ለአቶ አዲሱ አረጋ የተሰጠ ምላሽ

ነፃ ሃሳብ

4/4/20232 min read

የአቶ አዲሱ አረጋ ቂጤሳን ዘለግ ያለ ጽሁፍ አንብቤው ውስጤ በተለያዩ ጥያቄዎች ተሞላብኝ።

መሳይ መኮንን

የአቶ አዲሱ አረጋ ቂጤሳን ዘለግ ያለ ጽሁፍ አንብቤው ውስጤ በተለያዩ ጥያቄዎች ተሞላብኝ። እሳቸው የሚመልሷቸው አይደሉም። አቶ አዲሱ ቆንጆ አድርገው ጽፈዋል። ሊትሬቸሩ ጥሩ ነው። ሩዋንዳ ተጉዘው ከዚያ የክፍለዘመኑ የሰው ልጅ የዕልቂት መንደር ከነበረው ስፍራ ተገኝተው ያዩትንና የተሰማቸውን አካፍለውናል። ያሳስበኛል፡ ያብሰለስለኛል፡ ያስጨንቀኛል፡ ያስተክዘኛል፡ ያንቆራጥጠኛል፡ እረፍት ይነሳኛል በሚሉ ቃላት እያጀቡ ስሜታቸውን- የእውነት ውስጣቸው ያለውን ትክክለኛ ስሜት ልብና ኩላሊትን ለሚመረምረው አምላክ እንተወውና- የገለጹበት መንገድና የአደጋውን ጥልቀት ያሳዩበት ሁነት የሚያስጨንቅም፡ አብዝቶ የሚያሳስብም ነው። እኔም በታሪክ አጋጣሚ ወደ ቡሩንዲ ለሰላም ማስከበር ተግባር ለአንድ ዓመት ያህል ቆይቼ በነበረ ጊዜ የሩዋንዳን ጨምሮ የአብዛኞቹን የአከባቢው ሀገራትን ቁስልና ቁርሾ በቅርበት የማየቱና ምስክርነት የመስጠቱ እድል ገጥሞኛል። ዛሬ አቶ አዲሱ ተሰምቶኛል ያሉትን ፍርሀትና ጭንቀት በእኔ ልብና ደም ውስጥ ሰርስሮ ከገባ ዓመታት መቆጠራቸውን መግለጹ ተገቢነት ያለው ይመስለኛል።

የዛሬ 20 ዓመት አከባቢ ቡሩንዲ ነበርኩ። ለተለያዩ ስራዎች ከቡሩንዲ ወደ ሩዋንዳ፡ ኮንጎ ኪንሻሳና አጎራባች ሀገራት የድንበር አከባቢዎች እንቀሳቀስ ነበር። የሩዋንዳው የዘር ፍጅት ኮፒ የሆነውንና መቶ ሺዎችን የፈጀውን የቡሩንዲን የእርስ በእርስ መተላለቅ ያስቆመውን የአፍሪካ ህብረት የሰላም አስከባሪ ዘመቻ በመሳተፍ ነበር ወደ አከባቢው ያቀናነው። እንደአቶ አዲሱ አረጋ የሰነበተ አጽም፡ አሻራው የደበዘዘ ጠባሳ አልነበረም የገጠመን። በአንዳንድ ቦታዎች ትኩስ አስክሬኖች ተቆልለው የሚታዩበት ዘግናኝ ትዕይንትን በአካል የማየቱ አጋጣሚም ነበር። ከሰለባዎች ጋር ተገናኝተናል። ስለታላቁ የሰው ልጅ ጥፋት ከፈረሱ አፍ ሰምተናል። ይህንንም የመጀመሪያ ደረጃ ምስክርነትና ማስረጃዎች የተጠናቀሩበት የተለያዩ የጋዜጣ ጽሁፎችና የሬዲዮ ፕሮግራሞች በአዲስ አድማስ ጋዜጣና በድቡብ ድምጽ ሬዲዮ ኤፍ ኤም 100.9 እንዲሁም በብሄራዊው የኢትዮጵያ ሬዲዮ ለህዝብ እንዲቀርብ አድርጌአለሁ። አሁን አቶ አዲሱ እንዳስጨነቃቸውና፡ እንዳብሰለሰላቸው ያን ጌዜ ያስጨነቀንንና ያብሰለሰለንን ከባለታሪኮቹ እውነተኛ ታሪክ ጋር አድርገን ''የዘር ፖለቲካ ለኢትዮጵያ መቅሰፍት ነው'' የሚል ጩኸት ስናሰማ ነበር። ይኸው 20 ዓመታት ሙሉ ሳናቋርጥ እየጮኽን፡ እያለቀስን አለን። የአቶ አዲሱን የተለየ የሚያደርገው አዲስ ነገር የለም። ቁምነገሩ ይሄን የሚነግሩን እሳቸውና የሚያንቆለጳጵሱት ፓርቲያቸው ምን እያደረጉ ነው የሚለው ጉዳይ ነው።

አቶ አዲሱ በአውሮፕላን ተሳፍረው፡ ድንበር ተሻግረው ከኪጋሊ ያዩትን ሲነግሩን በእሳቸው አፍ ዘውትር እንደጅረት እየፈሰሰ በሚናገሩለት የ'ለውጥ' ዓመታት በተለያዩ የኢትዮጵያ አከባቢዎች የተፈጸሙትን የዘር ማጥፋትና የጅምላ ግድያ ወንጀሎችን የት አስቀምጠዋቸው እንደሆነ አላውቅም። የእነማይካድራ፡ ካሊጎማ፡ ጭና፡ ቆቦ ዕልቂቶች በተናጠልም ሆነ በድምር ካየናቸው ከሩዋንዳው የዘር ማጥፋት ድርጊት ቢስተካከሉ እንጂ የሚያንሱ አይደሉም። ወለጋ የሚታረዱት፡ በጅምላ የሚጨፈጨፉትን የት ደብቀዋቸው ነው የሩዋንዳውን ጄኖሳይድ እንደአዲስ ክስተት ሊነግሩን የመጡት? በአዲስ አበባ ዙሪያ የሚካሄደው ዘር ተኮር ማፈናቀል ከጄኖሳይድ ምን የሚለየው ነገር አለና ነው ከደሙ ንጹህ ነኝ አይነት ጨዋታ ይዘው ብቅ ያሉት? በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ፊት፡ ሚሊዮኖች በቀጥታ ቴሌቪዥን ስርጭት በሚታደሙት ስብሰባ ላይ ''አዲስ አበባ ኦሮሞ ጠል ነዋሪ ያለባት ናት'' ያሉት የእርስዎ ጠቅላይ ሚኒስትርና ጓደኛ ያንን ሲናገሩ ምን ማለት እንደሆነ ካልተረዱት የሩዋንዳ የዘር ማጥፋት ክስተት እንዴት እንደመጣ ታሪኩን በደንብ ያንብቡና ተመልሰው እንዲመጡ እጋብዝዎታለሁ። በበቀደሙ ፓርላማ ውሎም የእርስዎ ሜንተር ጠሚ/ር አብይ ''እኛ ኦሮሞዎች....'' እያሉ ሲናገሩ ህብረተሰቡ ውስጥ ምን ቁጭትና ቂም እንደሚፈጥር ካልተገለጸልዎ ስለሩዋንዳ የጻፈው ብዕርዎ ቢዶሎድም ይሻለው ነበር። ሰሞኑን በመላ ኦሮሚያ የጠራችሁት ሰልፍ ለጄኖሳይድ መከሰት የሚያበረክተውን ድርሻ ሳይረዱት ቀርተው ከሆነ ወይ ፖለቲካ አያውቁም አልያም አውቆ የተኛን ቢቀሰቅሱት አይሰማ ብለን እንድንተችዎት እንገደዳለን።

በእርግጥም አቶ አዲሱ የጻፉትን አይቼ ጠንቋይ ስለራሱ አያውቅም የሚለው ብሂል አፌ ላይ ግጥም አለብኝ። እውነት ለመናገር የሚሉትን ሁሉ እያደረገ ያለው ማን ነው? ለማን ነው ምክራቸው? ስለማን ነው የሚነግሩን? ይህን ሀሳብ ፓርቲያቸው መድረክ ላይ አንስተው ያውቃሉን? አሁን እሳቸውን በአመራርነት የሚሳተፉበት ገዢ ፓርቲ ወዴት ይዞን እየነጎደ እንደሆነ ሳያውቁት ቀርተው ነውን? የአኖሌ ታሪክ የፈጠራ ነው፡ የመለስ ዜናዊ የምሽግ ውስጥ ድርሰት ነው ብለው በድፍረት በአደባባይ ከነገሩን ወዲህ የገዛ ፓርቲያቸው እየፈጸመ ያለውንና ሀገርን ለታላቅ ቀውስ እያመቻቻት የሚገኘውን አደገኛ አካሄድ ለማየት የግድ ሩዋንዳ ድረስ መሄድ ነበረባቸው? የሩዋንዳን አስር እጥፍ የሚያስንቅ የዘር ፍጅት ድግሱ እየተቀመረ የሚገኘው ከየት እንደሆነ ጠፍቷቸው ነው ዛሬ መካሪ ዘካሪ ሆነው ብቅ ያሉት? ሰው እንዴት የራሱን የገዘፈ ጉድፍ ማየት ተስኖት የሌላውን ጩኸት ቀምቶ ማልቀስን ይመርጣል? እውነት ለመናገር አቶ አዲሱ ይህን ጭንቀትና መብሰልሰላቸውን እዚያው ፓርቲያቸው ጓዳ ለማንሳት ወኔ ነበራቸውን? የእምዬን ለአብዬ አይነት እርባና የሌለው፡ ሌላ ላይ ጣት ለመቀሰርና የራስን ሃጢያት ሌሎች ላይ ለመከመር የሚደረግ ፍጹም ሃላፊነት የጎደለው አካሄድ ነው።

አቶ አዲሱ ኢትዮጵያ ላይ የሩዋንዳ ዓይነት ዕልቂት እንዳይከሰት ሰጋሁ ብለዋል። እንግዲያውስ ይህን ስጋትዎን ለመቅረፍ አንድ እርምጃ ይውሰዱ። የእርስዎ ፓርቲ ሽምጥ እየጋለበ ከሚገሰግስበት የጥፋት መንገድ እንዲመለስ የበኩልዎን ሚና ይጫወቱ። እዚህ ለእኛ ጭንቀትዎን ከሚያካፍሉን እዚያው ከጓደኞችዎ ጋር በር ዘግታችሁ የእውር ድንብር ጉዞአችሁን በሚገባ ፈትሹት። መጎምዠታችሁን በልክ አድርጉት። ስልቀጣችሁን ሉጋም አበጁለት። ተረኝነቱን የምር አስቁሙት። አፋችሁንም ሰብሰብ አድርጉት። በየአደባባዩ የምትናገሩት ሀገሪቱን ከባድ ዋጋ እያስከፈላት መሆኑን አውቃችሁ አንደበታችሁን ለመግራት የሚቻላችሁን ጥረት ለማድረግ ሞክሩ። ሌብነቱንም ማጥፋት ባትችሉ እንኳን ቀንሱት። እርስዎን ጨምሮ የብልጽግና አመራሮች እየሰበሰባችሁት ያለው የህዝብ ሀብት አንዱ ለጄኖሳይድ መከሰት ምክንያት መሆኑ አይቀርምና የነገውን ገደል አስባችሁት ዛሬ ላይ ራሳችሁን አይን ካወጣ ዘረፋ አቅቡት። በተከበረው የኦሮሞ ህዝብ አትነግዱ። ኦሮሞ ኢትዮጵያን ያቀና፡ ኢትዮጵያን ያቆመ፡ ለኢትዮጵያ መጽናት የአንበሳውን ድርሻ የሚወስደውን ህዝብ አመድ አፋሽ አታድርጉት። በእናንተ ዘመን የኦሮሞ ህዝብ ታሪኩ እንዳይበላሽ አድርጉት። በቃ! ቆም ብላችሁ ምን እያደረግን ነው በሚል የሃላፊነትና የታላቅነት ስሜት ኢትዮጵያን ከመጣባት አደጋ ታደጓት። ሌላ ጋ ጣትዎን አይቀስሩ። መፍትሄው በእናንተ እጅ ነው። ገለቶማ!!!!

Related Stories