በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የታሰሩት የምክር ቤት አባላት የት እንዳሉ አለመታወቁን ጠበቃቸው ተናገሩ
በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የታሰሩት የምክር ቤት አባላት የት እንዳሉ አለመታወቁን ጠበቃቸው ተናገሩ
አበይት ጉዳይ
በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የተያዙ የምክር ቤት አባላት ታስረውበት ከነበረው የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን የማቆያ ቦታ እንደሌሉ እና ያሉበትን ቦታ ማወቅ እንዳልቻሉ ከጠበቆቻቸው አንዱ ለቢቢሲ ተናገሩ።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል እንዲሁም በምክር ቤቱ የመንግሥት ወጪ፣ አስተዳደር እና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የሆኑት አቶ ክርስቲያን ታደለ እና የአዲስ አበባ ምክር ቤት አባሉ ዶ/ር ካሳ ተሻገር ዛሬ ፍርድ ቤት እንደሚቀርቡ ለቤተሰቦቻቸው ቢገለጽም፣ ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ ቀርተዋል።
በተጨማሪም እስካሁን ድረስ ቤተሰቦቻቸውም ይሁን ጠበቆቻቸው ሁለቱ ታሳሪዎች ያሉበትን ቦታ እንዳላወቁ ጠበቃ ሔኖክ አክሊሉ ተናግረዋል።
“ዛሬ ፍርድ ቤት እንደሚያቀርቧቸው ከቤተሰቦቻቸው ሰምተን ፍርድ ቤት ተገኝተን ነበር፤ አልቀረቡም። በኋላ ላይ ስናጣራ ይገኙበት በነበረው የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ውስጥ እንደሌሉ እና ለጊዜው ያላረገገጥነው ቦታ እንደተወሰዱ ሰምተናል” ብለዋል ጠበቃው።
ቤተሰቦቻቸውም ወደ እስር ቤቱ አስገብተውላቸው የነበሩ ንብረቶችን መውሰድ እንደሚችሉ ተነግሯቸዋል የሚሉት ጠበቃ ሔኖክ፣ በሐዘን እና በከፍተኛ የስሜት መሰበር ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል።
አንዳንድ ቤተሰቦቻቸውም ሌላ እርምጃ ሊወሰድባቸው ይችላል በሚል የመረበሽ ስሜት ውስጥ እንዳሉ ጠበቃ ሔኖክ ተናግረዋል።
“ '11፡00 ሰዓት ላይ ሊነጋጋ ሲል ነው የወጡት'፣ 'ወደ አዋሽ ተወስደዋል' ” ከሚል ያልተረጋገጠ ወሬ በስተቀር የት እንዳሉ አናውቅም” ብለዋል ጠበቃው።
በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ተጠርጥረው በእስር ላይ ከነበሩ ሌሎች ግለሰቦች መካከል ዛሬ ሰኞ ነሐሴ 15/2015 ዓ.ም. ፍርድ ቤት የቀረቡ እንደነበሩ የገለጹት ጠበቃ ሔኖክ፣ ፍርድ ቤት እንደሚቀርቡ የተነገራቸው በፖሊስ መሆኑንም መረዳት እንደቻሉ ገልጸዋል።
በአማራ ክልል የተፈጠረውን የፀጥታ መደፍረስ ተከትሎ የሚኒስትሮች ምክር ቤት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከደነገገ በኋላ የዚያኑ ዕለት አርብ፣ ሐምሌ 28/2015 ዓ.ም. ከምሽቱ 3፡30 አካባቢ አቶ ክርስቲያን ታደለ በፀጥታ ኃይሎች ከመኖሪያ ቤታቸው ተይዘው መወሰዳቸውንና ድብደባም እንደተፈፀመባቸው ቤተሰቦቻቸው መግለጻቸው ይታወሳል።የአዲስ አበባ ከተማ የምክር ቤት አባል የሆኑት ዶ/ር ካሳም አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በተደነገገበት ዕለት እኩለ ሌሊት ላይ በፌስቡክ ገጻቸው “ፖሊሶች ነን የሚሉ ሰዎች በሌሊት መጥተው ክፈት እየተባልኩ ነው” የሚል መልዕክት ካሳፈሩ በኋላ ነበር በፖሊስ መወሰዳቸው የተሰማው።
ቢቢሲ ከፌደራል ፖሊስ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ያደረገው ጥረት ስልክ ባለመነሳቱ አልተሳካም።
በቁጥጥር ሥር ከዋሉበት ጊዜ ጀምሮም ቤተሰቦቻቸው እና ጠበቆቻቸው ያለመከሰስ መብት ያላቸውን የምክር ቤት አባላቱን እንዳያገኟቸው መከልከላቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈጻጸም መርማሪ ቦርድ አርብ ዕለት በአዋጁ የታሰሩ ተጠርጣሪዎችን እንደጎበኘ እና የሰብዓዊ መብት አያያዛቸው በመልካም ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ቢገልጽም፤ አሁንም በርካታ ታሳሪዎች የት እንዳሉ እንደማይታወቅ፣ ከቤተሰቦቻቸው እና ከጠበቆች ጋር መገናኘት እንዳልቻሉ እየተነገረ ነው።እንደ ጠበቃ ሔኖክ ከሆነ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አሳሪው አካል ተጠርጣሪዎችን ፍርድ ቤት የማቅረብ ግዴታ የለበትም።
ሆኖም ፍርድ ቤት ቢያቀርባቸውም፣ ባያቀርባቸውም በእስር ላይ እስካሉ ድረስ በጠበቃ እንዲሁም በቤተሰባቸው የመጎብኘት መብት አላቸው።
ፍርድ ቤት የሚያቀርቧቸው ከሆነም በጠበቆች ተወክለው የሕግ ድጋፍ የማግኘት መብት ስላላቸው ያሰራቸው አካል ለጠበቆች የማሳወቅ ግዴታ አለበት።
“እስካሁን ድረስ ግን ከጠበቆቻቸው እንዳይገናኙ ተከልክለዋል። ያሉበትን ቦታ እና ሁኔታም ቤተሰቦቻቸውም ሆኑ ጠበቆቻቸው አናውቅም” ብለዋል ጠበቃው።
“በሕግ ጥላ ሥር ያሉ ሰዎችን ያለምንም እውቅና ወደ ሌላ ቦታ ማዛወር ሕገ ወጥ ነው” የሚሉት ጠበቃ ሔኖክ፣ በሕግ አግባብ ይዣቸዋለሁ የሚለው የመንግሥት ተቋም ያሉበትን ሁኔታ የማሳወቅ ግዴታውን እየተወጣ አይደለም” ሲሉም ይከሳሉ።
የምክር ቤት አባላቱ ያለ መከሰስ መብታቸው ሳይነሳ መታሰራቸው ሕጋዊ አይደለም በማለት አካልን ነጻ የማውጣት ክስ መሥርተው ጉዳዩን እየተከታተሉ እንደሆነ ያስታወሱት ጠበቃ ሔኖክ፣ በቀጣይ እነዚህ ግለሰቦች የት እንዳሉ የማሳወቅ ግዴታ ያለበትን መርማሪ ቦርዱን እንጠይቃለን ብለዋል።
“አንድን ሰው አስገድዶ መሰወርም ሆነ ያለበትን አለማሳወቅ ዓለም አቀፍ ወንጀልም ነው፣ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅም ቢሆን የተከለከለ ተግባር ነው። ቤተሰቦቻቸውም ምን ዓይነት ሁኔታ ላይ እንዳሉ የማወቅ መብት አላቸው” ብለዋል።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ዕዝ ጠቅላይ መምሪያ በአማራ ክልል የተፈጠረውን “ግጭት ለማባባስ የከተማ ውስጥ ግዳጅ በመውሰድ የሎጅስቲክስ እና የፋይናንስ ድጋፍ በማድረግ የተለያዩ ሕገወጥ ተግባራትን ሲፈጽሙ ነበር” ያላቸውን 23 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ገልጿል።
ከእነዚህም መካከል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል እና በምክር ቤቱ የመንግሥት ወጪ፣ አስተዳደር እና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ክርስቲያን ታደለ እና የአዲስ አበባ ከተማ የምክር ቤት አባሉ ዶክተር ካሳ ተሻገር ይገኙበታል።
የሰብአዊ መብት ድርጅቶች እና ቤተሰቦች ግን በፀጥታ ኃይሎች በጅምላ እስር እየተፈጸመ መሆኑን በመግለጽ፣ በቁጥጥር ሥር የዋሉ ሰዎች ቁጥር ከተጠቀሱት በላይ ነው ይላሉ።