ማሞ ሌላ መታወቂያው ሌላ፣ ፍየል ወዲህ ቅዝምዝም ወዲያ፣

ነፃ ሃሳብ

4/15/20231 min read

በልዩ ሃይሉ መፍረስ ጉዳይ ላይ መግለጫ የሚሰጡ የመንግስት ባላስልጣናት መልስ መስጠት የሚገባቸው እንዲህ ተጨባጭ ሆነው ለሚወጡ የአማራ ህዝብ ስጋቶች እንጂ የልዩ ሃይል በፌደራል ሰራዊቱ ውስጥ መጠቃለል ለሚያመጣው ሃገራዊ ፋይዳ መሆን አልነበረበትም።

አንዳርጋቸው ጽጌ

እንደ እውነቱ ከሆነ ዛሬ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚታየውን ከቅስም ሰባሪ ድህነትና ከተስፋ መቁረጥ ጋር የተያይዘ የአብዛኛውን ህዝብ የህይወት ምስቅልቅል የሚመለከት፤ እየከፋ የሚሄደውን የሰብአዊ መብት ገፈፋ ለሚያይ፤ በየሰበቡ በመላው ሃገሪቱ በጦርነትና በእብሪተኞች ጥቃት የሚያልቀውን የሚፈናቀለውን የምስኪን ህዝብ ብዛት ለሚያሰላስል፤ የገጠጠ የመንግስት ባለስልጣናትና የቀማኛ ባለሃብቶች የተቀናጀ ዘረፋና የተንደላቀቀ ኑሮ መመዝን ለሚችል፤ በሁሉም የህይወት ዘርፎች ሰር የሰደደውን፣ የማስመሰል፣ የግብዝነት፣ የደንታቢስነትና የመሸዋውድ የከረፋ ባህል በውሉ ላጤነ፤ በሁሉም የመንግስት ተቋማት የተንሰራፍውን እና የተደላደለውን የጉቦ ስርአትና ሰንሰለት ለሚረዳ፤ ፍትህ በባለስልጣናትና እና በባለሃብቶች የተደፈጠጠበትን ሁኔታ ለሚታዘብ፤ ትንሽዬ የሰውነት ስሜት የተረፈው ሃገሩን እና ወገኑን የሚወድ ሰው መፈጠሩን መጥላቱ አይቀርም። የዘመኑ የኢትዮጵያ ፈተና ታላቁ የስነ ጽሁፍ ጀግናችን ጋሼ ጸጋዬ ገብረመድህን፣ አቡነ ጴጥሮስ በፋሽስት ኢጣሊያ እጅ በወደቁበት ወቅት የገቡበትን ሰቆቃ በማሰብ የጻፈውን ድንቅ ግጥም ደግሞ ደጋግሞ እንዲያስበው የሚያደርግ ነው። አቡነ ጴጥሮስ የኢትዮጵያን ውድቀት ከማየት “ምነው በእረኛነት እድሜ አይኔ በጓጎጣት የሎስ” የሚል ስሜት እንዳስተናገዱ ለማሰየት ጸጋዬ የተቀኘው ስንኝ ዛሬ የአንዳንዶቻችን ስሜት መግለጫ እየሆነ ነው። በዚህ ስሜት ውስጥ ሆኖ ብእርን ማንሳት እንዴት ከባድ እንደሚሆን ብዙዎች እንደምትገምቱት ተስፋ አለኝ። እንዲም ሆኖ ነው፣ በወቃትዊ ጉዳይ ላይ ያለኝን እይታ ላጋራችሁ የወሰንኩት።

በርእሱ ያሰቀመጥኳቸው ምሳሌያዊ ንግግሮች አንድ አይነት ትርጉም አላቸው። የመጀምሪያውን ምሳሌያዊ አነጋገር ለመጀመሪያ ጊዜ ነው የሰማሁት። አንድ ወዳጄ እየጻፍኩት ካለው ጉዳይ ጋር የሰነዘረውን አስተያየት የገለጸበት ነው። ምን ማለት እንደሆነ አልገባኝም ነበር። “ፍየል ወዲህ ቅዝምዝም ወዲያ” ማለት ነው ብሎ የተረጎመልኝ ይኸው ወዳጄ ነው። አነጋገሮቹን እንድጠቀም ያስገደዱኝ ከአማራ ልዩ ሃይል ጋር በተያያዘ ከመንግስትና ከመንግስት ደጋፊዎች የሚሰጡ ማብራሪያዎችና መግለጫዎች ናቸው።

የመንግስት ባለስልጣናት፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳድር፣ የመከላከያው ጀነራል አበባው፣ የብልጽግና ፓርቲ ባለስልጣናት፣ የመንግስት የኮምኒኬሽን ባለስልጣናት፣ ወንዱም ሴትየዋም፣ የመንግስት ሚድያዎች፣ የኢቲቪ፣ የፋና፣ የዋልታ ጋዜጠኞች ሁሉም በልዩ ሃይሉ ጉዳይ፣ በተለይ ከአማራ ልዩ ሃይል ጋር በተያያዘ የሚሰጡት አስተያየትና የሚሰሯቸው ፕሮግራሞች አንድ አይነት ናቸው። ይህ አስተያያት ሁሉም በጋራ በሚጋሩት መንደርደሪያ ላይ የተመሰረተ ነው። አሳምሬ ሳቀራርበው፣ መንደርደሪያው የሚቀጥለውን ይመስላል።

“የክልል ልዩ ሃይሎች፣ ህገ መንግስታዊ፣ አይደሉም፣ እነዚህ ሃይሎች ከተፈጠሩ ጀመሮ የሰሯቸው አንዳንድ በጎ ተግባራት ቢኖሩም፣ ክልሎች ከክልሎች የሚዋጉባቸው፣ ከዛም አልፎ ክልሎች ማእከላዊ መንግስቱን በመሳሪያ መገዳደር የሚችሉበትን አደገኛ ሁኔታ በመፍጠር የሰላምና መረጋጋት፣ የሃገር ህልውና ጸር ሆነዋል። በየትኛውም የፌደራል መንግስታዊ አስተዳደራዊ ስርአት የተዋቀሩ ሃገሮች፣ የሃገር መከላከያን መገዳደር የሚችል ትጥቅ ያላቸውን የክልል መንግስታት አይፈቅዱም። የሃገርን ዳር ድንበርና ሉአላዊነትን ማስከበር የሃገር መከላከያ ሰራዊት ስራ ነው። የክልል መንግስታት ውስጣዊ ሰላማቸውን እና የህግ የበላይነትን ለማስጠበቅ ከክልል ፖሊስ በላይ አቅም አያስፈልጋቸውም። ከዚህ በመነሳት ሁሉም የየክልሉ ልዩ ሃይሎች ይፈርሳሉ። አባላቶቻቸው እንደፍላጎታቸው፣ ወደ መከላከያ ወይም የክልሎች ፖሊስ ሃይሎች ይካተታሉ። ያልፈለገም ወደ ሲቪል ህይወት የሚመለሰበት መቋቋሚያ ተደርጎለት ይመለሳል።”

ከዚህ መንደርደሪያ ጋር የማነሳው አንድ ጥያቄ ነው። ይህ የመንደርደሪያ ሃሳብ አሁን በአማራ ክልል ለተነሳው ቀውስ እውነተኛው ምክንያት እንዳልሆነ እየታወቀ ሁሉም በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ የሚሰጡ የመንግስት አካላት ይህን መንደርደሪያ ለምን እንደ ድግምት እየደጋገሙ ይደግሙልናል?

አብዛኛዎቹ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ በተለይ ተፎካካሪ ድርጅቶች የየክልሉ ልዩ ሃይሎች መኖርን አጥብቀው ሲቃወሙ ነበር። ተቃውሟቸው ግን በተመሳሳይ ምክንያት ላይ የቆመ አልነበረም።

በጥቅሉ ግን “ልዩ ሃይሎች የሃገር አንድነት፣ የሃገራዊ ሰላምና መረጋጋት ጸር ናቸው። ልዩ ሃይሎች ተፎካካሪ ፓርቲዎች በየክልሉ በነጻነት የፖለቲካና የድርጅት ስራዎቻቸውን እንዳይሰሩ፣ በየክልሉ ነጻና ገለልተኛ ምርጫ እንዳይኖር የየክልሉን የብልጽግና ፓርቲዎች ወግነው የሚሰሩ አካላት ናቸው።” የሚል አቋም ተፎካካሪ ፓርቲዎች እንዳላቸው ይታወቃል።

ይህ አቋም እንደተፎካካሪው ፓርቲ ምንነት ሲመነዘርም አይተናል። ኢትዮጵያ እንደ ሃገር በአንድነቷ እንድትቀጥል አምረው የሚፈልጉና ይህም አንድነት በእውነተኛ ዴሞክራሲያዊ የፖለቲካ ስርአት ላይ እንዲመሰረት የሚፈልጉ፣ ልዩ ሃይሉን በሃገር አንድነት ብቻ ሳይሆን በዴሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታ ዙሪያም ትልቅ እንቅፋት እንደሆነ አድረገው ያዩታል። እነዚህ አካላት ልዩ ሃይሎች ቢፈርሱ ከብልጽግና በላይ ደስታ የሚሰማቸው እንጂ የሚያዝኑ አይደሉም። እነዚህ በአብዛኛው ራሳቸውን ሀገራዊ ፓርቲ አድረገው ያደራጁ ፓርቲዎች ናቸው።

ከነዚህ ሃገራዊ ድርጅቶች ውጭም የሃገር አንድነት ጉዳይ የሚያሳስባቸው በብሄር የተደራጁ ድርጅቶችም እንደ ሃገራዊ ፓርቲዎች የልዩ ሃይሎችን መፍረሰ ከሃገር አንድነትና በየክልላቸው ማየት ከሚፈልጉት የዴሞክራሲ ምህዳር መስፋት አኳያ ሲፈልጉት የኖሩት ጉዳይ ነው።

ሌሎች ስለኢትዮጵያ አንድነት ደንታ የሌላቸው ጽንፍ የረገጡ የተፎካካሪ የብሄር ድርጅቶች የልዩ ሃይሎችን መኖር ሲቃወሙ የነበረው “የኢትዮጵያን አንድነት ያናጋል” ከሚል አልነበረም። “በክልሎች ውሰጥ በነጻነት ለመንቀሳቀስና ለማደራጀት፣ በምርጫ ወቅትም ለገዥው ፓርቲ በመወገን ዴሞክራሲያዊ ፍትሃዊ ፉክክር እንዳይኖር ልዩ ሃይሎች እንቅፋት ሆነውብናል” ከሚል ነው። እነዚህ ብሄረተኛ ተፎካካሪ ፓርቲዎች በልዩ ሃይል ላይ ያላቸው ተቃውሞ ከሃገራዊ ፓርቲዎች ጋር ተመሳሳይነት ያለው ቢመስልም መሰረታዊ ልዩነት አለው። አክራሪ ብሄረተኞች የሚጠይቁት ሰፊ ሃገራዊ የዴሞክራሲ ምህዳር ያለምን ሃላፊነት አክራር ብሄረተኛ ወይም ዘረኛ አመለካከታቸውን በማሰራጨት ሃገር የመበተን ህልማቸውን ለማሳካት ነው።

ይህ ሃቅ የሚያሳየው እስከዛሬ ድረስ ከብልጽግና ፓርቲና ከህወሃት ውጭ አንድም ሌላ ተፎካካሪ ፓርቲ የልዩ ሃይሎችን በሃገሪቱ መኖር የሚደግፍ እንዳልነበር ነው። እግረ መንገዴን እኔም ብሆን በተለያዩ ጽሁፎቼ ለማስረዳት እንደሞከርኩት እንኳን መሳሪያ የታጠቁ በዘር የተዳራጁ ልዩ ሃይሎች ቀርቶ፣ በዘር በተደራጁ ፓቲዎች የሚታዘዙ የክልል ሚድያዎች እንደማያስፈልጉ፣ ተመሳሳይ ሚድያዎች በሌሎች ሃገሮች በዘር የተደራጁ ታጣቂዎችን በማነሳሳት ህዝብ እንዲተላለቅ የተጫወቱትን አውዳሚ ሚና በማጣቀስ ሞግቻለሁ። ወያኔ በጦርነቱ ወቅት “ድምጸ ወያኔን” የዘር ጥላቻ ለመቀስቀስ እንዴት እንደተጠቀመበት ካየን በኋላ የእነዚህ የክልል ሚድያዎች አደገኛነት መረዳት ከባድ አይመስለኝም። ይህ ማለት የክልል ሚድያዎች አደረጃጀት ሊፈተሽ ይገባዋል ማለት እንጂ በክልሎች ጉዳይ ላይ የሚሰሩ ሚድያዎች አያስፈልጉም ማለት እንዳልሆነ መታወቅ አለበት።

ታዲያ ለምንድን ነው የገዥው ፓርቲና የመንግስት ባላስልጣናትና እንዲሁም በእነዚህ አካላት የሚታዘዙ የመንግስት ሚድያዎች የልዩ ሃይሎችን መፍረስና ወደመከላከያ ወይም የክልል ፖሊስ ተቋማት መካተት ተፎካካሪ ፓርቲዎች ወይም ሌሎች ከመንግስት ውጭ ያሉ አካላት እንደማይፈልጉት አድርገው ለህዝብ በመግለጽ ጊዜያቸውን ሲያባክኑ የምናየው።

በተለይ ችግሩ የተነሳው ከአማራ ልዩ ሃይል ጋር በተያያዘ ስለሆነ እውን የአማራ ህዝብ ሆነ በአማራ ክልል የሚንቀሳቀሱ ድርጅቶች ከልዩ ሃይሉ ጋር በተያያዘ የሚያነሱት ጥያቄ የልዩ ሃይሎችን መፍረስ በተመለከተ የመንግስት ባላስልጣናት የሚያቀርቧቸውን ምክንያቶች ለመገንዘብ ስለተቸገሩ ነው? ልዩ ሃይሎች መፍረስ የለባቸውም ብለው ሰለሚያምኑ ነው? መልሱ የማያወላዳ አይደለም ነው። ለዚህም ነው “ማሞ ሌላ መታወቂያው ሌላ” የሚለው ምሳሌያዊ አነጋገር የመንግስትን ባለስልጣናት ድርጊት ገላጭ ሆኖ ያገኘሁት። ከአማራ ልዩ ሃይል መፍረስ ጋር የተነሳው ተቃውሞ በዋንኛነት ለምን ልዩ ሃይሎች ይፈርሳሉ ከሚል የመርህ ልዩነት ላይ የተመሰረተ ሳይሆን በሚቀጥሉት መሰረታዊ ስጋቶች ጋር የተያያዘ ነው። እነዚህን ስጋቶች እንደ ክብደታቸው መጠን በቅደም ተከተል እንሚቀጥለው ተቀምጠዋል፤

1) ወያኔ በፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት መሰረት፣ ከተሰባብሩና ተተኳሽ ካለቀባቸው ጥቂት ከባድ መሳሪያዎች በስተቀር ሌላ ምንም አይነት ትጥቅ አላወረደም። ይህን ሃቅ አቶ ሬድዋን በግልጽ ለተወካዮች ምክር ቤት ተናግሮታል። አቶ ሬድዋን በከባድ መሳሪያዎች ዙሪያ የተናገረው እውነት ነው። አቶ ሬድዋን በዚህ ንግግሩ ውስጥ ከባድ ያልሆኑ መሳሪያዎች የማስረከቡ ጉዳይ በፕሪቶሪያው ስምምነት ቢካተተም አስቀድመን ይህ እንደማይደረግ እናውቅ ስለነበር የትግራይ መከላከያ ሰራዊት ከከባድ መሳሪያ ውጭ ያለውን መሳሪያ አያወርድም ብሎናል። ይህ ለምን እንደሚሆን ለፓርላማው መግለጫ የሰጠ ባይሆንም ከፓርላማ ውጭ ኢንፎርማል በሆነ መንገድ የሚሰጡ ማብራሪያዎች እንዳሉ ይታወቃል። እነዚህ ማብራሪያዎች በአደባባይ ስላልተነገሩ እዚህ መድገሙ አስፈላጊ አይደለም። ሆኖም ግን አቶ ሬድዋን የሚናገረው፣ በርካታ ሰዎች ጆሮ መድረሱን እንዲያውቀው ማድረጉ ተገቢ ነው። ከዚህ ውጭ የአማራ ልዩ ሃይል መፍረስ ጋር በተያያዘ ውዝግብ ሲነሳ ማብራሪያ ለመስጠት ብቅ ያለው ጄነራል አበባው የችግሩ አንዱ ምክንያት ወያኔ ትጥቁን አለመፍታቱ እንደሆነ ስለገባው፣ ከትጥቅ ጋር የተያያዘው በትግራይ ውስጥ ያለው ሁኔታ፣ አቶ ሬድዋን ከገለጸው ምን የተቀየረ ነገር እንደሌለ እያወቀ ሙሉልባምነት በሌለው መንፈስ ወያኔ ትጥቅ እየፈታ ነው ብሎ ተናግሯል። ይህ ሃሰት መሆኑን እርሱም እኛም እናውቃለን። እኔም ይህን የምለው ከወያኔ ወታደራዊና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ጋር በተያያዘ የማገኘው መረጃ ከየት እንደሚመጣና ትክክለኛ መሆኑን ትልልቆቹ የመንግስት የፖለቲካና ወታደራዊ ባለስልጣናት እንደሚያውቁ ስለማውቅ ነው። አሁንም መሬት ላይ ያለው ተጨባጭ መረጃ ወያኔ ትጥቁን አለማውረዱ ብቻ ሳይሆን ከዚህ ቀደም ባቀረብኩት ጽሁፍ ለማሳየት እንደሞከርኩት በበርካታ ካምፖች ውስጥ ወታደራዊ ልምምድ እንሚያደርግ ነው። በቅርቡ ግን ወያኔ ከዚህ የካምፕ ውስጥ መደበኛ ከሆኑ ከወታደራዊ ዶክትሪን እና ከአካል እንቅስቃሴ ጋር ከተያያዙ ልምምዶች አልፎ፣

ማርች 29 2023 ባገኘሁት መረጃ

አርሚ 44 የተባለው የጦር ክፍል፣ በጎንካ፣ሰበበራ ወጀራት አካባቢ በከባድ መሳሪያ የታገዘ ወታደራዊ ልምምድ ሲያደርግ ነበር።

በቅርቡ በ6 ኤፕሪል 2023

በሃውዜን ፣ ነበለት ፣ወርቃ ኣንባ እንዲሁም በአግበ እሰከ የጭላ ባለው ኣከባቢ ከባለፈው ሰኞ ጀምሮ ከፍተኛ የሆነ ወታደራዊ ሰልጠና መሰጠት ተጀምሯል። በተጨማሪም ከክፍቶ ፣ጋርጃለ፣ታኦ በሚባሉ በአላማጣ ኣከባቢ በሚገኙ ቦታዎች ከፍተኛ ቁጥር ያለው የወኔ ሰራዊት በእዚሁ እለት ገብቷል። እስከ እዚህ እለት ደረስ የወያኔ ታጣቂዎች የፈቱት ትጥቅ የለም። የተሰጣቸው መምሪያ የለም። መረጃዎች የሚያሳዩት የወያኔ ታጣቂዎች በከፍተኛ የሆነ ወታደራዊ ሰልጠና መጠመዳቸውን ነው። ይህ መረጃ እንደጠቆመው ይህ የወያኔ እንቅስቃሴ በማእከላዊ መንግስት እንደሚታወቅ ነው። ወታደራዊ ስልጠና ለምን እንዳስፈለገ ወያኔዎች ለወታደሮቻቸው የሚሰጡት ማብራሪያ ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ ባወጣኋቸው ጽሁፎች እንደገለጽኩት በህወሃት ማእከላዊ ኮሚቴ ስብሰባዎች፣ ከሰላም ስምምነቱ በኋላ በይፋ ሲነገር የነበረው “የሰላም ስምምነቱን ተፈጻሚ ለማድረግ ስምመነቱን ከሚቃወሙ ከአማራና ከኤርትራ ሃይሎች ጋር ለምናደረገው ጦርነት ነው” የሚል ነው።

ከዚህ በተጨማሪ ወያኔ ከተተኳሽ ውጭ ያሉ ወታደራዊ ሎጂስቲክን ከአዲስ አበባ በወያኔ ደጋፊዎች ባላሃብቶች አስተባባሪነት እየተገዙ በአፋር በኩል በመኪና አስከ 100000 ሽህ ብር ጉቦ እየከፈሉ እያስገቡ ነው። ልብስ፣ የፕላስቲክ ኮዳዎች፣ ጫማዎች የጫኑ በርካታ የጭነት መኪናዎች ትግራይ ይገባሉ። የተተኳሽ እጥረት ለማስወገድ ወያኔ ሰፊ የኮንትሮባንድ ግዥ በማካሄድ ላይ ይገኛል። የክላሽ፣ የብሬን ፣የድሸቃ ተተካሽ በኮንትሮባንድ እየተገዛ በአፋር ጉጉውዶ ዳንደ ወደ ሞኮኒ በግመሎች እንደሚገባ መረጃዎች እየወጡ ነው። ከትግራይ የሚወጣው ወርቅ በአዲሳ አበባና በጅቡቲ እያለፈ ዱባይ ውስጥ መቸብቸቡን ቀጥሏል።

ከዚህ በፊት ወያኔ ከትግራይ ውጭ ለሽብር ስራ የመመለመላቸው በሽዎች የሚቆጠሩ ሰልጣኞች እንዳሉ አሳውቀን ነበር። ከእነዚህ ሰልጣኞች መሃል ይሁኑ አይሁኑ ባይታወቅም በርካታ ቁጥር ያላቸው ግለሰቦች በአዲስ አበባ በኩል ወደ ወለጋ በመሄድ ኦነግ ሸኔ እየተቀላቀሉ እንደሆነ፣ በርካታ የሚታወቁ የወያኔ የልዩ ሃይል ኮማንዶ አባላት አዲስ አበባ ውስጥ እየገቡ እንደሆነ፣ የወያኔ ከፍተኛ የመረጃ አባላትም አዲስ አበባ ውስጥ እንዳሻቸው የሚንቀሳቅሱበት ሁኔታ ተፈጥሯል። እነዚህን እና ሌሎች መረጃዎችን መንግስት ቢሰማም ባይሰማም ማድረስ ለሚችሉ አካላት ማስተላለፋችንን አላቆምንም። እነዚህ የወያኔ የሰራዊት አባላት በአዲስ አበባ ወስጥ አንዳንድ እርምጃ እየወሰዱ እንደሆነ የሚያሳዩ መረጃዎች መታየት ጀምረዋል። የበለጠ መጣራት የሚገባቸው መረጃዎች በእጃችን ላይ ይገኛሉ።

ከዚህ ከትግራይ ከሚገኘው መረጃ በተጨማሪም ተመሳሳይነት ያላቸው አስተማማኝ መረጃዎች ከአማራ ክልል እናገኛለን። እነዚህ አይነት መረጃዎች ለምን ከትግራይ፣ ከአማራና ከዛም አልፎ ከኦሮሚያ ክልል ለኔ እንደሚደርሱ አንባቢን ግራ ቢያጋባም ከፍተኛዎቹ የመንግስት ባለስልጣናት ምክንያቱ ምን እንደሆነ ያውቁታል።

ከወያኔ ጋር በተያያዘ ለወታደራዊና የደህንነት ጉዳዮች ቅርበት ካላቸው የአማራ አካላት የሚመጡት መረጃዎች ከትግራይ ከሚመጡት መረጃዎች ጋር ተመሳሳይ ናቸው።

ከአማራ ልዩ ሃይል መፍረስ ጋር በተያያዘ የአማራ ክልል ሲተራመስ በነበረባቸው ቀናት ውስጥ ወያኔ በሌላ በኩል የሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎች ይህን ይመስላሉ።

በሱዳን ግንባር ኣርሚ 27 አርሚ 31 እን አርሚ 70 በስየ አብርሃ እና ሳምሬ ብዱን፣ በበረከት እና በማይካድራ በኩል በረሀውን ይዘዉ ወልቃይት ለመቆጣጠር እቅድ አውጥተው እየተንቀሳቀሱ ነው። የወያኔ የምእራብ እዝ፣ 5ክ/ጦር ማይጠብሪ ለመያዝ በቀኝ እና በግራ እቅድ አውጥቷል። የአማራ ልዩ ሃይል ግን በዚህ ወቅት ተበትኗል።

በሰሜን ጎንደር የሚገኙትን የማይፀምሪ ግንባር 3ቱ ወረዳዎችን እና የወልቃይት ቀጠናዋችን ለመቆጣጠር በማሰብ ጁንታው እራሱ የአደራጃቸውን የወረዳዋችን አመራሮች ሽሬ ላይ አዘጋጅቶ በአሁኑ ሰአት እየተጠባበቀ ይገኛል።

በወያኔዎች ካምፕ እየተነገረ ያለው የፌደራል መንግስት በእነዚህ ማይፀብሪ እና ወልቃይት ግንባር አካባቢዎች በቅድሚያ መከላከያ አስገብቷል፣ ቀጣይ የፌደራል ፖሊስ ያስገባል። ከላይ የተጠቀሱት ቦታዎች በ2ቱ ሰራዊት ከተሸፈነ በኋላ የአማራ ልዩ ሃይል ጠቅሎ እንደወጣ በቀጥታ ትገባላችሁ የሚል ቃል በፌደራል መንግስቱ ተሰጥቶናል የሚል ነው። ጁንታ ተዋጊዎቹን በእዚህ አባባል ተስፋ እንዲሰንቁ አድርጎ በመጪው 3ቀናት ውስጥ ለመግባት ተዘጋጅቶ እየተጠባበቀ ነው።

እንዲህ አይነት ቃል በፌደራል መንግስቱ ይገባላቸው ወይም አይገባላቸው የሚታወቅ ነገር የለም። ሆኖም ጁንታው ለታጣቂዎች “መንግስት በገባው ቃል መሰረት እማይፈፅም ከሆነ በሃይል እንገባለን” የሚል አማራጭ እቅድ እንዳለው ለሰራዊቱ ገልጿል።

ልክ ከትግራይ እንደሚገኘው መረጃ በተመሳሳይ ከወልቃይት ግንባር ከመንግስት የደህንነት ሰዎች የሚመጣው መረጃ፣

“ይህ የጁንታ ታጣቂ የጥፋት ቡድን እስከ አሁኑ ሰአት ድረስ ትጥቅ አልፈታም። እንደ ጁንታ፣ የመጨረሻ ውሳኔው የወልቃይት፣ጠለምት፣ራያ ቦታዋች ካልተመለሱ ትጥቅ አንፈታም በማለት ለጥፋት ተዘጋጅተው ጥፋት ለማድረስ እየተንቀሳቀሱ እንዳሉ ይታወቅ” የሚል ነው።

ቦታዎችን መጥቀስ አስፈላጊ ባይሆንም፣ ልዩ ሃይሉ ለቆ በመሄዱ በመከላከያ ሆነ በሌላ ሃይል ያልተሸፈኑ፣ ወያኔዎች ጦራቸውን ያለምንም ከልካይ ማስገባት የሚችሉባቸው ግንባሮች እየተፈጠሩ ነው። በአንደኛው ግንባር ከዚህ ቀደም የህወሓት ወታደሮች የነበሩትን በጦርነቱ ያልተሳተፉትን በጀሌ ያለ ትጥቅ በምህረት ስም አስገብቷል።

ጁንታው በማይጠብሪ ወረዳ አዲማይዳጉሳ፤ ማይተክሊት ና ሀይዳ የሚባሉ ቦታዋችን፣ በአካሉ አብርሃና ሀጎስ መስፍን በሚባሉ የጁንታው አመራሮች በቁጥጥር ስር አድርጎቸዋል። ይህ ቦታ ማለት የተከዜ ወንዝን ተሻግሮ በግራ ክንፍ፣ ወርቅ ማውጫው ይዞ ለማይጠብሪ ከተማ በቅርብ ርቀት ላይ የሚገኝ ነው።

ከዚህ በተጨማሪ የህወሓት 40 ክ/ጦር የአንገረብ መደማምር ወይም ለሁመራ በቅርብ ርቀት ሸረሪና የሚባለው ቦታ ላይ ተጠግቶ ይገኛል። በተጨማሪም በአዲጎሹ፣ በቁራሪትና ማይጋባ የተከዜ ወንዝን ተፋሰስ ይዞ የተጠጋ ሀይል አላቸው።

ይህን መረጃ ለአማራ ክልል መሪዎች በራሳቸው የደህንነት መዋቅር እንዲደርስ የተደረገ ቢሆንም በጠቅላላ በሃገርና በክልሉ የደህንነት መስሪያ ቤት ዙሪያ የሚታየው መዝረክረክ የሚያሳስባቸው አካላት በኛ በኩል ለክልሉና ለፌደራሉ መንግስት ከፍተኛ መሪዎች እንዲደርሳቸው ይሉኩልናል። ደርሶናል የሚል ምላሽ ባናገኝም ተመሳሳይ መረጃዎችን ባላፉት ሁለት አመታት ስናደርስ ቆይተናል።

የአማራ ልዩ ሃይል መፍረስ ተቃውሞ ያስነሳው አንዱና ዋንኛው ምክንያት የአማራን ህዝብ ካለፉት 50 አመታት በላይ በጠላትነት ፈርጆ ህልቆ መሳፍርት የሌለውን መአት ያወረደበትና ባላፉት ሁለት አመታታ የአማራን ክልል በሶስት ተከታታይ ወረራዎች አማካይነት በመቶ ሽዎች ለሚቆጠሩ አማሮች እልቂት ምክንያት የሆነው፣ ከመነኩሴ እስከ የአራት አመት ሴት ህጻናትን የሚደርሱ የአማራ ሴቶችን ሆን ተበሎ በማእከል በተሰጠ መመሪያ በወታደሮቹ ያስደፍረን፣ ሰውን ብቻ ሳይሆን ገበሬው ዳግም እንዳይንሰራራ የእርሻ በሬዎቹን፣ ላሞቹን በጎቹን፣ የሚበላውን በልቶ፣ የሚያግዘውን አግዞ፣ የተረፈውን በጭካኔ ገድሎ የሄደው፣ በአማራ ክልል ባንኮችና በግለሰብ እጅ የነበሩ ገንዘቦችን፣ የእስልምና እምነት ተከታይ የሆኑ እናቶቻችንና እህቶቻቻን ብራቸውን በወርቅ እየቀየሩ እንደሚያስቀምጡ በማወቅ በመከራ ያጠራቀሙትን የወርቅ ሃብታቸውን የዘረፈ፣ የአማራን ህዝብ ወደ ድንጋይ ዘመን ለመመለስ ትምህርት ቤቶችን ክሊኒኮችን መስሪያ ቤቶችን ሆን ብሎ በማውደም፣ ቁሳቁሶቻቸውን በመዝረፍ፣ መዝረፍ የማይቻሉትን በማውደም የሚታወቀው ወያኔ በፕሪቶሪያው ስምምነት መሰረት ትጥቁን አለማውረዱ ብቻ ሳይሆን ለሌላ ዙር ጦርነት እራሱን እያዘጋጀ መሆኑ ስለሚታወቅ ነው።

በልዩ ሃይሉ መፍረስ ጉዳይ ላይ መግለጫ የሚሰጡ የመንግስት ባላስልጣናት መልስ መስጠት የሚገባቸው እንዲህ ተጨባጭ ሆነው ለሚወጡ የአማራ ህዝብ ስጋቶች እንጂ የልዩ ሃይል በፌደራል ሰራዊቱ ውስጥ መጠቃለል ለሚያመጣው ሃገራዊ ፋይዳ መሆን አልነበረበትም።

2) ሌላው ከአማራ ልዩ ሃይል ጋር በተያያዘ ችግር የፈጠረው ጉዳይ፣ የፌደራል መንግስቱ የወልቃይትና የራያን ጉዳይ እንዴት ሊፈታው እንዳሰበ ግልጽ አለማድረጉ ነው። በወያኔ በኩል በተደጋሚ በውስጥ በስብሰባዎቻቸው ሆነ በአደባባይ የሚናገሩት ግልጽ ሆኗል። የእነዚህ ሁለት ቦታዎች ጉዳይ በህገ መንግስቱ መሰረት እንደሚፈታ ከመንግስት ጋር ተግባብተናል እያሉ ነው። በወያኔ በኩል በህገ መንግስቱ መሰረት ማለት ቦታዎቹ መጀመሪያ በቅድሚያ ወደነበሩበት የትግራይ አሰተዳደር ተመልሰው ከዛ በኋላ በነዚህ ቦታዎች ላይ የሚነሳ የማንነትና የይገባኛል ጥያቄ ካለ በህገ መንግስቱ ይፈታል ማለት ነው። ወያኔዎች ለሰራዊት አባላቶቻቸው ለደጋፊዎቻቸው ደጋግመው ይህን እየተናገሩ ነው። የኢትዮጵያ መንግስትም ከፕሪቶሪያው ስምምነት መሃል ብዙ ተግባራት ቢያከናውንም ካልፈጸማቸው ተግባራት መሃላ የአማራን ሃይሎች ከወቃይትና ከራያ አሰውጥቶ ለትግራይ ማስረከብ እንደሆነ ጌታቸው ረዳ በሌላ ሚድያ ሳይሆን በኢትዮጵያ ቴለቪዥን ላይ ቀርቦ ተናግሯል። በኢትዮጵያ መንግስት በኩል የእነዚህን ሁለት ቦታዎች ችግር በህገ መንግስቱ መሰረት ይፈታሉ ከማለት አልፎ ይህ ማለት ቦታዎቹን ለትግራይ ጊዜያዊ አሰተዳደር ማስረከበ መሆኑን ወይም ሌላ መንገድ እንዳለው ግልጽ አላደረገም። ይህ ግልጽነት የሌለው አቋም ከላይ ከተጠቀሰው የወያኔዎች ትጥቅ አለመፍታት ጋር ተደመሮ የአማራ ልዩ ሃይል እንዲበተን የተደረገው እነዚህ ቦታዎች ለትግራይ ጊዚያዊ አስተዳደር አሳልፎ ለመስጠት ነው ከሚል መደምደሚያ ላይ የአማራን ህዝብ አድርሶታል። በዚህ ላይ አሜሪካኖች ያለማቋረጥ እነዚህ ክልሎች ወደ ወያኔ አገዛዝ መመለስ አለባቸው ብለው መወትወታቸውና የኢትዮጵያ መንግስት ለአሜሪካ ብቻ ሳይሆን ለአውሮፓ መንግስታት ጫና በማጎንበስ እነዚህን ቦታዎች መንግስት ለወያኔ አሳልፎ ሊሰጥ የሚችልበት እድል አለ ብሎ በማሰቡ ህዝብ ስጋት ውስጥ ገብቷል።

ሚዛናዊ ነን ብለው የሚያስቡ ሰዎች የኢትዮጵያ መንግስት በወልቃይትና በራያ ህዝብ ላይ ከጦርነቱ በፊት ብቻ ሳይሆን በጦርነቱ ወቅትም ወያኔ የፈጸመውን ግፍ እያወቀ፣ ይህን አካባቢ መልሶ ለወያኔ አያስረክብም ይላሉ። ከዛም አልፈው በተለይ የኢትዮጵያ መንግስት ወልቃይትን ለወያኔ አሳልፎ በመስጠት ወያኔ ከኢትዮጵያ ጠላቶች ጋር በቀጥታ በመገናኘት ኢትዮጵያን የማወክ፣ ህልወናዋን የማናጋት አቅም ማግኘት የሚችልበትን እድል ሊፈጥር አይችልም በማለት ይከራከራሉ። ሚዛናዊ ነን የሚሉ ግለሰቦች የሚያቀርቧቸውን መከራከሪያዎች የሚያግዝ ምንም አይነት ፍንጭ ከመንግስት ወገን የማይታይ በመሆኑ የአማራ ህዝብ፣ መንግስት በቅድሚያ የአማራ ልዩ ሃይልን ወደማፍረስ የሄደው እነዚህን ቦታዎች ለወያኔ ሲያስረክብ ከአማራ ህዝብ ተቃውሞ እንዳይገጥመው ነው የሚል እምነት እንዲኖረው አድርጓታል። የመንግስት ባለስልጣናት ከልዩ ሃይሉ መፍረስ ጋር በተያያዘ ማብራሪያ ሊሰጡበት የሚገባ ጉዳይ የወልቃይትና የራያ ጉዳይ ነው። በዚህ ጉዳይ ላይም አንዲትም ቃል አይተነፈሱም።

3) ባላፉት 5 አመታት በአማራ ክልል ወስጥና ከአማራ ክልል ውጭ የሚኖረው የአማራ ህዝብ በአብዛኛው ህይወቱ ያለፈው ንብረቱ የወደመው በማንነቱ እየተለዬ የአማራ ተወላጅ እንደሆነ የአማራ ህዝብ ያውቃል። በተለይ በወለጋ ወስጥ እጅግ አሰቃቂ በሆነ ደረጃ የዘር ማጽዳት ስራ በአማራው ላይ እየተሰራ እንደሆነ ይረዳል። ከዛም አልፎ ወያኔ ያስታጠቃቸው ያደራጃቸው ከወያኔ ጋር እጅና ጓንት ሆነው የሚሰሩ፣ የቅማንት፣ የአገው፣ የኦነግ ሰራዊቶች በአማራ ክልል ውስጥ የክልሉን ሰላም በማደፍረስ፣ አማራን በማንነቱ ለይተው በአሰቃቂ ሁኔታ በመግደል ማለቂያ ለሌለው ስቃይ ህዝቡን እንደዳረጉት ያውቃል።

በትናንትና እለት ብቻ 05/08/2015 ዓ/ም ከምሽቱ 12.25 ጀምሮ ሰአት ከኦረሞ ብሄረሰብ ዞን ጅሌ ጥሙጋ ወረዳ ጓዳ ፣በጤ፣ገርቢ ባልጪ እና ኤፍራታ ግድም ወረዳ ጀውሀ ቀበሌዎች የኦሮሞ ታጣቂዎች አማራ ሲቪል እና የልዩ ሃይል አባላትን ተሳፋሪዎችን ከመኪና እያስወረዱ እጅግ አሰቃቂ በሆነ ሁኔታ እየገደሉ ነበር። መከላከያ ወደ ቦታው ገብቶ እያረጋጋ ቢሆንም አሁንም ችግሩ ሰፊ ቀበሌ የሚሸፍን ስለሆነ እንዳልቆመ ታውቋል።

ወያኔ ትጥቁን ባልፈታበት ከእነዚህ አካላት ጋር እጅና ጓንት ሆኖ እየሰራ ባለበት፣ ትግራይ ውስጥ ለእነዚህ ሃይሎች ማሰልጠኛ ይሆን ዘንድ የከፈታቸውን ካምፖች ባልዘጋበት፣ ስልጠና መስጠት ባላቆመበት ወቅት፣ የአማራን ህዝብ በዚህ መንገድ እስከጥርሳቸው ከታጠቁ ሃይሎች ጋር የሚያደርገውን የራስ መከላከል ስራ የሚሰራለት ልዩ ሃይል ይፍረስ ሲባል የአማራ ህዝብ መቆጣቱ ማንም ሊያስገርም አይገባም ነበር። የመንግስት ባለስልጣናት ማብራሪያ መስጠት ያለባቸው፣ የአማራ ህዝብ ከክልሉ ውጭና በክልሉ ውስጥ የሚሰማውን የደህንነት ስጋት እንዴት እንደሚቀርፉለት ሊሆን ሲገባው ከክልሉ ልዩ ሃይል መፍረስ ጋር ህዝብን ባላሳሰበው ጉዳይ ላይ ማብራሪያ መስጠት ባልተገባቸው ነበር።

4) ሌላው ህዝብን ግራ ያጋባውና የአማራ ልዩ ሃይል መፍረስና በመንግስት በኩል በተከታታይ ከአማራ ክልል ጋር በተያያዘ ማእከላዊ መንግስቱ የሚያቀርባቸው ስጋቶች መገጣጠማቸው ነው። “ከአማራ ክልል በርካታ አሸባሪዎች ወደ አዲስ አበባ ከተማ እየገቡ ስለሆነ ነው መንገድ የምንዘጋው፣ በአመጽ ስልጣናችን ለመቀማት የሚደራጁ የአማራ አካላት አሉ ወዘተ” የሚሉ አባባሎችና የአማራ ልዩ ሃይል መፍረስ መጋጠማቸው፣ የልዩ ሃይሉ መፍረስ የመንግስት ባላሰልጣናት እንደሚሉት ለስልጣናቸው ካላቸው ስጋት እንጂ አንድ ጠንካራ የመከላከያ ሃይል ከመገንባት ጋር የተያያዘ አይደለም የሚል ጥርጣሬ በህዝቡ ውስጥ ፈጥሯል። መንግስት በደጋፊዎቹ በኩል እንዲወጣ ያደረገው እስር ቤት የጨመራቸው ሁለት ግለሰቦች የስልክ ልውውጥ ልዩ ሃይሉን መንግስትን ለመገልበጥ ለሚያሴሩ አካላት መጠቀሚያ ለማድረግ የሚፈልጉ ሰዎች እንዳሉ ለማሳየት ይጠቅመኛል ብሎ ነው እንደሆነ ግልጽ ነው። የስልክ ልውውጡ ችግር፣ እውነተኛነቱ ቢረጋገጥም እንኳን መንግስት ልዩ ሃይሉን እንዲፈርስ ወስኛለሁ ካለበት ምክንያት ጋር ስለማይገናኝ የመንግስትን ተአማኒነት የሚቀንስ እንጂ የሚጨምር አይሆንም። በመንግስት በኩል ማብራሪያ የሚያስፈገው ልዩ ሃይሉን በመሳሪያነት ሊጠቀሙበት የሚፈልጉ ጥቂት አካላት ሊኖሩ እንደሚችሉ ቢታወቅም ልዩ ሃይሉ እንዲፈርስ የተወሰነው በዚህ ምክንያት እንዳልሆነ የበለጠ ግልጽ በማድረግ ሌሎችን የአማራን ህዝብ ስጋቶች እንዴት እንደሚያቃልላቸው ማብራራት ነበር። አልተደረገም።

5) ሌላው፣ ህዝብን ከአማራ ልዩ ሃይል መፍረስ ጋር ጥርጣሬ ወስጥ እንዲወድቅ ያደረገው ምክንያት ሞራል አልባ የሆነው የወቅቱ ፖለቲካ ነው። ከምክንያትና ከእውነት የተጣላ ፖለቲካ የአለም የፖለቲካ መገለጫ እየሆነ እየሄደ እንደሆነ ባውቅም፣ ለጊዜያዊ ይሁን ለዘለቄታ የፖለቲካ ጥቅም ሲባል በፖለቲካ ውስጥ ብዙ አይነት ኢሞራል የሆኑ ነገሮች እንደሚሰሩ ባውቅም፣ ባሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ እየታየ ያለው በየትኛውም መመዘኛ ዝቅጠቱን ማሳነስ የማንችለውን የመሰለ የፖለቲካ አመለካካትና ድርጊት አንብቤም ወይም ሰምቼው አላውቅም። ይህን ኢሞራል የሆነ የሃገራችን ፖለቲካ ጉዳይ ከአማራ ህዝብ የደህንነት ስጋትና ከልዩ ሃይሉ መፈረስ ጋር የተያያዘ ባይሆን ኖሮ በሰፊው ልመለከተው ያሰብኩት ጉዳይ ነበር። ቢሆንም ትንሽ ማለቱ አስፈላጊ ሆኖ አግንቸዋለሁ።

ወያኔዎች በእብሪት የጀመሩት ጦርነት ከሚሊዮን በላይ የሃገሪቱ ዜጎች ህይወት እንዲቀጠፍ አድርጓል። ያስከተለው የስብእና መራከስ የሚዘገንን ነው። የምናያቸው ነገሮች ግን እጅግ የሚያስደነግጡ እየሆኑ ነው። ጉዳዩን ለማስረዳት አንድ የስበእና መራከስ የሚያሳይ ምሳሌ ላንሳ። “የተከዳው የሰሜን” እዝ ከሚለው መጽሃፍ የተወሰደ ነው። ወያኔዎች “ ከገደሏቸው ውስጥ የአ/አለቃ ስንታየሁ አገዳደል እውነተኛው አኖሌ ነው። መጀመሪያ ጡቶቹና ቆረጡ። ቀጥሎ አንገቷን ቆረጡ። አንገቷን እና ጡቷን ዛፍ ላይ አንጠለጠሉ። ይህ ሲያደርጉ እጅ የሰጠው ሰራዊት ያያል።” ጸሃፊው እንደነገረን ይህን የፈጸሙት የትግራይ ልዩ ሃይል አባላት/ የትግራይ መከላከያ አባላት ናቸው። ወደ ኤርትራ ያፈገፈገው ሰራዊት ከቀናት በኋላ እንደገና ተደራጅቶ ወደ ትግራይ ሲመለስ የአ/አለቃ ስንታየሁ ጡቶችና ጭንቅላቷ እዛው ዛፍ ላይ፣ እንዲሁም የሌሎች የሰራዊቱ አባላት አስከሬን ከወደቀበት ቦታ እንደተገኘ ይነግረናል።

ወያኔ የፈጸመውን የስብእና መራከስና ግፍ መጠን ለመለካት ይህን አንድ ምሳሌ በብዙ መቶሽዎች ማባዛት ይቻላል። ይህን አይነት ግፍ በህዝብ ላይ እንዲፈጸም የፖለቲካ አመራራ ከሰጡ ሰዎች ጋር የአሜሪካ ባለሰልጣናት መቀሌ ሄደው እየገለፈጡ የሰልፊ ፎቶ መነሳታቸውን ሰብአዊነት የጎደለው ኢሞራል የሆነ ድርጊት ነው በማለት አውግዣለሁ። ይህ ድርጊት በኢትዮጵያ ባላስልጣናት ይደገማል ብዬ ግን አስቤ አላውቅም። ጦርነት በሰላም እንዲቆም ለማድረግ ስምምነት ላይ መድረስ አንድ ነገር ሆኖ ሳለ የሰላም ስምምነቱን በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ሰዎች እልቂት ምክንያት ከሆኑ ሰዎች ጋር ጋቢ ለመጋፈፊያ ምክንያት ማድረግ ሌላ ነገር ነው። ከቀን አንድ ጀመሮ በሰላም ስምምነቱ ለመሳተፍ የኢትዮጵያን መንግስት ወክለው የሄዱት ሰዎች ይህ ሰላም ከኋላው የተሸከመውን የህዝብ ሰቆቃ የማይመጥን የፊት ገጽታ የሰውነት ቋንቋ እያሳዩ፣ ከወያኔ ሰዎች ጋር የነበረው ግጭት በአንድ ምሽት በስካር መንፈስ ዳንስ ቤት ውስጥ የተፈጠረ ችግር በሚመስል መልኩ፣ በሳቅና በፈገግታ የተሞላ ግንኙነት ምን ያህል በጦርነቱ የተጎዳውን በሚሊዮኖች የሚቆጠር ህዝብ ሊያስከፋ እንደሚችል ዞሮ ማሰብ ባልቻሉ ስሜት አላባ፣ ሃላፊነት በማይሰማቸው ግለሰቦች የተደረገ ነበር።

በተከታታይ የተድረጉት የወያኔን ነፈሰ ገዳይና ዘራፊ ባላስልጣናት ለማስተናገድ የተሄደበት እርቀት፣ የጌታቸው ረዳና የሺመልስ አብዲሳ መተቃቀፍ፣ የኦሮሞን ባህላዊ ስጦታዎች ለጌታቸውና ለጓደኞቹ መስጠት፣ እንደጌታቸው ረዳ አይነቱን ወንጀለኛ ሰፊ የሚድያ ሽፋን በዋልታ ቴሌቪዥን ላይ በመስጠት፣ ጋዜጠኛው ከወትሮ ባህርይው በተለየ መንፈስ መድረኩን ጌታቸው ያሻውን ፕሮፓጋንዳ እንዲያኪያሂድበት በማድረግ የተሰራው ስራ፣ በጦርነቱ ለተጎዳው ህዝብ የሚያስተላልፈው መልእክት፣ እንኳን የአማራን እና የአፋርን ህዝብ ፈጃችሁልን፤ አዋረዳችሁልን፣ ዘረፋችሁልን፣ እንኳም የሰሜን እዝን የመከላከያ ሰራዊት በተኙበት አረዳችሁልን፣ እንኳን ከየክልሉ ያዘመትናቸውን የልዩ ሃይል አባላት ፈጃችሁልን የሚል ደንታ ቢስ መልእክት ለህዝብ ከማስተላለፍ የተለየ ትርጉም የሚሰጠው አይሆንም። የትግራይ ህዝብም ቢሆን በወያኔ መሪዎች እብሪት የተነሳ የወደቀበትን ስቃይና ሰቆቃ ከቁም ነገር ያልቆጠረ ግንኙነት ነው።

የብልጽግና ፓርቲ በተለይ የኦሮሞ ብልጽግና ከወያኔዎች ጋር ለመቀራረብ የሚሄበትን እርቀት የሚያሳይ ነው። ወያኔዎችም ከኦሮሞ ብልጽግና ፓርቲ ጋር ለመቀራረብ ምን ያህል ዝግጁ እንደሆኑ ያመላከተ ነው። ይህን መቀራረብ በአደባባይ የሚያየውና የሚሰማው የአማራ ህዝብ፣ ሌሎችም በወያኔዎች አማካይነት በደል የደረሰባቸው ህዝቦች ይህን የወያኔ እና የኦሮሞ ብልጽግና ሰዎች አዲስ ፍቅር ከፍተኛ ጥርጣሬ ውስጥ ቢከታቸው የሚያስገርም አይሆንም። ከዚህ መቀራረብ ጋር የአማራ ልዩ ሃይል የመፍረስ ሃሳብ ሲደመርበት ወጤቱ ምን ሊሆን እንደሚችል ትንሽ ማስብ ለሚችል ሰው መገመቱ ከባድ አይደለም። የአማራ ህዝብ በአዲስ የትግሬ/ኦሮሞ የፖለቲካ አሰላለፍ ዝንተ አለም በአማራነቴ ሲደርስብኝ የኖረው ጥቃት ሊቀጥል ነው የሚል ስጋት ውስጥ ቢወድቅና የልዩ ሃይሉን መፍረስ ቢቃወም የሚያስገርም ሊሆን አይገባውም። የመንግስት ባለስልጣናት ስለአማራ ልዩ ሃይል መፍረስ ማብራሪያ ሊሰጡ ብቅ ሲሉ እግረመንገዳቸውን የኦሮሞ ብልጽግና ለምን ለጌታቸው ረዳ ቀይ ምንጣፍ አንጥፎ አስተናጋጅ እንደሆነ መግለጫ መስጠት ነበረባቸው። በዚህ ጉዳይ ላይ ምን አይነት መግለጫ እንደሚሰጡ ባላውቅም።

ከአማራ ህዝብ ጋር ባይገናኝም ይህ የኦሮሚያ ብልጽግና እና የነጌታቸው አሰፋ የጫጉላ ሸርሽር፣ ወያኔን ለማስወገድ በሚታገለው የትግራይ ህዝብና ወጣት ፖለቲከኞች ሞራል ላይ የሚያሳድረውን፣ ከዛም አልፎ የትግራይ ብልጽግና ነኝ በማለት በወያኔዎች ደጋፊዎቹና አባላቱ በተገደሉበት፣ በጅምላ በታስሩበት ድርጅት አባላት ላይ የሚያሳድረው የሞራል ስብራት እንዴት ታይቶ ይሆን የሚል ጥያቄ ማንሳት ተገቢ ነው። ወይንስ ሁሉም የብልጽግና ፓርቲ አባላት አወቁትም ወይም አላወቁትም ወያኔን የትግራይ የብልጽግና ፓርቲ አባል ለማድረግ ሰራ እየተሰራ ይሆን ወይ የሚል ጥያቄ የሚያስነሳ ሆኗል።

ከእነዚህ ኢሞራል ከሆነ ድርጊቶች ጋር የተያያዘው ጉዳይ በትግራይ ምድር ወደ አንድ ሚሊዮን የሚሆኑ ትግራዋይ በጦርነት እንዲያልቁና የአካል ጉዳት እንዲደርስባቸው እንዲሁም ተመሳሳይ ቁጥር ያላቸው ሌሎች የሃገሪቱ ዜጎች ወያኔ በለኮሰው ጦርነት መከራና ስቃይ ውስጥ እንዲወድቁ፣ በትግራይ በረሃና በየጦር ግንባሩ ሲቀሰቅሱ የነበሩ እንደ ሙሉጌታ ማሉዳና ሰሎሞን ባይራይ የተባሉ ዘፋኞች ዛሬ አዲስ አበባ መሃል እመበር ተጋዳላይ፣ ወያኔ አሸናፊ፣ ፒፒ ተሸናፊ የሚሉ ዘፈኖቻቸውን በመጠጥ ጢንቢራቸው በዞሩና ገንዝብ እንደቅጠል በሚበትኑላቸው ደጋፊዎቻቸው ፊት በጠባቂዎች ታጅበው ሲጨፍሩ እያየን ነው። https://vm.tiktok.com/ZMYs57L9E/ https://vm.tiktok.com/ZMYs5TRmY/ https://vm.tiktok.com/ZMYsaJUWW/

እነዚህ ዘፋኞች ነገ ቅዳሜ መጋቢት 8 2015 አዲስ አበባ ውስጥ በሜሎዲ ላውንጅ ባዘጋጁት ኮንሰርት ታዳሚ መሆን የሚፈልግ VIP 100000 ብር ለሌላው ሰው 50000 ብር መግቢያ የሚጠይቁበትን ፖስተር በአደባባይ እያስተዋወቁ ይገኛሉ። በአንድ በኩል በአማራ ምድር የሚፈሰውን ደምና እምባ፣ የሰፈነውን ስጋት፣ በሌላ በኩል በወያኔ መሪዎች ቤት እየሰፈነ ያለውን ሰላም መረጋጋት፣ ፈንጠዝያና ደስታ የሚመለከት የአማራ ህዝብ በልዩ ሃይሉ መፍረስ የሚያሰማውን ቁጣ አግባብነት የሌለው አድርጎ ማየት አይችልም። የሚገርም ነገር ቢኖር ይህ ስጋት የማይጋራ አማራ ከተገኘ ብቻ ነው።

6) ከዚህ በላይ ከቀረቡት ምክንያቶች በተጨማሪ አንድ ጸሃፊ እንደጠቆመው “በተለያዩ አጋጣሚዎች ከማእከላዊ መንግስት ባለስልጣናት፣ የአማራ ክልል አለብኝ ብሎ በሚያስበው የጸጥታ ስጋት ልክ የክልሉን ልዩ ሃይል ለማደራጀት በሚያደገው ጥረት ላይ ሲሰጡ የነበሩ አሉታዊ አስተያየቶች፤ ከጦርነቱ በኋላም የአማራ ህዝብና ልዩ ሃይሉ የከፈሉትን መስዋእትነት በቂ እውቅና ላለመስጠት የሚታዩ መሽኮርመሞች፣” በወያኔዎች ጉትጎታ በአሜሪካ መንግስት የአማራ ልዩ ሃይል ተለይቶ የከፋ ወንጀለኛ ሆኖ የቀረበበት ሁኔታ፤ በሃገር ውስጥም እስከትናንት ድርስ የላቆመውን በአጣዬ ከተማ ዙሪያ የኦነግ ሸኔን ጥቃት ለመከላከል የተወሰዱ እርምጃዎችን፣ “ልዩ ሃይሉን በጦር ወንጀለኛነት ለመክሰስ አፋቸውን ሞልተው የሚናገሩ የፓርላማ አባል የታዩበት ሁኔታ”፣ አማራው ወዶ ያላመጣውን፣ በመጀመሪያውና በሁለተኛው ዙር የሃገር መከላከያ በደረሰበት ያልተጠበቀ ጥቃት ማስቆም ያልቻለለትን ወረራ ለመከላከል፣ የሚደርስበትን ግድያና ዘረፋ ለማስቆም ከብቶቹን እየሸጠ፣ “መንግስት ራሱ ጠላትን ገድለህ ወይም ማርከህ ታጠቅ ብሎ የሰጠውን መመሪያ ተከለቶ የታጠቀውን መሳሪያ፣ የአማራ ክልል ከሚገባው በላይ የመሳሪያና የትጥቅ ቀጠና በመሆን በስልጣን ላይ ላለው መንግስት አደጋ ይሆናል በሚል በኦሮሞዎች እጅ ባሉ የሚድያ ተቋማትና እንደ የኦሮሞ ኮንግሬስ የመሳሰሉ ድርጅቶች ሲወጡ የነበሩ ጸረ አማራ መግለጫዎችና ውንጀላዎች፤” ጥቂት የፋኖ አባላት እንደመከላከያ፣ እንደ ልዩ ሃይልና የትኛውም ወታደራዊ ተቋም ውስጥ እንዳሉ አባላት የሚፈጽሙትን ወንጀል ወይም ጥፋት “ከሚገባው በላይ ለጥጦና አጋኖ ሁሉንም የፋኖ አባላት የወንጀለኛነት ቅብ ለመቀባት የተሄደበት እርቀትና ከ12ሺህ በላይ የአማራ ወጣቶች በዘመቻ መልኩ እንዲታስሩ የተደረገበትን ሁኔታ፣ አንዴ በአማራ ክልል የሰኔ 15 አይነት የመፈንቀለ መንግስት ሙከራ ሊደረግ ነው፣ አንዴ በማእከላዊ መንግስቱ ላይ መፈንቅለ መንግስት እየታሰበ ነው የሚሉትን ጉዳዮች በአማራ ክልል ከታጠቁ አካላት ጋር በማገናኘት ሲሰሩ የቆዩ የፕሮፓጋንዳ ስራዎች፣ ሌላ ቀርቶ በወለጋ የሚታየውን የአማሮች እልቂት እና መፈናቀል ከአማራ ክልል መሳሪያ በሚነገዱ ሰዎች የተነሳ ነው ማስቆም ልቻልነው የሚል ተልካሻ ምክንያት ጋር የተያያዝበት ሁኔታ፣ ሸኔ ብቻ ሳይሆን እራሱ ወያኔ ከመከላከያ ሰራዊት በምርኮና በግድያ የታጠቃቸው ጥቁር ክላሾች እንዳሉ እየታወቀ፣ ጥቁር ክላሽ በጁ የያይዘ ፋኖ በሙሉ መሳሪያውን ያገኘው የመከላከያ ሰራዊት አባላትን ገሎና ገፎ ነው የሚል ጥቅል ውንጀላ የተካሄደበት ሁኔታ፣ የአማራ መታጠቅና ራሱን አምሮ ወደመከላከል መሄዱ ግጭቱን ከታጣቂዎች ግጭት አልፎ በአማራና በኦሮሞ ህዝብ መሃከል እንዲሆን የሚያደርግ ነው የሚል ትንተና በኦሮሞ ፖለቲከኞች በስፋት መቅረቡ፣ አማሮች ጥቃት ለመፈጸም ወደመሃል ሃገር እየገቡ ነው የሚለው የፌደራል መንግስትና የአዲስ አበባ አስተዳደር ባለስልጣናት ተደጋጋሚ መግለጫዎች፣” ሌሎችንም ጽሁፉን ለማሳጠር በማስብ የልጠቀስኳቸውን ጭብጦች በመደመር የአማራ ህዝብና መሳሪያ መገናኘታቸው ቀልባቸውን እንዲስቱ (paranoid) ያደረጋቸው አካላት የአማራን ልዩ ሃይል ብቻ ሳይሆን በሂደት የአማራ ህዝብን ከዚህ ቀደም ወያኔ እንዳደረገው መሳሪያውን ለመግፈፍ እሰበው እየተንቀሳቅሱ ነው ወደሚል ድምዳሜ ቢያደርሰውና ህዝቡም ይህንንማ ዳግመኛ አልፈቅድም ብሎ በጋራ ቢነሳ እንዴት የሚያገርም ወይም ግራ የሚያጋባ ይሆናል።

ግራ የሚያጋቡን ከየትኛው በሃገሪቱ ውስጥ ከሚገኝ ህዝብ በከፋ መልኩ፣ በስልጣን ሽኩቻ ይሁን በተሳስተ ትርክትና የፖለቲካ እይታ የጥቃት ሰለባ ሲሆን የኖረውን እና አሁምን እየሆነ ያለውን የአማራ ህዝብ ስጋት የማይጋሩ አማሮችና ይህን ስጋት መቅረፍ የሚያስችል ተጨባጭ መፍትሄዎችና መሬት ላይ ሳያስቀምጡ አማራውን በሃገር አንድነትና በጠንካራ መከላካያ ስም ትጥቁን ለማስፈታት የሚሞክሩ የፌደራል አካላት ናቸው።

የአማራ ህዝብ አሁን ያለውን መከላከያ ከጥቃት ለማዳን መስዋእትነት የከፈለው መከላከያ ዋናው የሃገር ህልውና የአማራና የሌሎችም ህዝቦች አለኝታ መሆኑን ስለሚያውቅ ነው። ከወያኔ በፊት በነበሩ መንግስታዊ ሰርአቶች ውስጥ ኢትዮጵያ ጠንካራ የመከላከያ ሃይል እንዲኖራት የአማራ ህዝብና ወታደራዊ ልሂቃን ከሌሎች ወንድሞቻቸውና እህቶቻቸው ጋር በመሆን የከፈሉትን መስዋእትነት ታሪክ የሚያስታውሰው ነው። በአጼ ሃይለስላሴና በደርግ ዘመን የሰራዊቱ አመራሮች በብሄር ተዋጽዋቸው የነበራቸው ድርሻ ለብሄሮች እኩልነት ቆሚያለሁ ከሚለው የወያኔ ዘመን የተሻለ ሆኖ ሳለ፣ ለዘመናት በስንት መከራ የተገነባውን እና በከፍተኛ ፕሮፊሽናሊዝም ስራውን ሲሰራ የነበረውን፣ የዘር ልዩነት እያደረገ አንዱን ማህበረሰብ ከሌላው ለይቶ ጥቃት ስንዝሮ የማያውቀውን፣ በየዘመኑ መንግስታት “ህግ አስከብር” የሚል ትእዛዝ ሲሰጠው በጎጃሙ አርሶ አደር፣ በባሌው አርብቶ አደር፣ በትግራዩ ወያኔ፣ በኤርትራ አማጽያን ላይ በእኩልነት መሳሪያውን የሚያነሳውን ሃገራዊ የጦር ሃይል” የአማራ ሰራዊት” በሚል ስያሜ ወያኔ ሲያፈርሰው ተባባሪ የነበሩ ሃይሎች ለአማራው፣ የጠንካራና አንድ ወጥ ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያ ብቻ የቆመ ጎጥ ዘለል ሃገራዊ ሰራዊት አስፈላጊነት ሊያስረዱት መምጣታቸው የታሪክ ምጸት ሆኖ የሚቆጠር ነው።

በመጨረሻም፣ አሁን በአማራ ክልል ከልዩ ሃይሉ ጋር የተፈጠረውን ችግር በማስፈራራት፣ የክልሉን መሪዎች ወያኔዎች ሲያደርጉ እንደኖሩት በስልጣን እና በጥቅም በመደለል፣ በፕሮፓጋንዳ ውርጅብኝና በሌሎችም ዘለቄታዊ መፍትሄ ማምጣት በማይችሉ መንገዶች ሄዶ ለማቃለል የሚደረግ ሙከራ የትም እንደማያደርስ መታወቅ ይኖርበታል። የአማራ ህዝብ የደህነት ስጋቶች በሙሉ በሚገባ መርምሮ ለእነዚህ ስጋቶች መፈትሄ በመስጠት ብቻ ነው ችግሩን በተሳካና ለዘለቄታው መፍታት የሚቻለው። በዚህ የአማራ ህዝብ ለችግር በተዳረገበት ወቅት ሁሉም በኢትዮጵያ ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን፣ ኢትዮጵያ ለሁሉም ዜጎቿ በእኩልነት የምትመች ሃገር እንደትሆን የሚመኙ ዜጎች በሙሉ ከአማራ ህዝብ ጎን ሊቆሙ ይገባል። ፍትሃዊ የሆነ ጭንቀት ከተጋረጠበት ህዝብ ጎን ለመቆም አማራ መሆን አያስፈልግም። ሰው መሆን ብቻ በቂ ነው።

Related Stories