በሃገራችን ህልውና እና የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ላይ ያንዣበቡ አደጋዎች እና የመውጫ መንገዶች ካለፈው የቀጠለ

ነፃ ሃሳብአበይት ጉዳይ

3/12/20232 min read

በሃገራችን ህልውና እና የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ላይ ያንዣበቡ አደጋዎች እና የመውጫ መንገዶች

አንዳርጋቸው ጽጌ

ካለፈው የቀጠለ

3. የፖለቲካ ምህዳሩ መጥበብና ለዴሞክራሲ ስርአት ግንባታ የተገኘ ጠባብ እድል የውርጃ አደጋ

በጣም የሚገርመውና የሚያሳሰበው ሌላ ጉዳይ ሁሉም የፖለቲካ ሃይሎች የዴሞክራሲ ስርአት ምስረታ ህልማችን ከመቼውም ጊዜ በላይ የከፋ አደጋ ውስጥ መውደቁን ለማየት ፈቃደኞች አለመሆናችን ነው። ይህን አደጋ እንዳናይ የሚያድርጉ ነገሮች ብዙ ናቸው። “ከሞላ ጎደል የፖለቲካ እስረኛ የሚባል ነገር አለመኖሩ፣ ሚድያዎች በነጻነት የሚዘግቡ መምሰላቸው፣ የታገዱ የፖለቲካ ድርጅቶችና ድረ-ገጾች አለመኖራቸው፣ በፌደራል መንግስቱ በኩል እውነተኛ ዴሞክራሲ በሃገር ላይ እንዲኖር አስፈላጊ ናቸው የተባሉት ተቋማት ነጻና ገለልተኛ ሆነው እንዲቁቋሙ ባለስልጣናቱ ደፋ ቀና ማለታቸው፣ በመንግስትና በተፎካካሪ ፓርቲዎች መሃል ቅርበት ያለው፣ ግልጽነት የተሞላበት ግንኙነት መኖሩና ወዘተ፣ ለተሳሳተ የሁኔታዎች እውነተኛ ግንዝቤ እንዳይኖረን እያደረጉ ነው።

ሆኖም ግን ሁኔታዎችን በጥሞና ለተመለከተ የዴሞክራሲ ምህዳሩ አደገኛ በሆነ መንገድ እየጠበበ መሆኑን ማየት ይችላል። የፖለቲካው ምህዳሩን በማጥበብ ላይ ያለው መሰረታዊ ምክንያት አሁንም የዘር ፖለቲካ ነው። የፌደራል መንግስቱ የፈለገውን ያህል ቅን ቢሆን ዋነኛ የፖለቲካው ትግል በሚደረግበት ቦታ ላይ የሚገኙት የመንግስት አካላት ተመሳሳይ ቅንነት ማሳየት ካልቻሉ የፌደራል መንግስቱ ጥረት ከንቱ ሆኖ የሚቀር ነው።

ችግሩን ባጭሩ ለመግለጽ ልሞክር። ተጨባጭ የሆነው የሃገሪቱ የፖለቲካ አውደማ የሚገኘው በፌደራሉ እጅ ሳይሆን በክልሎች እጅ ነው። ፖለቲካው ብቻ ሳይሆን ተጨባጭ የሆነው ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ህይወት ያለው በፌደራል ደረጃ ሳይሆን በክልሎች እጅ ነው። ፌደራል መንግስቱ ዜጎችን የሚያኖርበት የራሱ ነጻ ክልል ወይም ወረዳ የለውም። ኢትዮጵያ የፌደራሉ መንግስት ጉዳይ ትሁን እጅ የኢትዮጵያ ህዝብ ሁለንተናዊ ህይወት በክክሎችና በስራቸው ባሉ ዞኖች ወረዳዎችና ቀበሌዎች እጅ ነው። መሰረታዊ የሆነው የዜጎች ህይወት ተጀምሮ የሚያልቀው በክልሉ መንግስታት ስልጣን ስር በሚገኙ ግዛቶች ውሰጥ ነው። በፖለቲካው ላይ ብቻ ስናተኩር፣ አንድ የፖለቲካ ድርጅት፣ ስልጣንን በወረዳ ይሁን ወይም በክልል ወይም በሃገር አቀፍ ደረጃ መያዝ የሚችለው የምርጫ ወረዳዎች ላይ በሚያደርገው ወሳኝ እንቅስቃሴና ፉክክር ነው። እነዚህ የምርጫ ወረዳዎች በክልል መንግስታት እጅ እንጂ በፌደራል መንግስቱ እጅ አይደሉም። የምርጫ ቦርድ፣ የፍትህ ስርአት፣ የመከለካያ፣ የደህንነት የፖሊስና የሚድያ አካላት በፌደራል መንግስቱ ጥረት ምንም ያህል ነጻና ገለልተኛ ሆነው ቢደራጁ በወረዳ ደረጃ የሚፈይዱት ነገር አይኖርም። ወረዳዎች የሚገኙት ዘርን መነሻ አድርጎ በተዋቀረ የክልል አስተዳደርና ዘርን መሰረት አድርገው በተደራጁ የፖለቲካ ድርጅቶች እጅ ነው።

እነዚህ ክልሎች የራሳቸው በመቶ ሽዎች የሚቆጠሩ የሚሊሻ አባላት፣ በሽዎች የሚቆጠሩ የልዩ ሃይል አባላት፣ የፖሊስ አባላትና የደህንነት አባላት አሏቸው። በዚህ ላይ በነዚህ በዘር በተደራጁ ፓርቲዎችና በስራቸው ባለ የክልል መንግስት ሙሉ ቁጥጥር ስር ያለ የቴሌቪዥንና የሬዲዮ ጣቢያዎች አሏቸው። እነዚህ ክልሎች በዘር ላይ የተመሰረተ ፓርቲ የሚያንቀሳቅሰው የሲቪል ሰርቪስና ይህ ፓርቲ የሚያንቀሳቅሰው ከፍተኛ በጀት አላቸው። ከፍተኛ የመሬትና የቤት ሃብት አላቸው። ይህንን ሁሉ ጉልበት እንዳሻቸው መጠቀም የሚያሰችል የፌደራል መንግስቱ ገድብ ሊያበጅበት የማይችል ነጻነት አላቸው። ይህን ሃብትና ጉልበት ተጠቅመው ዜጎችን በፈለጉት መንገድ ለነሱ አጎብድደው እንዲኖሩ የሚያስደርግ የበላይነት አጎናጽፏቸዋል። አንድ ዜጋ ቤት ቢሰጠው በነሱ በጎ ፈቃድ እንጂ ቤት በዜግነቱ ማግኘት የሚገባው መብት እንዳልሆነ አድርጎ እንዲያይ አድርገውታል። እነሱን ሲያስቀይም ቤቱን እንደሚያጣ ያውቀዋል። በጥቃቅንና አነስተኛ የተደራጁ ወጣቶች የሚያገኙት ብድር፣ ብድር የሰጣቸውን የክልል መንግስትና ፓርቲ እስከደገፉና እስከሚደግፉ ብቻ እንደሆነ ያውቁታል። ብድሩ ቢስማማቸው ነገር ግን ብደር የሰጣቸው የመንግስት አካልና የፓርቲው ፖሊሲዎች ባይጥማቸው የፖለቲካ ነጻነታቸውን ተግባራዊ ማድረግ አይችሉም። ቤት፣ ብድር፣ መሬት ከፓርቲ ጋር በሚደረግ ቁርኝት በሚሰጥበት፣ ግለሰቦች ምንም አይነት የኢኮኖሚ ነጻነት ሊኖራቸው በማይችል ኢትዮጵያን በመሰለ ደሃ ሃገር ውስጥ የመንግስት ስልጣን የሚይዙ የፖለቲካ ድርጅቶች እንዴት ሁሉንም ህዝብ ያለፍላጎቱ የፖለቲካ ድርጅታቸው ቁራኛ ወይም ምርኮኛ ማድረግ እንድሚችሉ ግልጽ ነው። ሃብታሙ ሁሉ ለኢህአዴግ በሚሊዮኖች ሲያዋጣ የኖረው ያለማዋጣትን መዘዝ በሚገባ ስለሚያወቀው እንጂ ኢህአዴግን ወዶ እንዳልሆነ የታወቀ ነው። ከባለስልጣናቱ ጋር በሽርክና ከሚዘረፈው ሃብታም ውጭ ስላለው ሃብታም ነው የማወራው። የደሃው እጣ ደግሞ ከሃብታሙም የባሰ ነው። በክልሎች ውስጥ የንብረት፣ የሃብት፣ የቅጥር፣ የሰራ ዋስትና ሌሎችንም ለማንኛውም ዜጋ በዜግነቱ ማግኘት የሚገባውን ግልጋሎቶች ፈልጎ ከክልል መንግስታት ገዥ ፓርቲዎች የተለየ የፖለቲካ ልዩነት ይዞ መገኘት የማይታሰብ ነው። በሆዱ ወይም መኝታ ቤቱን ዘግቶ፣ ሚስቱንና ሰራተኛው እንዳይሰሙት ተጠንቅቆ፣ የሚያምንበትን የፖለቲካ እመነት ይጮህ ካልሆነ በስተቀር በአደባባይ ሰለክልል ባላስልጣናት ያለውን በጎ ያልሆነ አመለካክት ደፍሮ የሚናገር ያበደ ብቻ ነው ።

እነዚህ ከላይ የጠቀኳቸው በክልሎች እጅ ያሉ ወታደራዊና ሲቪል ተቋማት በፌደራል እጅ እንዳሉት ተቋማት ነጻና ገለልተኛ ማድረግ አይቻልም። ከፍጥረታቸው አንድን ዘር ለይተው እንዲያገለግሉ የተደራጁ ናቸው። የፍጥረታቸው ድርና ማግ ገለልተኛነት ሳይሆን ውግንና ነው። ዋናው የፖለቲካ አውደማ ላይ በዚህ ደረጃ ፈጽሞ የገለልተኛነት እሳቤ ሊዘራባቸው የማይችሉ ተቋማት ባሉበት ሁኔታ በምን አይነት ሳይንስና ቀመር ነው በኢትዮጵያ ውስጥ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ሆነ ዴሞክራሲያ ሽግግር ማድረግ የሚቻለው? ዴሞክራሲው ቀርቶብን እንዲህ አይነቶቹ የፈረጠመ ጡንቻ ያላቸው የፌደራል መንግስቱን በጉልበት መገዳደር የሚችሉ ክልሎች በተመሰረቱበት ሁኔታ እንዴት ተደርጎ ነው የሃገርን ህልውና ማስከበር የሚቻለው?

በእነዚህ በዘር በተደራጁ የፖለቲካ ሃይሎች የሚዘወሩ መሳሪያ የታጠቁና ያልታጠቁ ተቋማት ባሉበት ሁኔታ እንኳን ነጻና ፍትሃዊ ምርጫ ማድረግ፣ ሰላማዊ በሆነ መንገድ የምርጫ ውጤትን መቁጠርና የምርጫ ወጤትን በጸጋ መቀበል ቀርቶ ምርጫ የሚባል ነገር ገና ስሙ ባልተጠራበት ወቅት እንኳን በእነዚህ ክልሎች ነጻ ሰላማዊና ህጋዊ የፖለቲካ እንቅስቅሴ ማድረግ ወደማይቻልበት ሁኔታ ሃገራችን ገብታለች። በዚህ ረገድ የሚታየው ችግር የለውጥ ሃይሎቹ ከመምጣታቸው በፊት ከነበረውም የከፋ ሆኗል።

ቀደም ባሉት አመታት ምርጫውን በጉልበት ወይም በሌብነት አሸንፈዋለሁ የሚል መተማመን የነበረው ኢህአዴግ በሃገር ወስጥ ለነበሩ ተቃዋሚ ድርጅቶች በየትኛውም ቦታ ዞረው ማደራጀትና መቀስቀስ ይፈቅድ ነበር። በወቅቱ ግን የፌደራል መንግስቱ ስለዴሞክራሲ የሚያስተላልፈው መልእክት የምር መሆኑን ክልሎች ተረድተውታል። በዚህ የተነሳ “ዴሞክራሲ ያለ ለማስመሰል ለተቃዋሚዎች ነጻነት እንስጣቸውና በክልላቸን ይንቀሳቀሱ” የሚለውን ጨዋታ አቁመዋል። “ወደ ቀያችን ትደርስና ውርድ ከራስህ” የሚል ማስፈራሪያ ከየክለሉ መድረስ የሚጀመረው ተቃዋሚ ድርጅቶች ወደ ክልሉ መንቀሳቀስ ከማሰባቸው በፊት ሆኗል። የክልሎች ዴሞክራሲያዊ ጭምብል ወልቆ አይን ያወጡ አፋኝ አሰተዳደሮች ሆነዋል።

ዛሬ ባለንበት ወቅት ከአዲስ አበባ ውጭ ከዚህ ቀደም ታይቶ በማይታወቅ ደረጃ የፖለቲካ ምህዳሩ የጠበበበት ሁኔታ ውስጥ እንገኛለን። አዲስ አበባ ውስጥም የሚደረግ የፖለቲካ እንቅስቃሴ አልፎ አልፎ በዘር በተደራጁ የፖለቲካ ቡድኖች ተጽእኖ የተነሳ ነጻና ሰላማዊ የፖለቲካ እንቅስቃሴ የሚስተጓጎልበት ሁኔታ ይታያል። ከአዲስ አበባ ውጭ ይህ የፖለቲካ ምህዳር መጥበብ ምን እንደሚመስል እንመልከት፤

3.1. በየክልሎች ስልጣን ላይ ያሉ በዘር የተደራጁ ሃይሎች የፖለቲካ ምህዳር የማጥበብ ሚና

በስልጣን ላይ ያሉ ክልሎችን እየተቆጣጠሩ ያሉ ሃይሎች ከማንም በላይ የፌደራል መንግስቱ በአንጻራዊነት ያሰፋውን የፖለቲካ ምህዳር የማጥበብ ጉልበቱ አላቸው። የማጥበቡ ስራ በዋንኛነት የሚሰራው በፌደራል ደረጃ በከፍተኛ ደረጃ በመገናኘት የተለያዩ ክልሎች በመወከል በሚሰሩ ከፍተኛ የክልል ባለስልጣናት አይመስልም። እነዚህ ባለስልጣናት፣ ሁሉም ባይሆኑ፣ ሃገርና ህዝብ የገባበትን አደገኛ አጣብቂኝ በመረዳት በግላቸው ስልጣንና ጥቅም፣ በራሳቸው ድርጅት ኪሳራ ጭምር ሃገርና ህዝብን ለማዳን ቆርጠው ለመነሳታቸው ጥርጥር የለኝም። ችግሩ የሚጀምረው ከነዚህ ባለስልጣናት ቀጥሎ በሚመጣው የስልጣን እርከን ላይ በተቀመጡት የየክልሉና የየዞኑ ሃላፊዎች መውረድ ስንጀምር ነው።

የለውጥ ሃይሉ በፌደራል ደረጃ መፈጸም ከሚችለው ጉዳዮች ውጭ የለውጥ ህልሙን በክልሎች ማስፈጸሚያ መሳሪያ የለውም ወደሚል መደምደሚያ ያደረሰኝ ይህ ትዝብት ነው። በፌደራል ደረጃም ቢሆን የለውጥ ሃይሉ የሚፈልገውን ማስፈጸም የሚያስችል በቂ በተለያዩ ሙያዎችና ክህሎቶች የሰለጠነ የሰው ሃይል አቅም ያለው ለመሆኑ እርግጠኛ ሆኖ መናገር አይቻልም። አቅም የጉልበት ጉዳይ ብቻ አይደለም። የለውጥ መሪዎቹን ሰፊና ጥልቅ ራእይ መገንዝብና በተግባር ለመተረጎም የሚያስችል እውቀት፣ ክህሎት፣ ስብእና እና የሞራል ልቀት ያለው የሰው ሃይል መኖሩን ነው የምጠራጥረው። ሃገሪቱ ባለፉት 40 አመታት በተለይ ደግሞ ባለፉት 27 አመታት ማህበራዊ ምሁራዊና ሞራላዊ ካፒታሏ ክፉኛ ሲደቅ የነበረባቸው ዘመናት እንደነበሩ ልብ ይሏል። ይህ የስብአዊ ካፒታል ወፍጮ ፍጥነቱን ጨምሯል እንጂ አልቀነሰም።

ከላይ ስለፌደራል መንግስቱ ያልኩት እንዳለ ሆኖ ትልቁ የለውጡ እንቅፋት ያለው በወሳኙ የፖለቲካ ስራ መስሪያ መድረክ በሆነው በክልል ውስጥ ነው። ክልሎች የፖለቲካ ምህዳሩን ለማጥበብ የሚገለገሉበት ከፍተኛ ትጥቅ፣ የመንግስት ሃብት፣ የአስተዳደር ስልጣን በጃቸው እንዳለ በተደጋጋሚ ገልጫለሁ። የየክልሉ የስልጣን ባለቤቶች፣ የክልሉ ገዥ ፓርቲዎች በመሆናቸው የክልሉን ሙሉ አቅም ፓርቲያቸውን ከማናቸውም ተቀናቃኝ ሃይሎች ለመከላከል ይጠቀሙበታል።

እነዚህ የክልል ባለስልጣናትና የክልል ገዥ ፓርቲዎች በፖለቲካው መስኩ ሁለት ተቀናቃኞች ይታዩዋቸዋል። አንዱ ተቀናቃኝ “የዘር ፖለቲካ ከጦርነት፣ ከረሃብ፣ ከስደት፣ ከመፈናቀል፣ ከመዘረፍ፣ ከመብት መገፈፍ፣ አላዳነህም ወደፊትም ለከፋ መከራ ይዳርግሃል ከመከራህ መውጫው ብቸኛው አማራጭ ከዘር ነጻ የሆነ የዜግነት ፖለቲካ ነው። በዜግነት ላይ የተመሰረተ አስተዳደር ብቻ ነው።” የሚል አቋም ያለው ማንኛውም የፖለቲካ አካል ነው። ሌላው ተቀናቃኛቸው እነዚህን የስልጣን ባለቤቶችና የገዥውን ፓርቲ መሪዎች “የዘራቸውን ህዝብ ያጠቁና ያስጠቁ፣ የዘረፉና ያዘረፉ ለዘራቸው ህዝብ ምንም አይነት ተቆርቋሪነት የሌላቸው ከሃዲዎች” አድርጎ በመሳል ከህዝብ ነጥሎ በእነሱ እግር መተካት የሚፈለገው ሌላው በዘር የተደራጀ የፖለቲካ አካል ነው።

ባለንበት ወቅት በስልጣን ላይ ያሉ የየክልሉ አካላት እነዚህን ሁለት ሃይሎች ይፈራሉ። በአካባቢያቸው እነዚህን ሁለት ሃይሎች በነጻ እንዲንቀሳቀሱ እንዲያደራጁ የፖለቲካ ስራ እንዲሰሩ ቢፈቅዱ የፖለቲካ ሽንፈት ይከተለናል የሚል ስጋት አለባቸው። የፖለቲካ ሽንፈት ደግሞ መዘዙ ብዙ ነው። ያለችሎታቸው ስልጣን አግኝተው ይኖሩ የነበሩና በዘረፋ ያከበቱት ሃብት የሌላቸው ሌላ ስራ ማግኘት ስለማይችሉ ጦማቸውን ወደ ማደሩ ሊሄዱ ይችላሉ። የረሃብ ስጋት የሌለባቸው ደግሞ በዘረፉት የህዝብ ሃብትና በስልጣን ዘመናቸው በተሰራ ወንጀል የምንጠየቅበት ዘመን ሊመጣ ይችላል ብለው ሊሰጉ ይችላሉ።

በዚህ የተነሳ እነዚህ የክልል ሃይሎች ሁለቱም ተቀናቃኞቻቸውን በክልላቸው ውስጥ በነጻነት እንዳይንቀሳቀሱ የተለያዩ እንቅፋቶች ይፈጥራሉ። በሁሉም ክልሎች ይነስ ይብዛም ይህ እየተፈጸመ ነው። መንግስታዊ ተቋማትን ገንዘብና ንብረትን በሙሉ፣ እንዲሁም በክልሉ ያሉ ሚድያ ተቋማትን በቅጥረኞች የሚዘውሯቸውን ማሀበራዊ ሚድያዎችን ጭምር በመጠቀም ተቀናቃኝ የሚሏቸውን ድርጅቶች እንቅስቃሴ ለማደናቀፍ ሲጥሩ እያየን ነው።

3.2. ክልላዊ የዘር የፖለቲካ ድርጅቶች የፖለቲካ ምህዳሩን በማጥበብ ረገድ ያላቸው ሚና።

በሁሉም ክልሎች በስልጣን ላይ ያለውን በዘር ላይ የተመሰረቱ ፓርቲዎችን የሚገዳደሩ በዘር ላይ የተመሰረቱ ተቀናቃኝ ድርጅቶች ተፈጥረዋል። ይህ ሂደት ከለውጡ በኋላ ተጠናክሮ ቀጥሏል። እነዚህ ተቀናቃኝ ድርጅቶች ባላንጣ አድርገው የሚያዩት በፌደራል ደረጃ ስልጣን ላይ ያለውን የለውጥ ሃይል፣ በየክልሉ ያለውን የክልል መንግስት ገዥ ፓርቲና የዜግነት ፖለቲካ የተሻለው አማራጭ ነው የሚለውን የተፎካካሪ የፖለቲካ ሃይል ነው። በፌደራል ደረጃ ስልጣን ላይ ያለው የለውጥ ሃይል በባላንጣነት የተፈረጀበት ምክንያት ስለሃገራዊነት፣ ስለኢትዮጵያዊ ብሄርተኝነት፣ ስለአንድነት፣ መቻቻል፣ አብሮነት በተደጋጋሚ የሚያስተላላፋቸው መልእክቶች በዘር ላይ ለተመሰረቱ ድርጅቶች እንቅፋት ሊሆን እንደሚችል በመረዳት ነው።

በመላው ሃገሪቱ የሚገኙ በዘር ላይ የተመሰረቱ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ ተቃዋሚ ይሁኑ የገዥው ፓርቲ አካል ድርጅቶች፣ በለውጥ ሃይሉ ላይ የመረረ አመለካከት አላቸው። ቢቻላቸው ይህን ሃይል ገና ከጅምሩ ለመቅጨት ከፕሮፓጋንዳ አንስተው እሰከ አመጽ ለመጠቀም ወደኋላ የማይሉ መሆናቸውን አስመስክረዋል። የምሬታቸው መነሻ የለውጥ ሃይሉ የዘር ፖለቲካን የማምከን እድሉ ትልቅ ነው ከሚል ስጋት ጋር የተሳሰረ ነው። የለውጥ ሃይሉ የሚያቀነቅናቸው አመለካከቶች በዜግነት ላይ ፖለቲካችን ይመስረት ከሚሉ ተፎካካሪ ሃይሎች ጋር ተቀራራቢነት ስላለው ይህን ሃይል የዜግነት ፖለቲካ ከሚያራምዱ ተፎካካሪ ሃይሎች ጋር አዳብሎ ማየት በአንድነት እንዲጠፋ መመኘት፣ በሁለቱ አካላት በጋራ የሚሸረብ ሴራ እንዳለ በማስመሰል የሃሰት ፕሮፓጋንዳ ማሰራጨት በዘር የተደራጁ ተቀናቃኝ ድርጅቶች የሙሉ ጊዜ ስራ ከሆነ ሰንበት ብሏል።

እነዚህን በዘር ላይ የተደራጁ ተቀናቃኝ ቡድኖች በዘር የተደራጀውን ገዥ ፓርቲ ለማዳከም ከክልል ክልል የተለያዩ እርምጃዎች እየወሰዱ ነው። በአንዳንድ ቦታዎች በገዥው ፓርቲ ስር ያሉ አሰተዳደሮችን አፍርሶ በራስ እስከ መቆጣጣርና ጠመንጃ ጭምር ያካተተ እርምጃ የወሰዱ ተቀናቃኝ ድርጅቶች እያየን ነው። ጠመንጃ የሌላቸው በተራ ጉልበትና ማስፈራራት የመንጋ ተቃውሞ በማነሳሳትና በመቀስቀስ አሳፋሪ የሆነ የሃሰት ፕሮፖጋናዳ በማካሄድ በክልሉ ገዥ ፓርቲ ላይ የበላይነት ለማግኘት ጥረቶች ሲያደርጉ ይታያሉ። በአንዳንድ ተቃዋሚዎቹ ለዘብተኛና ስልጡን በሁኑባቸው ቦታዎች ገዥዎች መብታቸውን እንዲያከብሩ ከመጣር ያለፈ ነገር የማይሰሩ እንዳሉ ሳልጠቅስ አላልፍም። እነዚህ ግን በጣም ጥቂቶች ናቸው።

ከነዚህ ከመጨረሻዎች አይነቶች ለዘብተኛ በዘር ላይ የተመሰረቱ ፓርቲዎች በስተቀር በዘር ለተደራጁ የተቀናቃኝ ድርጅቶች ሌላው ጠላት ተደርጎ እየተወሰደ ያለው በዜግነት ፖለቲካ የሚያምነው የፖለቲካ ሃይል ነው። ይህ የፖለቲካ አመለካከትና አስተሳሰብ የያዙ ድርጅቶችና ግለሰስቦች እምነታቸውን ለህዝብ እንዳይገልጹ በማድረጉ ስራ ላይ እነዚህ በዘር የተደራጁ ድርጅቶች በየክልሉ በስልጣን ላይ ካለው ገዥ ፓርቲ ያልተናነሰ ችግር ፈጣሪዎች ሆነዋል።። የዜግነት ፖለቲካ አመለካከት የያዙ ድርጅቶች የመንቀሳቀስ እድል ካገኙ በቀላሉ ባብዛኛው የዘር ፖለቲካው አሳርና መከራ ውስጥ በጨመረው ህዝብ ዘንድ ተቀባይነት ያገኛሉ የሚል ስጋት ወስጥ በመግባታቸው፣ የዜግነት ፖለቲካ የሚያራምዱ ድርጅቶችን እንቅስቃሴ ለማደናቀፍ ተራ ወንጀል እስከ መፈጸም የማይመለሱ መሆናቸው እየታየ ነው።

በዜግነት ፖለቲካ የሚያምኑ ግለሰቦችንና ቡድኖችን ማስፈራራት መደብደብ፣ የንግድ ስራዎቻቸውን ማስተጓጎል፣ ቢሮዎችን መስበር፣ ስበሰባዎችን በተደራጀ መንገድ ማወክ የመሳሰሉ ድርጊቶች በመፈጸም የፌደራል መንግስቱ በአንድ በኩል ለማስፋት እየጣረ ያለውን የፖለቲካ ምህዳር ከመቼውም በከፋና ይፋዊና ህጋዊ ባልሆነ መንገድ እያጠበቡት ይገኛሉ። ሁሉም በዘር ላይ የተደራጁ ተቀናቃኝ የፖለቲካ ድርጅቶች በየክልሉ በተመሳሳይ በተደራጁ ገዥ ፓርቲና አስተዳደሮች ውስጥ ደጋፊ ተባባሪና አባል ስላላቸው በዜግነት ፖለቲካ ዙሪያ የተሰባሰቡ ሃይሎችን ለማጥቃት መንግስታዊ አቅም ሲጠቀሙ ይታያል።

3.3. የፖለቲካ ምህዳሩን በማጥበብ ስራ የተጠመዱ ሃይሎች አደገኛ ቅንጅት

በክልሎች ወስጥ የፖለቲካ ምህዳሩን በማጥበብ ስራ ላይ የተጠመዱ፣ በመሃከላቸው መሰረታዊ ቅራኔዎች

ያሏቸው፣ ነገር ግን እንደ አስፈላጊነቱ የሚስማሙ ሶስት ሃይሎችን እናገኛለን። የመጀመሪያው ሃይል፣ የተጀመረው የለወጥ እንቀስቃሴ የዲሞክራሲ በሩን እስከ ክልል ድረስ ከከፈተው ከያዝኩት ስልጣንና ከዚህ ስልጣን ጋር ያገኘሁትን ተጠቃሚነት በተቀናቃኞቼ ተሸንፌ አጣለሁ የሚል ስጋት ውስጥ የገባው ከላይ በኢህአዴግ ወስጥ ለተጀመረው የለወጥ እንቅስቃሴ ቀና አመለካክት የሌለው የየክልሉን የኢህአዴግን የድርጅትና የክልሉን አሰተዳደራዊ መዋቅር በአብዛኛው የተቆጣጠረው ሃይል ነው። ሌላው ይህን ሃይል አባሮ በቦታው እተካለሁ ብሎ ቀንና ለሊት የሚያልመው በዘር የተደራጀ ሃይል ነው። ሶስተኛው የፖለቲካ ሳይሆን የኢኮኖሚ ጉልበት ያለው ቡድን ነው። ከነባሩ ስርአት ጋር በተለያዩ መንገዶች ተሳስሮ እንደ ወያኔ ባለስልጣናት እንኳን ባይሆንም እንደ አቅሙ ከፍተኛ ሃብት ያፈራና ነባሩ ስርዓት እንዲቀጥል ከፍተኛ ፍላጎት ያለው ሃይል ነው።

አንደኛውና ሶስተኛው የቆየ ወዳጅነት ያላቸው በመሆኑ ለጋራ ጥቅም መቆማቸው የሚጠብቅ ነው። ይሁንና

አሁን እየታዬ ያለውና እጅግ አሳሳቢው ጉዳይ እነዚህ ሶስት ሃይሎች በጋራና በቅንጅት የሚሰሩበት ሁኔታ መከሰቱ ነው። በዘረፋ የከበሩ ባለሃብቶች ከሁለቱም በዘር ከተደራጁ ሃይሎች ጋር በቅርብ በመስራት ገንዘባቸውን ሁለቱም ሃይሎች የፖለቲካውን ምህዳር ለማጥበብ እንዲጠቀሙበት እያደረጉ ነው። እነዚህ ባለሃብቶች በዘረፋ ባከማቹት ሃብት ላይ በመንግስት የተወሰዱ እርምጃዎች ባለመኖራቸው ይህን ከፍተኛ ነዋይ ምንጩ መታወቅ እንዳይችል በሚያደርግ የሽያጫና የስም መዛወር ሂደት እንዲያልፍ እያደረጉት ነው። በግለሰቦች እጅ በዘረፋ የተከማቸ ለከት የሌለው ብር የውጭ ምንዛሪውን ከዚህ ቀደም ታይቶ በማይታወቅ ደረጃ ከኦፊሲያሊያዊ ምንዛሪው በላይ እንዲመነዘር እያደረገው ነው። ቋሚ ንብረቶች እየተሸጡ ወደ ተነቀሳቃሽ ንብረትነት፣ ወደ ዶላርና መኪናነት እየተቀይሩ ነው። እነዚህ ንብረቶች በማእከላዊ መንግስት አይደረስበትም ተብለው መተማመኛ ወደ ሚገኝባቸው ክልሎችና የውጭ ሃገራት በየፈርጃቸው እየተከማቹ ነው።

ይህ መጠነ ሰፊ ህገ ወጥና ከመንግስት ቁጥጥር ውጭ የሆነ ሃብት፣ እነዚህን ባለሃብቶች ሃገር አቀፍ የሆነ መረብ ዘርግተው በተለያዩ ክልሎች የሚታዩትን የመንጋ እንቅስቅሴዎችና ግጭቶች ፋይናንስ አድራጊዎች አድርጓቸዋል። እነዚህ ባለሃብቶች በየክልሉ አስተዳደር ወስጥና በዘር በተደራጁ ተቀናቃኝ ድርጅቶቹ ውስጥ ያሏቸውን ቅጥረኞች በመጠቀም በዜግነት ፖለቲካ ዙሪያ የሚንቀሳቀሱ ሃይሎችን አባላትና ደጋፊዎችን በየክልሉ እንቅስቃሴ እንዳያደርጉ በማድረግና የፌደራል መንግስቱ ያነፈሰው የለወጥ አየር በክልሎች እንዳይነፍስ ወሳኙን ሚና ተጫዋቾች ሆነዋል። እነዚህ ባለሃብቶች እነዛን በዘር ተደራጀተው ‘እኔ ካንተ

በላይ ለዘሬ እቆረቆራለሁ” በሚል ግጭት ወስጥ የሚገኙትን ሁለት ሃይሎች በማስተባበር በኢህአዴግ ወስጥ የተንሳውን የለወጥ ሃይልና የዜግነት ፖለቲካ በሚያራምዱ ሃይሎች ላይ የሚሰነዘሩትን ማናቸውንም ጥቃት በገንዘባቸው አሳላጮች ሆነዋል። ግር የሚለው ነገር ይህን ህገ ወጥ በሆነ መንገድ ተዘርፎ በየሌባው ቤት መጋዘን ተሰርቶለት የተከመረን ህገ ወጥ ገንዘብ ትርጉም አልባ የሚያደርግ እርምጃ ለምን በመንግስት እንደማይወሰድ ብቻ ነው።

ሶስቱ ሃይሎች በዜግነት ፖለቲካ ዙሪያ የሚንቀሳቀሱ ሃይሎችን ክፉኛ ከመፍራታቸው የተነሳ የዜግነት ፖለቲካ አራማጆችን በማጥቃቱ ስራ በግንባር እየተንቀሳቅሱ ነው። በተለያዩ ቦታዎች የክልሉ ባለሃብቶች ፋይናንስ የሚያደጓቸው የመንጋ ፈጥኖ ደራሾች የሌሎችን ድርጅቶችን የፖለቲካ ስብሰባዎች ሲረብሹ፣ ተሰብሳቢዎቹን ሲደበድቡ ንብረታቸውን ሲዘርፉ የክልል አስተዳዳሪዎችና ፖሊሶች ቆመው የሚያዩበትን ሁኔታዎች ታዝበናል። ባሁኑ ሰአት የክልል ባለስልጣናትና በየክልሉ የተሰባሰቡ በዘር ላይ የተመሰረቱ ድርጅቶች የመንደር ጉልበተኞች በተናጠልና በጋር በሚወስዷቸው እርምጃዎች በተለይ በዘር ፖለቲካ የማያምኑ የህብረተሰብ ክፍሎች ከፍተኛ ጥቃት እየደረሰባቸው ነው። አንገታቸውን ደፍተው የሚኖሩበት ሁኔታ ተፈጥሯል።

በመጀመሪያ የለውጡ ወራቶች ግራ ተጋብተውና ተደናግጠው በየአካባቢያቸው የዜጎችን ነጻነት መገደብ የተሳናቸው የየክልሉ ባልስልጣናት ውሎ ባደረ ቁጥር ቀልብ እየገዙ፣ ከመደናገጥ እየወጡ ሲመጡ በየአካባቢያቸው በግርግር ተፈጥሮ የነበረውን የነጻነት ምህዳር ለመዝጋት ጊዜ አልፈጀባቸውም። የዛሬ 6 ወር በተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎች የተፎካካሪ ድርጅቶች ህዝብን ለመድረስ የሚጠሯቸውን ስብሰባዎች መከልከልና ማወክ የማይደፍሩት የየክልሉ ባላስልጣናት ዛሬ ማንንም ሳይፈሩ “በአካባቢያችን ብትደርሱ ወየውላቸሁ” የሚል ማስፈራሪያ እስከማስተላለፍ ደርሰዋል።

ቀደም ብዬ እንደጠቀስኩት ይህን ማስጠንቀቂያ ተፈጻሚ ለማድረግ ከሚቀናቀኗቸው ሌሎች የዘር ድርጅቶች ጋር ሳይቀር ለዚህ እኩይ አላማ በጋራ እሰከማሴር ሲሄዱ እየታየ ነው። የተለያዩ ሰበብ አሰባቦች በማቅረብ በየትኛውም ክልል በተለይ በዜግነት ፖለቲካ ዙሪያ የተደራጁ ሃይሎች መንቀሳቀስ የማይቻሉበት ሁኔታ ፈጥረዋል። ማስፈራራት፣ ዱላ፣ ዘረፋ፣ እስራት መንግስታዊ የደህንነት ጥበቃና ማናቸውንም መንግስታዊ አገልግሎት መከልከል በተግባር የዋሉ አንገት ማስደፊያ እርምጃዎች ናቸው። ለህክምና የሄዱ ዜጎችን “የኛን ዘር ፖለቲካ አራማጅ ብትሆን ኖሮ እናክምህ ነበር” በማለት በሽተኛን የህክምና አገልግሎት እስከ መከልከል የደረሰ የሰብአዊ መብት ገፈፋ በሃገራችን ዜጎች ላይ እየተፈጸመ ለመሆኑ በደሉ የደረስባቸውን ግለሰቦች በማስረጃነት ማቅረብ ይችላል።

የለውጡ እንቅስቃሴ እውን ነው ብለው በማሰብ ቀደም ባሉት የለውጡ ወራት እውነተኛ የፖለቲካ እምነታቸውን በአደባባይ የገለጹ ዜጎች ልክ ከምርጫ 97 ማግስት እንደሆነው ሁሉ በየክልሉ ተለይተው ጥቃት እየደረስባቸው እንደሆነ ይታወቃል። ሰልፍ ወጥታችኋል፤ ቲ-ሸርት ለብሳችኋል፤ ህዝብ ቀስቅሳችኋል፤ በተደራጀ መንገድ ተንቀሳቅሳችኋል፣ ገንዝብ አዋጥታችኋል በሚሉ ውንጀላዎች ዜጎች ብዙ መከራ እየተቀበሉ ነው። በነዚህ ዜጎች ላይ የደረሰውን ጥቃት የተመለከቱ ተመሳሳይ የፖለቲካ አመለካከት ያላቸው የክልሎች ኗሪዎች ተመልሰው “ፖለቲካና ኮረንቲ በሩቁ ነው” የአፈና ዘመን እሳቤ እየተመሩ የዜግነት መብታቸውን በጉልበተኞች አስገፍፈው በውርደት መኖሩን ተያይዘውታል።

በማስፈራሪያ ምክንያት ተወልደው ካደጉበት መንደራቸው የተፈናቀሉ፣ ንብረታቸውን የተቀሙ ለሌሎች

መቀጣጫ እንዲሆኑ የታሰሩ፣ የተደበደቡ ዜጎችን እያየን ነው። ከአዲስ አበባ ውጭ ባሉ፣ በተለይ በበርካታ የኦሮሚያና የደቡብ ከተሞችና ገጠሮች ፍራቻ ነግሷል። ለውጡ በፈጠረው እፎይታ ወደ ሃገራቸው የተመለሱ በርካታ የዳያስፖራ አባላት በአንዳንድ የሃገሪቱ ገጠሮች የሚኖሩ ቤተሰቦቻቸውን ሄደው እንዳይጠይቁ “አትምጡ” የሚለው ምክር የሚመጣው ከቤተሶቻቸው ሆኗል። “እዚህ ያለው ሁኔታ ስለማያስተማምን ከአዲስ አበባ አትንቀሳቀሱ እኛ እንመጣለን” እየተባሉ ነው። በፖለቲካ አመለካክታቸው በዳያስፖራ የሚታወቁ ዜጎችና ቤተሰቦቻቸው የዚህ ስጋት ሰለባ ሆነዋል።

በየጊዜው ከፌደራል መንግስቱና በየክልሉ በሚገኙ ጥቂት አርቆ አሳቢ የክልል ባለስልጣናት በኩል የሚደረጉ ጫናዎች ባይኖሩ በሁሉም ክልሎች ከአዲስ አበባ በስተቀር የመንግስትን ጥሪ አክብረው ወደ ሰላማዊና ህጋዊ ትግል የተመለሱ ድርጅቶች በየትኛውም ክልል አንድ ጋት መራመድ የሚችሉበት ሁኔታ እንደማይኖር ግልጽ ሆኗል። ይህ የማእከላዊ መንግስት ጫና በየትኛዎቹ ክልሎች በምን ያህል ደረጃ ተፈጻሚ ይሆናል፣ ምንስ ያህል አስተማማኝና ቀጣይነት አለው ለሚለው ጥያቄ በድፍረት መልስ መስጠት የሚችል አካል ያለ አይመስልም።

4. ማጠቃለያ

ኢትዮጵያ ብዙ ችግሮች የተሸከመች ሃገር ናት። ከዘመን ዘመን ችግርቿ እየበረቱና እየተወሳሰቡ የሚሄዱ ሆነዋል። በየዘመኑ ህዝብ ከዚህ የከፋ ዘመን ሊገጥመው አይችልም እየተባለ እዚህ ደርሰናል። ያሁኑንም ዘመን በዚሁ ቋንቋ መግለጽ ጀምረናል። ይህ አገላለጽ የተለመደ በመሆኑ ይህ ዘመን ካለፉት ዘመናት ልዩነት የሌለውና እንዲያው ዝም ብለን ችግሮችን የምናጋንን ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል። በበኩሌ ግን “የዚህን ዘመን ችግሮች እንደ ሌሎች ዘመን ችግሮች እንደዋዛ ማለፍ ግዙፍ ታሪካዊ ስህተት ብቻ ሳይሆን ከዛም አልፎ ታሪካዊ ወንጀል ከመፈጸም የሚለይ አይሆንም” ባይ ነኝ። የለውጥ ሃይሎች የምንላቸው ቡድኖች ወደ መድረክ ብቅ ከማለታቸው በፊት ሃገሪቱ እየተጓዘች የነበረችበትን የገሃነም መንገድ መለስ ብሎ ማስተዋል ያስፈልጋል።

ያንን የገሃነም መንገድ እንድትጀምረው ያደረጓት መሰረታዊ ችግሮች፣ ከፖለቲካ ከኢኮኖሚ ከማህበራዊ ጉዳዮች ጋር የተሳሰሩ መሰረታዊ መዋቅራዊ ችግሮች ስር ሰደውና ተወሳስበው የቀጠሉበት ሁኔታ እንጂ የተቀነሱበት ሁኔታ የለም። የገሃነሙን መንገድ ለጊዜው የዘጋው ለውጡ በብዙሃኑ ውስጥ በተለይ ወጣቱን ጨምሮ የጫረው ተስፋ ብቻ ነው። ይህ ተስፋ ግን በጊዜ ተጨባጭ ችግሮች በመፍታት ካልተደገፈ ለነፋስ እንደተጋለጠ ዱቄት ብን ማለቱ የማይቀር ነው። ሃገራችናን ህዝቧን ከመቀመቅ አፋፍ የመለሰውን ተስፋ ለማስቀጠል ግን እንዲሁ በዋዛ ፈዛዝ የሚቻል አይደለም።

5. ካለንበት ቅርቃር እንዴት እንወጣለን?

• ያለንበት ሁኔታ እጅግ ልዩና አሳሳቢ መሆኑ መገንዝብ የመጀምሪያው የመፍትሄ እርምጃ ነው (extraordinary-challenges)

• ከዚህ ልዩና አሳሳቢ ሁኔታ ለመውጣት መወሰድ ያለባቸው እርምጃዎች ልዩና በሚገባ የታሰበባቸውና አፋጣኝ ሊሆኑ እንደሚገባ መገንዘብ ሁለተኛ የመፍትሄ እርምጃ ነው። (solving these extraordinary challenges demands taking extraordinary measures)

• ሃገሪቱ የገጠማትን ችግሮች ለመፍታት ከቆየው የአመለካክት የአደረጃጀት እስር ቤት መውጣትና አስፈላጊ ሆኖ በሚገኝበት ወቅት ስር ነቀል እርምጃ ለመውሰድ መዘጋጀት ይገባል።

• በመግቢያው ለመጥቀስ እንደሞከርኩት የሃገሪቱ ህዝቦች ችግሮች በተለያዩ ዘርፎች የሚታዩ ቢሆኑም በቅድሚያ በዋንኛንት በፖለቲካ ዘርፉ የሚታዩ ችግሮች ሳይፈቱ ሌሎችን ችግሮች መፍታት እንደማይቻል መገንዝብ ከሃገራችን የፖለቲካ እውነቶች ሁሉ ቁንጮው እውነት መሆኑን መረዳት፣ ሶስተኛውና ወሳኙ እርምጃ ነው።

• የፖለቲካ ችግሮች ከምንላቸው መሃል ደግሞ ዋነኛው ችግር ከዘር ፖለቲካ ጋር ተሳሰሮ በሃገር የተረጋጋ ህልውና ዙሪያ ያሰፈሰፈው ችግር መሆኑን መቀበል ሌላው የእውነቶች ሁሉ እውነት ነው።

• ኢትዮጵያውያን እንደ አንድ የፖለቲካ ማህበረሰብ ካልሆነ በስተቀር በሌላ መልኩ ተገነጣጥልው በብዙ አዳዲስ ሃገራት ኗሪዎች ሁነው፣ በሰላም የሚኖሩባቸው ግዛቶች ሊኖሯቸው ከቶውኑ የማይችል መሆኑ መረዳት ሌላው ወሳኝ ነጥብ ነው።

• ኢትዮጵያን እንደሃገር ማስቀጠል የወያኔ ህገ-መንግስት ሊነግረን እንደሚሞክረው የተለያዩ ብሄረሰቦቿ መልካም ፈቃድ ላይ የተመሰረተ የምርጫ ጉዳይ አለመሆኑን፣ አንድነት ምርጫ የሌለው የህልውናቸን መሰረት መሆኑን መረዳት ሌላው ትልቅ ጉዳይ ነው።

• ኢትዮጵያ በምንላት ሃገር ወስጥ መከበር የማይችሉ የማህበረሰብ መብቶች ኢትዮጵያ የምትባል ሃገር በሌለችበት ሊከበሩ ቀርቶ ሊታሰቡ የማይችሉ፣ የመብት ዋስትና ሳይሆን ውሎ የማደር፣ ስጋ ከነፍስ አጣብቆ የመኖር ዋስትና የሚጠፋበት ምድራዊ ሲኦል ውስጥ ሁላችንም እንደምንወረወር መረዳት ብልህነት ነው።

• በሃገር አንድነትና በሃገር ህልውና በዴሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታና ድህነትን በማስወገድ ሰብአዊ መብት በማስከበር ሙስናን በማጥፋት ህልማቸን ላይ ትልቅ አደጋ እንዲያንዣብብ ከአደረጉት ምክንያቶች ሁሉ ትልቁና ዋንኛው የዘር የፖለቲካ አደረጃጃት ወይም የዘር የክልል አደረጃጃት ሳይሆን (ይህ ለጊዜው በሁለተኛ ደረጃ ሊታይ የሚገባውና ዋንኛው ችግር ከተፈታ በኋላ እንደ አስፈላጊነቱ ሊነካካ የሚችል ነው) የማእከላዊ መንግስትን ስልጣንና ሃላፊነት መጋፋት የሚያስችል ለአያንዳንዱ በዘር ለተደራጀ ክልል የራሱ አመጽ መፈጸሚያ የታጠቀ ሃይል እንዲኖረው ወያኔ የወሰነው ውሳኔ ነው። ይህንንም ውሳኔ ወያኔ ሲወስን ቅድሚያ የሰጠው በሃገርና በህዝብ ላይ መሪዎቹ ለሚፈጽሙት ወንጀል ራሳቸውን ከተጠያቂነት ለማምለጫ በመሳሪያነት ሊገለገሉበት ስላሰቡ እንጂ የብሄረሰቦችን መብት ለማስጠበቅ ወይም ለሃገር ይበጃል በማለት እንዳልሆነ ባለንበት ወቅት እየፈጸሙት ባለው ድርጊታቸው መረዳት እንችላለን። በየትኛውም በአለማችን ውስጥ በተዘረጉ የፌደራል ስርአቶች፣ የፌደራል መንግስቱን ስልጣን ሊጋፋ የሚችል የክልል ታጣቂ ሃይል እንዲደራጅ ተፈቅዶ አያውቅም። የፌደራሊዝም አንዱ የአስተዳደራዊ ስርአቱ መገለጫ በአመጽ መሳሪያ ባለቤትነትና ተጠቃሚነት እንዲሁም በውጭ ጉዳይ የፌደራል መንግስቱ የስልጣን ሞኖፖል ፍጽም መሆኑ ነው።

በመሆኑም ይህን አመጽ የመፈጸም ማናቸውንም ሃይል ሙሉ በሙሉ ከክልሎች እጅ አውጥቶ በፌደራል መንግስቱ እጅና እጅ ብቻ ማድረግ የወቅቱ ብቸኛና ትልቅ ሃገራዊና ህዝባዊ ጉዳይ ነው። ይህን ማድረግ ከተቻለ፣ በፌደራል መንግስቱ ስር በሚዋቀሩ ነጻና ገለልተኛ ተቋማት አማካይነት በመላው ሃገሪቱ ሰላምና መረጋጋት ማስፈን፣ የህግ የበላይነትን፣ የዜጎችን ሰብአዊ መብቶች ማስከበር፣ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ማድረግ፣ ሙስናን መግታት፣ በሁሉም የሃገሪቱ ክልሎች እርስበርሱ የተቆላላፈና የተመጣጠነ ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት ማስመዝገብ፣ ከውጭ ጠላቶች ጣልቃ ገብነት ራስን በቀላሉ መከላከልና ሌሎችንም የለውጥ ሃይሉንና የህዝቡን ቀና ህልሞች ማሳካት ይቻላል።

• አሁን እየታየ እንዳለው በፌደራል መንግስቱ የለውጥ አካላት ዘንድ እየታሰበ ያለውን ሃገር የማዳን፤ ዴሞክራሲያዊ ስርአት የመገንባትና በፍጥነትም ሌላውን ቀውስ ፈጣሪ ድህነትን ለመወጋት እንዳንችል እያደረገን ያለው ችግር የፌደራል መንግስቱ አቅመ ደካማነት መሆኑን መካድ አንችልም። ከተናጠል ክልሎች ብቻ ሳይሆን ከሁሉም ክልሎች ይበልጥ የሁሉንም ዜጎች መብቶችና ጥቅሞች በሁሉም የሃገሪቱ ክልሎች ያለምንም ተገዳዳሪ በእኩልነት ማስጠበቅና ማስከበር የሚችልበት አቅም ሊኖረው የሚገባው ማእከላዊ መንግስት ህገ መንግስታዊ ስልጣኑን በአንዳንድ ክልሎች ተግባራዊ ማድረግ የሚያስችል አቅም የሌለው ሆኖ መገኘቱ ነው ዋናው የሃገራችን የጊዜው የፖለቲካ በሽታ ።

• በሃገራችን ሰላም እንዲሰፍን ሁሉም ዜጎች በየትኛውም የሃገሪቱ ክልል መብታቸው ተከብሮ፣ በማናቸውም የዜጎች እንቅስቃሴ ባለሙሉ የመብቶች ባለቤቶች ሆነው እንዲንቀሳቅሱ የሚያደርግ፣ ሁሉም ዜጎች ፍትህን ዴሞክራሲን ነጻነትን በእኩልነት እንዲቋደሱ ማድረግ የሚቻለው፣ ማህበረሰቦች ከወል ተፈጥሯዊ መብቶችቻቸው (ይህ መብት እርስ በርስ መባላትን የሚጨምር መሆኑ መታወቅ አለበት) ቀንሰው እነዚህ መብቶች መከበር የሚችሉበትን ብቸኛው የፌደራላዊ መንግስት ስልጣን ከራሳቸው ስልጣን በላይ ሊሆን እንደሚገባው እንዲረዱ ማድረግ ሲቻል ነው። በየቦታው በወል መብት ስም ለመደፍጠጥ ሲሞከር የኖረው የዜጎች መብት የሃገሪቱ የፖለቲካ ችግሮች ሁሉ መሰረት መሆኑን ይህንን መብት ደግሞ ማስከበር የሚችለው የሁሉም ዜጎች ስልጣን መገለጫ የሆነው ፌደራላዊው ማእከላዊ መንግስት መሆኑን መቀበል ይጠይቃል።

• ይህን ያልተረዳ ካለ እንዲረዳ ማድረግ ይገባል። ከዛም ተሻግሮ በኢትዮጵያ ምድር ማናቸውንም ሰብዓዊ ስልጡን ማህበራዊ ክንዋኔዎችን ለማከናወን፣ የሃገር ህልውና በቅድሚያ ቀጥሎም የዴሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታ መረጋገጥ ወሳኝ መሆኑንና ይህ መፈጸም የሚቻለው በየትኛውም የሃገሪቱ ክልል አመጽ የመፈጸሚያ አቅም በማእከላዊ መንግስትና በማእከላዊ መንግስት እጅ ብቻ መሆን እንዳለበት ዜጎች እንዲቀበሉት ማድረግ ይገባል።

• የኢትዮጵያ ህዝብ በሃገሩ ላይ ያሰፈሰፈውን የመበታተን አደጋ መግታትና ከጥቂት ወራት በፊት የፈነጠቀው የዲሞክራሲ ጮራ እንዳይጨልም ማድረግ የሚቻለው በቅድሚያ ሁሉም ክልሎች በዘር ያደራጁትን ሚሊሺያ፣ ልዩ ሃይል ፤ ደህንነትና ሚድያ በክልሉ በዘር ተደራጅተው ከሚያዙት ሃይሎች እጅ አውጥቶ በሃገሪቱ ማናቸውንም የአመጽ እርምጃ የመውሰድ አቅምና መብትና እንዲሁም የመንግስት የሚድያ ተቋማት የማዘዝ ስልጣን በሙሉ የፌደራል መንግስቱ ብቻ እንዲሆን ሲደረግ መሆኑን ማወቅ ይገባል። እንዴት እነዚህን ተቋማት ባሉበት የባለቤትነት ሁኔታ ነጻና ገለልተኛ ማድረግ ይቻላል ወይ ለሚለው ጥያቄ መልሱ ቀላል ነው። አይቻልም።

• ይህ ወሳኝ እርምጃ በቅድሚያ ሳይወሰድ፣ ወገንተኛ የሆኑ ታጣቂዎችና የሚድያ አውታሮች በክልል መንግስቶችና በክልል ፓርቲዎች እጅ እንዳሉ በሃገራችን ስለምርጫ፣ ስለዴሞክራሲ ግንባታ፣ በፌደራል መንግስቱ ስለሚቁቋሙ ነጻና ገለልተኛ ተቋማት ማውራት ለህጻናት ተረት ከመተረት የተለየ ትርጉም ሊሰጠው አይገባም።

• እንዲህ አይነቱ አይን ያወጣ በሃገር አንድነትና በዴሞክራሲ ስርአት ግንባታ ዙሪያ ያሰፈሰፈ መአት ባለበት ሁኔታ ምርጫው የተያዘለትን የቀን ቀጠሮ ጠብቆ ይደረግ የሚሉ አካላት ይህን አጀንዳ ለምን እንደሚገፉት መረዳት የሚቸግር አይሆንም። መሰረታዊ የሆነ ዴሞክራሲያዊ ሁኔታ በኢትዮጵያ ለመኖር ወሳኝ የሆኑት ሁኔታዎች ፈጽመው በሌሉበት ወቅታዊ ሃገራዊ ሁኔታ ምርጫ ወቅቱን ጠብቆ ይደረግ የሚሉት አካላት የዴሞክራሲ ምህዳሩን በመሳሪያ፣ በጉልበት፣ በዘረፋ፣ በህዝብ ውስጥ ፍርሃት በማንገስ፣ ብጥብጥ በመፍጠር፣ የማእከላዊ መንግስትን ስልጣን በመጋፋት የታወቁ ሃይሎች መሆናቸውን ልብ ማለት ያስፈልጋል። በታፈነ ሁኔታ ምርጫ ቢካሄድ ሃገር በማፍረሱም ይሁን በጉልበት ለሚገኝ የምርጫ ድል ባለቤቶች እንደሚሆኑ የተማመኑ ሃይሎች ብቻ ናቸው በህገ መንግስት ስም ምርጫ ይከበር እያሉ የሚጮሁት።

• ከዚህ በላይ የተቀመጠውን ቁልፍ የፖለቲካ ችግር ለመፍታት በብዙ ነገሮች ዙሪያ በርጋታ በብልሃት ማሰብን በድፍረትና በቆራጥነት መወሰን ይጠይቃል። ቁልፉ ጥያቄ ችግሩ እውነተኛ ችግር መሆኑን አለመገንዘብ ላይ አይሆንም። ችግሩ ትልቅ ውስብስብና አስቸጋሪ፣ የለውጥ መሪው አካል አቅም ደግሞ ደካማ መሆኑ ላይ ነው። ይህን ችግር ለማቃለል በፖለቲካው፣ በህዝብ ግንኙነት፣ በወታደራዊ፣ በዲፕሎማሲ፣ በሰው ሃይልና በሌሎችም ዘርፎች ምን ማድርግ እንደሚቻል ማሰብ ይጠይቃል። በፌደራል መንግስቱ ወስጥ ሆነው ለውጥ ለማምጣት እየደከሙ ያሉት ሃይሎች፤ ለውጡን ለመጻረር ከሚፍጨረጭሩ ማናቸውም ሃይሎች የላቀ እምቅ አቅም አላቸው። እያደር እየቀነሰ ቢሆንም አሁንም ሰፊ የህዝብ ድጋፍ አላቸው። በሚገባ ከታሰበበት ይህን እምቅ አቅም ወደ እውን አቅም ቀይሮ ወደ መፍትሄ ሰጭነት ለመሸጋገር ከባድ አይደለም።

• የተጨባጭ የመፍትሄ እርምጃዎች የመሰረት ድንጋዮች የሚከተሉት ናቸው፤

o የኢህአዴግ ድርጅታዊ መዋቅር ይሁን በዚህ ድርጅት አባላት የተያዙት መንግስታዊ አስተዳደራዊ መዋቅሮችና አባላት ራሳቸው የችግሩ አካል እንጂ የመፍትሄው አካል እንደማይሆኑ መረዳት፣

o የለውጥ ሃይሉ፣ ሰላምና የተረጋጋ ህይወት መኖር በሚፈልገው ህይወቱ እንዲሻሻል በሚሻው፣ እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ባለው የኢትዮጵያ ሕዝብ ዘንድ እጅግ ከፍተኛ ድጋፍ እንዳለው መረዳት ያስፈልጋል።

o የለውጥ ሃይሉና ለውጡን የሚደግፈው ህዝብ በቀጥታ የሚገናኙበት መዋቅራዊ ሰንሰለት በፍጥነት መፍጠር ለውጡን ከአደጋ መጠበቂያ ብቸኛ መሳሪያ መሆኑን መገንዘብ ያሻል። ህዝቡ እንጂ የኢህአዴግ የድርጅት መዋቅር የለውጥ አስፈጻሚው ዋንኛ ኤጀንት አለመሆኑን መቀበል ያስፈልጋል። ህዝቡ የለውጡ ኤጀንት መሆን የሚችልበት ሁኔታ ሲፈጠር ብቻ እንደሆነ ለውጡ መቀጠል፣ የለውጥ ሃይሎቹም ከአደጋ መትረፍ የሚችሉት መሆኑን ማመን ይጠያቃል፣

o ወቅቱ ሃገርን ማዳን ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባበት፣ ሰላምና መረጋጋት ከሁሉም ነገር ሊቀድም የሚገባው የሆነበት፣ የሌሎች ነገሮች ህልማችን በሙሉ ይህ ሁኔታ ሳይረጋገጥ ከንቱ ድካም መሆኑን የተቀበሉ ሃይሎች ሁሉንም ልዩነቶች ወደጎን አሰቀምጠው በዚህ ጉዳይ ላይ እንዲተባበሩ የማድረግ ስራ መስራት የለውጥ ሃይሉ ሌላው ተግባር ነው። የለውጥ ሃይሉ ከማያቁት መልአክ የሚያቁት ሰይጣን ይሻላል በሚል አደገኛ ብሂል የሚመራ ይመስላል። ይህን የለውጥ ሃይል አምነው ወደ ሰላማዊ ፖለቲካ የተመለሱትን ሃይሎች ከማመን የቆየውን በብዙ ነገሮች የተበከለ ድርጅታዊና አስተዳደራዊ መዋቅር ማመን የቀለለው፤ ወይንም ችግር እንዳለው ቢያውቅም እንኳን ከዚያ ውጭ ሌላ መንገድ የለም ብሎ ያመነ ይመስላል። ሰይጣን ሁል ጊዜም ሰይጣን ነው። የለውጥ ሃይሉን አምነው ከገቡት መሃል የለውጥ ሃይሉ ጥረቶች እንዲሳኩ ከልባቸው የሚፈለጉ በርካታ የፖለቲካ ድርጅቶችና ግለሰቦች እንዳሉ በማመን፣ ሁሌም ጥቁር በግ እንደሚኖር ሳንዘነጋ፣ የነዚህን ድርጅቶች በጎ ፍላጎትና አቅም አሟጦ ለመጠቀም መዘጋጀት ያስፈልጋል። ሃገር ለማዳን የለውጥ ሃይሉ ህዝቡና ለውጡን የሚድግፉ ሃይሎች በጋራ መስራት ከልባቸው ወደ ሰላም፤ የህግ የበላይነት፣ የመአከላዊ መንግስት ተደማጭነት እስክንሻገር በጋራ ተባብረውና ተመካክረው የማይሰሩበት ምክንያት ሊኖር አይገባም።

o ሃገሪቱ ያለችበትን ፈታኝ ሁኔታ ለህዝብ ያለምንም መሸፋፈን፣ ሁሉም ዜጋ እንዲያውቀው፣ ዜጎች መንግስት ችግሬን ይፈታልኛል ከሚል ጠባቂነት ወጥተው መንግስት በሚያመቻችላቸው ሁኔታ የአካባቢያቸውን ሰላምና መረጋጋት፣ የመንግስት አገልግሎቶችና የልማት እንቅስቃሴዎች የሚቆጣጠሩና የሚያስፈጽሙ እንዲሆኑ ሁኔታዎችን ማመቻቸት ያስፈልጋል።

o ህዝብን ከታች የጉልበት መሰረት በማድረግ የፌደራል መንግስቱ በእጁ የሚገኘውንና የሚያዘውን የፌደራል መንግስት የጦር፣ የፖሊስ፣ የደህንነት ሃይልና የሲቪል ተቋማት ሁለንተናዊ ብቃት በፍጥነት ማሳደግ የሚያስችል ፈጣንና ቀልጣፋ እርምጃዎች አስቀድሞ መውሰድ ይገባል።

o በተለያዩ የሙያ መስኮች በሃገሪቱ ያለውን ምሁራዊና ሙያዊ አቅም ድክመት ማከም የሚችል ከኢህአዴግ ሳጥን ውጭ ተወጥቶ ምሁራዊና ፕሮፌሽናል አቅም ያለውን ሃገር ወዳድ የሰው ሃይል የማሰባስብ ስራ በተቀላጠፈ መንገድ እንዲሰራ ማስቻል፤ የለውጥ ሃይሉን ያለምንም ወጪና ራስ መቆጠብ ሊያገለግሉ የሚችሉ በመቶ ሽዎች የሚቆጠሩ በከፍተኛ ደረጃ በተለያዩ ሙያዎች የሰለጠኑ ዜጎችን ማግኘት የሚያስቸግረው አይሆንም።

o የለውጥ ሃይሉ በወሰዳቸው በርካታ ዴሞክራሲያዊና ፍትሃዊ ውሳኔዎች የተነሳ ከአለም አቀፍ ማህበርሰቡ ያገኘውን ተቀባይነትና አድናቆት በመጠቀም ራሱ የአለም አቀፍ ማህበረስቡ የሃገሪቱ ችግሮች ናቸው ብሎ ለሚያምናቸው ከላይ የዘረዘርኳቸው ችግሮች እንዲፈቱ የራሱ አስተዋጽኦ እንዲያደርግ በቀላሉ ማድረግ ይችላል።

o እግረ መንገዱን ሃገራቸን በዲፕሎማሲ መድረኩ ሊኖራት የሚገባው ተጸእኖ አድራጊነት ከሚያዳክሙ ነጥቦች ዋንኛው፣ እንዲሁም ለሃገራችን ብሄራዊ ደህንነትና ጥቅም ትልቁ አደጋ በዘር የተሰነጣጠቀ አገር ባለቤቶች መሆናችንን መረዳትና፣ ይህ ችግር ለሃገሪቱ ጠላቶችም ትልቁ የትሮይ ፈረስ እንደሆነ በመረዳት ይህን መሰረታዊ ችግር ማቃለል ዘርፈ ብዙ ፋይዳ እንዳለው በመገንዘብ በዚህ ችግር መፈታት ዙሪያ የጎረቤት ሃገራት ትብብራቸውን እንዲለግሱ ማድረግ በተለይ በዚህ ጉዳይ ዙሪያ የተለየ ድጋፍ ሊያደርጉ የሚችሉትን ሃገራት ለይቶ የተለየ ትብብር መጠየቅ ይቻላል። ባሁኑ ጊዜ ከጎረቤቶቻቸን መሃል ለትብብር ጥያቄያችን አሉታዊ መልስ ሊመልሱ የሚችሉ አለመኖራቸው የለውጥ ሃይሉን ድካም የሚቀንሰው ይሆናል።

o ማእከላዊ መንግስት ስልጣኑን በሃገር ደረጃ በማያወላዳ መንገድ ለማረጋገጥ የሚወስዳቸው እርምጃዎች በሁሉም ግንባር ከሁሉም ጋር በአንድ ጊዜ መፋጠጥን ያስወገደ፣ ቁልፍና ወሳኝ በሆኑት አካላት ላይ ያተኮረ ወሳኝ የመፍትሄ ርምጃ በመውሰድ ችግሮችን ለመፍታት መከፈል ያለበትን የመስዋእትነት ዋጋ የሚያስቀንስ ስትራቴጂ መንደፍ ይገባል።

ከዚህ በላይ የቀረቡት ምክረ ሃሳቦች ጥቅል ናቸው። በመሰረታዊ ጉዳይ ላይ ስምምነት ካለ ማለትም የሁኔታዎች አሳሳቢነትና አሳሳቢነቱን በፈጠሩት ቁልፍ ችግሮች ዙሪያ መግባባት ካለ በሁሉም መስኮች እንዴት ከምክረ ሃሳብ ወደ ድርጊት እንሸጋግራለን የሚሉትን ጥያቄዎች በዝርዝር ማቅረብ በጣም ቀላል ነው።

Related Stories