የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ከሽግግር ፍትሕ ባለፈ የዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ ተሳትፎ ያስፈልጋል አለ

HR REPORTSየዜና ትንታኔ

4/6/20232 min read

በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ተፈጸሙ የሚባሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ለማጣራትና ፍትሕና ተጠያቂነትን ለማስፈን፣ የፌዴራል መንግሥት ከጀመረው የሽግግር ፍትሕ ሒደት ባሻገር፣ የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብም ተሳትፎ እንዲኖር የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳዳር ፍላጎቱ እንደሆነ አስታወቀ፡፡

በቅርቡ የጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዚዳንት ሆነው የተመረጡትና በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የተሾሙት አቶ ጌታቸው ረዳ እንደገለጹት፣ ጠንካራ የሆነ የአገር ውስጥ ሥርዓት ለፍትሕና ለተጠያቂነት ሥራዎች አካል መሆን እንደሚችል እምነታቸው ነው፡፡ ሆኖም የትግራይ ክልልን በሚመለከት በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ተሳትፎ ፍትሕና ተጠያቂነትን ማስፈን አስፈላጊ ነው ብለዋል፡፡

ሰኞ መጋቢት 25 ቀን 2015 ዓ.ም. በአውሮፓ የትግራይ ዳያስፖራ ካውንስል ባዘጋጀው የበይነ መረብ ፓናል ውይይት ላይ የተሳተፉት የጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዚዳንት፣ የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ድርሻ ማነስ እንደሌለበት ገልጸው፣ ‹‹የገጠመን ፈተና ትልቅነትና የተከሰተው የወንጀል ዓይነት ከሽግግር ፍትሕ ባሻገር ሌሎች መንገዶችንም ይፈልጋል፤›› ብለው፣ ‹‹በቀላሉ እንኳን የኤርትራ ኃይሎች ተሳትፎ ጠንካራ የሆነ የፍትሕ ሒደት ያስፈልገዋል፤›› ሲሉ አክለዋል፡፡

በእሳቸው ጊዜያዊ አስተዳደርና በፌዴራል መንግሥት በኩል በዚህ ረገድ የጋራ ተሳትፎ እንዲኖር እንደሚሹ የገለጹት አቶ ጌታቸው፣ አስተዳደራቸው እስካሁን በብሔራዊ የሽግግር ፍትሕ ሒደቱ ላይ የመወያየት ዕድል እንዳላገኘ ተናግረዋል። አስተዳደራቸው በሽግግር ፍትሕ ሒደቱ ላይ ቢሳተፍና ሒደቱም ቢሳካ እንኳን፣ ‹‹በትግራይ ላይ የተፈጸመው ወንጀል የዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ ተሳትፎ በእጅጉ አስፈላጊ ያደርገዋል፤›› ብለዋል፡፡

የበይነ መረብ ፓናል ውይይቱ መቀመጫውን በአሜሪካ ያደረገው በሰብዓዊ መብቶች ላይ የሚሠራው ‹‹የሂዩማን ራይትስ ዎች›› የምሥራቅ አፍሪካ ዳይሬክተር ላቲሽያ ባደርንን ጨምሮ፣ አምስት ተሳትፊዎች የተካተቱበት ነበር፡፡ በውይይቱ መክፈቻ ላይ የተናገሩት አቶ ጌታቸው፣ በፕሪቶሪያ ከተደረገው የሰላም ስምምነት በኋላ ለሚታዩት ለውጦች ዕውቅና፣ እንዲሁም ከፌዴራል መንግሥት ጋር እየተደረጉ ላሉት ውይይቶችም ዋጋ እንደሚሰጡ ገልጸዋል፡፡

‹‹የኤርትራና የአማራ ኃይሎች በተወሰኑ የትግራይ አካባቢዎች ከመኖራቸው በስተቀር›› ሰላም በበርካታ ሥፍራዎች መሥፈኑና ተኩስ የማይሰማበት ሁኔታ መፈጠሩ በከፊል መሳካቱን፣ ከስምምነቱ በኋላ የተፈጠሩትን ሁኔታዎች ሲገልጹ አንስተዋቸዋል፡፡

የፌዴራል መንግሥትና የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ጠንካራ አቋም የያዙባቸው ጉዳዮች እንዳሉ ያወሱት አቶ ጌታቸው፣ ግንኙነቱን የበለጠ ለማጠናከር የጋራ መግባባት እስካለ ድረስ፣ ‹‹እኛ የራሳችን የሆነ ጠንካራ አቋም ስላለን ብቻ ለቀጠለው ትብብር እንቅፋት መሆን የለብንም፤›› ብለዋል፡፡ በመቀጠልም ‹‹ከፍትሕና ከተጠያቂነት ጋር በተፃረረ መንገድ ግን መሆን የለበትም፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡

የፌዴራል መንግሥት የተለያዩ አካላትን እያሳተፈ በሚገኝበት የሽግግር ፍትሕ ሒደት ዝርዝር ማዕቀፍ ላይ ብዙም ተሳትፎ እንደሌላቸው፣ በዚህ ጉዳይ ላይ ከፍትሕ ሚኒስትሩ ጋር በነበራቸው ውይይት፣ የትግራይ ክልል የቅርብ ተሳትፎ እንዲኖር መጠየቃቸውን ተናግረዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ ከተለያዩ የፌዴራል መንግሥት ኃላፊዎች ጋር በነበራቸው ውይይት፣ የዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ ተሳትፎ በተመለከተ መነጋገራቸውን ገልጸዋል፡፡ ‹‹የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ተሳትፎ ምንም ዓይነት ወንጀል አልፈጠርንም ብሎ የሚያስብ ማንም ኃይል ፍላጎት ሊሆን እንደሚችል ተነጋግረናል፤›› ሲሉ አቶ ጌታቸው ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ይህን ጉዳይ ማንሳታቸውን አስረድተዋል፡፡

ዓለም አቀፍ ተቋማት ወደ ኢትዮጵያ መጥተው እንዲመረምሩ መፈቀድ እንዳለበት፣ ባይፈቀድም ደግሞ አስፈላጊውንና የሚያሳምን ማስረጃ ይዘው ከመቅረብ የሚያቆማቸው ማንም እንደሌለ አቶ ጌታቸው ተናግረዋል፡፡

Related Stories