በተለያዩ አካባቢዎች በተደጋጋሚ የሚፈጸሙ እገታዎች የፈጠሩት ስጋት

ባለፉት ጥቂት ዓመታት በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች ውስጥ የሚከሰቱ እገታዎች የሕዝቡ እና የመገናኛ ብዙኃን መነጋገሪያ ርዕስ ለመሆን ከበቁ ጉዳዮች መካከል አንዱ ነው።

የዜና ትንታኔ

BBC Amharic

7/5/2023

ባለፉት ጥቂት ዓመታት በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች ውስጥ የሚከሰቱ እገታዎች የሕዝቡ እና የመገናኛ ብዙኃን መነጋገሪያ ርዕስ ለመሆን ከበቁ ጉዳዮች መካከል አንዱ ነው።

አልፎ አልፎ በተለያዩ አካባቢዎች ይፈጸም የነበረው እገታ አሁን መልኩን ቀይሮ በአብዛኛው የአገሪቱ ክፍል ማጋጠሙን የሚገልጹ መረጃዎች እየወጡ ነው።

ከቤት ሠራተኞች እስከ ታጣቂዎች ድረስ ይህ ለገንዘብ ሲባል የሚፈጸመው እገታ በርካቶችን ለማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ምስቅልቅል ዳርጓል።

ታጋቾችን ለማስለቀቅ ከጥቂት ሺህ ብሮች ጀምሮ እስከ ሚሊዮኖች ድረስ ለመክፈል የተገደዱም በርካቶች ናቸው።

(በዚህ ጽሑፍ ለባለታሪኮቹ ደኅንነት ሲባል ማንነታቸውን ሊገልጹ ወይንም ሊጠቁሙ የሚችሉ መገለጫዎችን ቀይረናል ወይም አስቀርተናል።)

ታሪክ አንድ - ከተማ

ከእገታው ጥቂት ቀናት በፊት ለመጀመሪያው ባለታሪካችን ከማያውቀው ቁጥር ስልክ ይደወላል። “200 ሺህ ብር አምጣ” የሚል ትዕዛዝ ይተላለፋል። ቀልድ መሰለው። የማያውቀው ሰው ነው ደውሎ 200 ሺህ አዘጋጅ ያለው።

እሱ፡ ታዲያ እንዴት ብሩን ልስጣችሁ? [እየቀለደ]

እነሱ፡ አዘጋጅ ብቻ እኛ እንዴት እንደምንቀበልህ እናውቃለን። [አምርረው]

ህጻናት መታገታቸውን ሰምቷል። አንድ ወጣት ልጅም ታግቶ ብር ከፍሎ ተለቀቀ ሲባልም ሰምቷል። አንዳንዶች ደግሞ ወጣቱ በእጁ የነበረውን ብር አጥፍቶ በአጋቾች አመካኝቶ ነው ሲሉ ተናገሩ። ይህ ነው እንዲዘናጋ አደረገው።

አምስት ቀን ሰጡት። ቀልድ ስለመሰለው ረሳው። እነሱ የምራቸውን ስለሆነ አልረሱትም።

እነሱ መረጃ ነበራቸው። እሱ ምንም መረጃ ለውም። እነሱ ገቢውን እና ሌሎች የገንዘብ ምንጮቹን ያውቃሉ። ስለእነሱ ግን ምንም መረጃ የለውም።

ስድስተኛው ቀን ቅዝቅዝ ብሎ ጉም ተከናንቦ ነው የጀመረው። ብዙ ሰው የአልጋውን ሙቀት ለቅቆ መንገድ ላይ ውር ውር ሲል አይታይም። ግድ የሆነባቸው ጥቂቶች ብቻ ደራርበው ወዲያ ወዲህ ይላሉ።

ከቤት ወጥቶ ጥቂት እርምጃዎችን ከመራመዱ አምቡላንስ የምትመስል መኪና መጥታ አጠገቡ ቆመች። በፍጥነት ከውስጥ ሰዎች ወርደው ‘ይቅርታ ይቅርታ’ እያሉ በኋላ በር አስገቡት። ይህ ሲሆን ያየው ሰው የለም።

‘አውርዱኝ፣ አውርዱኝ’ እያለ ለመታገለ ሞከረ። በኋላ ላይ ስላፈኑት ትግሉን አቆመ። በቤቱ አጠገብ ይዘውት ሲያልፉ ትዝ ይለዋል። በኋላ ግን ራሱን ሳተ። ሲነቃ የት እንዳለ አያውቀውም። ቀዝቃዛው አየር ተቀይሮ ሞቃታማ ቦታ ደርሷል። ከሞቀ ቤቱ የወጣበት ዓላማ ተቀይሮ ቆርቆሮ ቤት ተከረቸመበት። ከቅርብ ወፍ ጩኸት ከርቀት ደግሞ የቤተክርስቲያን ቅዳሴ ብቻ ነው የሚሰማው።

በመጀመሪያው ቀን የኤቲኤም ካርዱን ወሰዱ። ማለፊያ ቁልፉን (ፓስዎርድ) በወረቀት አጻፉት። የቤቱን ቁልፍ ተረከቡ። ከመኪናውን ቁልፍ አንዱን ተቀብለውት ነበር።

በመጀመሪያው ቀን አብዛኛውን ብር ከቤትም፣ ከኤቲኤም ማሽንም ወሰዱ። ከእሱ እንጠብቃለን ካሉት ገንዘብ ጥቂት ብቻ ቀራቸው።

እነሱ፡ ቀሪውን ብር ክፈል?

እሱ፡ ልቀቁኝ እና ልክፈል

ለቀሪው ብር ግን ቀናትን አብሯቸው ለማሳለፍ ተገደደ።

መጀመሪያ በአምቡላንስ ይዘውት ከሄዱት ውስጥ አንዱ ብቻ መሣሪያ ይዞ ይጠብቀው ነበር።

“ፊታቸውን ባየው አሁን እለያቸዋል። ከዚያ በፊት ግን ምንም የማውቃቸው ሰዎች አይደሉም” ብሏል።

አልፎ አልፎ ያወሩለታል። አንዳንድ ቦታዎች ላይ እንዴት ዝርፊያ ሊፈጽም እንደሚችል ጥያቄ አቀርቦለታል።

ከአጋቾቹ ጋር በነበረው ቆይታ ከፖለቲካ ፓርቲም ሆነ ከታጣቂ ኃይሎች ጋር ግንኙነት አላቸው እንዲል ምክንያት ሆነው ነገር አላገኘም።

አንዳንዶች በሚናገሩት ቋንቋ እንዲህ ናቸው እንዲያ ናቸው ለማለት ቢፈልጉም፣ እሱ ግን ከዚህ ራሱን ቆጠብ ያደርጋል። እነሱ አማርኛ እና ኦሮሚኛ ያወራሉ እሱም ሁለቱንም ቋንቋ ይችላል።

“አንተ እንደዚህ ነህ፣ እንደዚያ ነህ ያሉኝ ነገር የለም ቀጥታ ስለ ብር ነው የጠየቁኝ። ጉዳያቸው ከብር ጋር የተገናኘ ነው። ምንም ከፖለቲካ ጋር የተገናኘ አይደለም፤ ብር እና ብር ብቻ ነው የጠየቁኝ” ሲል ይገልጻል።

ፖሊሶች እና ኃላፊዎች ይደውሉላቸው ነበር።

ለቀናት ሊለቁት ያልፈለጉት ታጋቾች በመጨረሻም ፊቱን ሸፍነው ሌላ ከተማ መግቢያ ላይ ጥለውት ሄዱ።

በለቀቁት ሰዓት ደሙ በጣም ወርዶ ነበር። አስር ቀን ሲቆይ ዳቦ እና ሙዝ ነው የሚሰጡት። ለጥቂት ቀናት ነበር ውሃ ያገኘው። ይህ ተደማምሮ ነው ደሙ እንዲወርድ ምክንያት የሆነው።

እንደዚያም ደካክሞ ሳይውል ሳያድር ለሚመለከታቸው አካላት ሪፖርት ለማድረግ አልቦዘነም። ከእገታው በኋላ ብዙ ነገር ሰምቷል። አንዳንዶች ታግቶ ነው ሲሉ ሌሎች ደግሞ ወንዝ ውስጥ ጭምር ሲፈልጉት ነበር።

ፖሊስ ጣቢያ ሲደርስ በርካታ ሰዎች በእሱ ምክንያት ታስረዋል። ታግቶ ከሆነ በሚል ከእሱ ጋር ግንኙነት ያላቸው ሰዎች ናቸው የታሰሩት።

አጋቾቹም ሲለቁት መረጃ እንዳይሰጥ አስጠንቅቀውታል። ድጋሚ ካገኙት እንደሚገሉት ዝተውበታል። “እኔን እና አኔን ብቻ ነው ያስፈራሩኝ። ስለገንዘብ ብቻ ነው ያወሩኝ። የትም ቦታ ብትሆን እንመጣለን ብለውኛል” ይላል።

በዚህ ምክንያት ከተለቀቀበት ደቂቃ ጀምሮ በጥንቃቄ ነው የሚንቀሳቀሰው።

አሁን ጨርቄን ማቄን ሳይል ከተማዋን ለቆ ወጥቷል። ከእዚያ ከተማ የሚያውቁት ሰዎች ሲደውሉለትም ስልካቸውን አያነሳም። የማያቀውንም ስልክ አያነሳም። ከባድ ሥነ ልቦናዊ ጉዳት እንደደረሰበት ይናገራል።

ታሪክ ሁለት - ገጠር

የምዕራብ ሸዋ ነዋሪ የሆኑት አቶ አቶ ጫሊ ዋቅወያ የ10 ልጆች አባት ናቸው።

አቶ ጫሊ ዋቅወያ በምዕራብ ሸዋ ነዋሪ ሲሆኑ የ10 ልጆች አባት ናቸው።

ጨርቄን ማቄን ሳይሉ ከቤታቸው ተሰደው ከሚገኙበት አነስተኛ ከተማ ሆነው ነው ቢቢሲ ያናገራቸው።

የሕይወታቸው ምስቅልቅል የጀመረው ምሽት ላይ ነው። በሠላም አሳድረኝ ብለው በተኙበት ታጣቂዎች ከደጃቸው ደረሱ።

ያገኙትን ዱላ አንስተው ራሳቸውን እና ቤተሰባቸውን ለመከላከል ሞከሩ። የምሽቱ “እንግዶች” ግን ጠመንጃ የታጠቁ በመሆናቸው አልቻሉም።

“የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት አባል ነን አሉኝ። ሹሩባ ተሰርተዋል። ከአካባቢው ሽፍቶች ይለያሉ። ከእነሱ መካከል አንዱ ብቻ ሽጉጥ ሲይዝ ቀሪዎቹ ስድስቱ ክላሽንኮቭ ይዘዋል። በዚህ ምክንያት ነው እነሱ (የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት) መሆናቸውን ያወቅኩት” ብለዋል ለቢቢሲ።

ቀጣዩ ጥያቄ ገንዘብ አምጣ የሚል ነው።

“‘100 ሺህ ብር አምጣ’ አሉኝ። ‘ይህን ያህል ገንዘብ የለኝም’ አልኳቸው። ‘ካልፈለክ ጭንቅላትህን እንበትናለን’ አሉኝ፝” ሲሉ ያስታውሳሉ።

ታጣቂዎቹ አቶ ጫሊን ሚሊሻ ነበርክ፣ በአካባቢው ያሉ ወጣቶችን አሰቃይተሃል የሚል ክስ ቢኣርቡባቸውም፤ “እኔ ግን ይህን አልፈጸምኩም ብዬ ተናገርኩኝ” ይላሉ።

በርካታ ቤተሰብ እንዳላቸው እና የሚያግዛቸው እንደሌለ በመግለጽ ደጋግመው ለምነዋል። ታጣቂዎቹ ግን ጆሮ ዳባ ልበስ ብለው 10 ከሚደርሱ ሌሎች ታጋቾች ጋር ይዘዋቸው ከአካባቢው ተሰወሩ።

ታጣቂዎቹ ገንዘቡን እንዲከፈላቸው ካልሆነ እንደሚገድሏቸው ደጋግመው ይዝቱባቸው ጀመር። መልዕክት ለቤተሰብ ደረሰ። ቤተሰብም ገንዘብ ማሰባሰብ ጀመረ።

የአቶ ጫሊ ባለቤት ህመምተኛ የነበረችው ሲሆን ባለቤቷን ለማዳን ከቤተሰብ እና ከጎረቤት ገንዘብ ማሰባሰብ እና መበደር ጀመረች። ሰንጋዎችን ሸጡ። የተባለው 100 ሺህ ብር ግን አልተሟላም።

መጀመሪያ ላይ 75 ሺህ ብር መሰብሰብ ብትችልም፣ ታጣቂዎቹ የጠየቁት ካልሞላ አንቀበልም በማለታቸው፣ ከፊል መሬታቸውን ለማከራየት ከፊሉንም ለመሸጥ ተገደዱ።

ቤተሰብ አቶ ጫሊን ለማስለቀቅ ያለውን ሁሉ አሟጦ ታጣቂዎች የጠየቁትን ብር ካሟላ በኋላ ተለቀው ወደ ቤታቸው ተመለሱ።

“አጋቾቹ ኦሮሞ አማራ አይሉም ሁሉንም ይይዛሉ” የሚሉት አቶ ጫሊ፣ ገንዘቡ ይለያይ እንጂ የአካባቢውን ነዋሪዎች አግተው እንደሚያስከፍሉ ይናገራሉ።

አቶ ጫሊ ከእገታው በኋላ ወደ ቀዬያቸው ቢመለሱም ችግሩ በዚህ የሚያበቃ አልሆነም።

ታጣቂዎቹ ብር ከወሰዱ በኋላ በአካባቢው 11 ሰዎችን ይዘው መግደላቸውን ጠቅሰው “እኔም ለሕይወቴ ስለሰጋሁ ቤተሰቦቼን ይዜ ወደ ከተማ ተሰደድኩ” ብለዋል።

በምሽት የተጀመረው እገታ በሬያቸውን እና ግማሽ ማሳቸውን አስጦ ግማሹን ደግሞ ለኪራይ ዳርጎ ከቤታቸው እንዲሰደዱ በማድረግም ሊጠናቀቅ አልቻለም።

ታጣቂዎቹ እየደወሉ እንደሚገድሏቸው ስለሚዝቱባቸው የሸሹበት ቦታ እንኳን ደኅንነት አይሰማቸውም።

በቅርቡ ደግሞ ዘግተው የወጡት ቤታቸው በታጣቂዎች መቃጠሉን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

“አሁን ልጆቹም የሚለብሱት እንኳን አጥተው ተርበው ችግር ላይ ናቸው” የሚሉት አቶ ጫሊ በሐዘን ተውጠው “የማስተዳድራቸው ቤተሰቦቼ በሰው ቤት ራቁታቸውን ናቸው” ብለዋል።

ፖሊስ ምን ይላል?

ይህ ከጊዜ ወደ ጊዜ ከገጠር አካባቢዎች ወደ ከተሞች አድማሱን እያሰፋ የመጣው የእገታ ድርጊት፣ በሁሉም አካባቢ የሕዝቡ ዋነኛ የስጋት ምንጭ ሆኗል።

በፌደራል መንግሥት እና ክስተቱ በተደጋጋሚ እየተከሰተባቸው ያሉት የክልል አስተዳደሮች አስካሁን ስለዚህ አሳሳቢ ጉዳይ እምብዛም ሲናገሩ አይሰማም።

ስለዚህም የታገተ የቤተሰብ አባል ያላቸው ሰዎች ብቸኛው አማራጫቸው አቅማቸው በቻለው ያላቸውን አሟጠው እና እዳ ገብተው አጋቾች የሚጠይቁትን በመክፍል እያስለቀቁ ይገኛሉ።

ቢቢሲ ይህንን ክስተት በተመለከተ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን የኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተር የሆኑትን አቶ ጄላን አብዲ ጠይቋል።

አቶ ጄይላን ይህ ጉዳይ ጥንቃቄ እንደሚያስፈልገው በመግለጽ “ለምሳሌ ኦነግ ሸኔ ባለፈው ይህን ድርጊት ፈፅሟል። ሾፌሮችን አግቷል። እና በተለያየ መንገድ ሊከሰቱ የሚችሉ ችግሮች ይኖራሉ” ብለዋል።

(ቢቢሲ በታገቱት ሾፌሮች ጉዳይ የአንድ አሸክራከሪ አባትን አነጋግሮ “የልጄን ሕይወት በአንድ ሚሊዮን ብር ገዛሁ” ስለማለታቸው ዘገባ መሥራቱ ይታወሳል።)

አክለውም “እነዚህ ሽፍቶች ከመከላከያ ወይም ከፖሊስ ጋር ፊት ለፊት የሚታኮሱ አይደሉም። ተደብቀው ሕዝብ ላይ ችግር የሚፈጥሩ ናቸው። ይህንን መከላከል የምንችለው ከሕዝብ ጋር ነው። ፖሊስ ብቻውን ሁሉንም አይችልም” ብለዋል።

ነገር ግን የእገታ ድርጊቶች ተበራክተዋል የሚል መረጃ እና ድምዳሜ እንደሌላቸው የሚናገሩት ዳይሬክተሩ “በየጊዜው ለፖሊስ የሚደርሱ መረጃዎች አሉ። ከአምና ጨምሯል አልጨረም የሚለውን ስናይ እኛ የጨመረ ነገር አልተመለከትም። ሰው በግምት ወንጀል ጨምሯል ሊል ይችላል። ከጠቅላላ የአገሪቷ ሁኔታ ሲታይ ግን ወንጀል እየቀነሰ ነው እየመጣ ያለው። እንደጠቅላላ በሃገር ደረጃ የተሻለ ነገር እየተፈጠረ ነው” መሆኑን ይናገራሉ።

እነዚህ በየጊዜው መፈፀማቸውን እየሰማን ያለነው እገታዎች እና የገንዘብ ክፍያዎች በስፋት በየትኞቹ ክልሎች እየተስተዋሉ ይሁን የሚል ጥያቄ ያቀረብንላቸው አቶ ጄላን “በክልሎች ደረጃ በዚህ ክልል ጨምሯል ወይም እዚህ ቀንሷል የሚል አልተጠናም። በአጠቃላይ ግን እገታ ጨምሯል የሚል ሐሳብ የለኝም። የመረጃ ትንተና ሊደርሰን ይገባል። እዚያ ደረጃ ላይ ለመድረስ ገና ሪፖርት እየተዘጋጀ ነው ያለው” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።

“ሆኖም ግን በወለጋ መስመር ሸኔ በሚንቀሳቀስባቸው አካባቢዎች [ያሉ ስጋቶችን] ሕዝቡም ያውቃል። ስለዚህ ሰዎች ሲንቀሳቀሱ ዝም ብሎ ከመሄድ ይልቅ ከፀጥታ አካላት መረጃ መውሰድ ያስፈልጋል። በተለይም ሸኔ በሚንቀሳቀስባቸው አካባቢዎች ላይ ዝም ብሎ መንቀሳቀስ ልክ ሹፌሮቹ ላይ እንዳጋጠመው አደጋ ላይ ሊጥል ይችላል” በማለት ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ፖሊስ የህብረተሰብ ደህንነት ከማስጠበቅ አንፃር ለሚነሳበት ቅሬታ ምላሽ የሰጡት የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን የኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተሩ አቶ ጄላን “ሁለት ሦስት ክስተቶችን መነሻ በማድረግ ሠላም የለም ብሎ ድምዳሜ ላይ መድረስ አይቻልም። ፖሊስ ሌት ተቀን ይንቀሳቀሳል። ማንኛውም ሠላማዊ የተባለ አገር ውስጥ ወንጀል ይፈጸማል” በማለት እያጋጠመ ያለው ችግር ከቁጥጥር የወጣ አለመሆኑን ይናገራሉ።