን አካል እንዳሻው እንዲታጠቅ ልቅ አድርገውታል። በአንዳንድ ክልሎች መንግስት ስልጣን የሰጣቸው አካላት ማህበርሰቡን እያሳታጠቁ ያሉት ለማይቀረው ውጊያ ራስህን አዘጋጅ የሚል በዘር ላይ የተመሰረተ ቅስቀሳ እያደረጉ ነው። የሚገርመው ነገር በየክልሎቹ መሳሪያ የሌለውን ግለሰብ የየክልሉ ባላሃብት በገንዘባቸው እየገዙ አስታጣቂዎች መሆናቸው ነው። ግለሰቦች ከፈለጉ ከነፍስ ወከፍ መሳሪያ በላይ መግዛት የሚችሉበት ገበያ መፈጠሩን የውጭ መንግስታት ድርጅቶች ሳይቀሩ እየተናገሩት ያለ ጉዳይ ሆኗል። ይህ ሁኔታ ደግሞ ክልሎች በሌሎች ክልሎች ሊሰነዘርብን ይችላል ከሚሉት ጥቃት በተጨማሪ ዜጎች በክልሎች ወስጥ በገፍ በታጠቁና የራሱ የክልሉ ኗሪ በሆኑ ሽፍቶች እጅ አበሳቸውን ማየት የሚችሉበትን ሁኔታ በአጭር ጊዜ እውን እንዳያደርግ ያሰጋል።

ድህነት፣ ስራ አጥነት ዘረኛንተና የመሳሰሉ ማህበራዊ ህፀጾች በተጠራቀሙባት ሃገር እንኳን መሳሪያ በማንም እጅ ገብቶ ቀርቶ ጥብቅ የመሳሪያ ቁጥጥር በሚደረግባቸው ሃብታም ሃገሮች ሳይቀር በዜጎች ላይ የቀትር ዘረፋና ፍጅት የሚያኪያሂዱ ቡድኖች ማስቆም አይቻልም። በዚህ ላይ ሁሉም ከየት አካባቢ ሊሰነዘረበት እንደሚችል እርግጠኛ ላልሆነበት ጥቃት እራሱን ለመከላክል የሚያደርገው ሙከራ ሲታከልበት ሃገር በሩር እንዲጋይ የሚፈልገው አንድ ብልጭታ ብቻ መሆኑ ግልጽ ነው።

በህግ ሊፈለጉ የሚገባቸውና ህግ እየፈለጋቸው ያሉ ወንጀለኞች ራሳቸውን መሸሸግ የሚችሉባቸው ክልሎችና የፖለቲካ ድርጅቶች እያገኙ ነው። የግለሰቦች ስብእና ቀናነት፣ የሞራል ጥብቅነት በሚገባ ሳይመረመር እንደ ወያኔ ገራፊዎች ገዳዮችና ዘራፊዎች የተቃዋሚ ድርጅት መሪዎችና አባላት በነበሩበት ወቅት በሰሩት ወንጀል በህግ ሊጠየቁ የሚገባቸው ግለ-ሰቦችና ቡድኖች በተቃዋሚ ስም ብቻ በገዥው ፓርቲ ወሰጥ ሳይቀር የሚታቀፉበት ለከፍተኛ ስልጣንና ጥቅም የሚበቁበት ሁኔታ እየታዬ ነው። ይህ እየተከናወነ ያለው በክልሎች አካባቢ መሆኑ ችግሩን የበለጠ አሳሳቢ ያደርገዋል። እነዚህ አይነት ሃይሎች በቂምና በቀል ላይ የተገነባ ስብእናቸው የጥላቻ መርዙን ሲዘራ የሚውልና የሚያድር ብቻ ሳይሆን፣ ከፍተኛ የነዋይ አፍቃሪነታቸው በአጭር ጊዜ ውስጥ ይህን የፈረደበትን ህዝብ ከወያኔ ባልተናነሰ መብቱን ሊገፍፉና ሃብቱን ሊዘረፉ የማይችሉበት ምክንያት የለም። በዚህ ደግሞ መልካም ስሙና ተአማኒነቱ የሚጎዳው እነዚህን ግለሰቦችና ቡድኖች ያቀፈና ለስልጣን ያበቃ ተደርጎ በስህተት የሚታየው ከኢህአዴግ ውስጥ የወጣው የለውጥ ሃይል ራሱ ነው።

ከዚህ በላይ የጠቀስኩት ውጥረት በተጋነነ መልኩ በአዲስ አበባና በአንዳንድ ከተሞች አለመታየቱ የሃገሪቱን ገዥዎችና መቀመጫቸውን በሃገሪቱ ዋና ከተማ ያደረጉ የሃገሪቱ የፖለቲካ ልሂቃን በከተማው በሚያዩት የተረጋጋ የሚመስል አሳሳች ሁኔታ ተሸብበው የወቅቱ አደገኛነት ላይታያቸው ይችላል። በሌሎች የሃገሪቱ ክልሎቸ እየተከሰተ ያለው አሳዛኝ እጣ እንደ አዲስ አበባ ወዳሉ ከተሞች ሳይቀር ሊስፋፋ አይችልም የሚል ተስፈኛነት ሊኖር እንደማይገባ የቡራዩን አሰቃቂ እልቂት ማስታወሱ በቂ ነው። አዲስ አበባ ከተማም ወስጥ የተደራጀ ዘረፋ እየተበራከተ እየመጣ እንደሆነ መዘንጋት የለበትም። ዘረፋውን ተቋማዊ ለማድረግ የሚሰሩ የፖለቲካ ሃይሎች እንዳሉም ፍንጮች እየተያዩ ነው።

ጥግ የያዘ አስፈሪ የዘረኝነት አመለካከትና የዘር መቧደን እንደ ወረርሽኝ በሽታ ከተገመተው በላይ በከፍተኛ ፍጥነት እንዲስፋፋ ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ ነው። የሃገሪቱን የኢኮኖሚና ማህበራዊ ድህነትና በ50 ሚሊዮኖች የሚቆጠር የህይወት ተሰፋ የጨለመበት፣ በስራ አጥነትና በድህነት የሚኖር፣ በዘር ላይ በተመሰረተ የማንነት ግንዛቤ ላይ ተኮትኩቶ ያደገ ወጣት ባለባት ሃገር የሰላምና የመረጋጋት ደሴት የሆኑ ጥቂት ቦታዎች ላይ ትኩረትን እያደረጉ (ለዛውም ካሉ ነው) ራስን ማታለል ትልቅ ስህተት ነው። ዘርን መሰረት አድርጎ፣ ጥላቻን ተመርኩዞ፣ ቂም በቀለን አርግዞ የሚነሳው ሱናሜ አዲስ አበባን እንደ ሶሪያ ከተሞች ለማድቀቅ እንደሶሪያ አመታት አይደለም ሳምንታት አያስፈልገውም።

ብዙዎቻችን በጣም መጥፎ ነገሮች ይሆናሉ ብለን ስንሰጋ በውስጣችን የሚቀሰቀሰውን መረበሽ መቋቋም አንችልም። ይህን የሚያውቅ ተፈጥሯችን ስጋቶቹ እንደሌሉ አድርገን ወስደን እንድንረጋጋ የሚያደርግ ውስጣዊ መከላካያ አለው። ይህ በእውነታ ክህደት ላይ የተመሰረተ የውስጣዊ ሽብር መከላከያ ከግለሰብ ህይወት ጀምሮ ለዘመናት ህዝብን፣ ስልጣኔዎችን፣ ሃገራትን ለቀውስና ለከፋ አደጋ ያጋለጠ ነው። ሮም በመጨረሻዋ ሰአት ሁሉም ዜጎቿ፣ ገዥውና ተገዥዋ፣ ስልጣኔዋን ዶግ ዓመድ ሊያደርግ ያሰፈሰፈውን መዓት አይናቸውን ገልጠው በማየትና መፍትሄ በመፈለግ ፈንታ የወይን ጠጅ፣ የአስረሽ ምችውና የልቅ-ወሲብ መስተንግዶ እንዲቀርብላቸው ይጠይቁ እንደነበር ይነገራል።

ዛሬ በሃገራችን ከመቼውም ጊዜ በላይ አይንን ከፍቶ ፣ በሃገር ህልውና ላይ ያሰፈሰፈውን አደጋ ለማየት በሚያስፈልግበት ወሳኝ ወቅት ላይ ይህን የሚፈቅድና ሊጋፈጠው የሚሞክር ዜጋ እየታየ አይደለም። ይህ እጅግ በጣም አሳሳቢ ጉዳይ ነው።

ይቀጥላል

ህዳር 2011

Related Stories