በአዲስ አበባ እና በሸገር ከተሞች ከ111 ሺህ በላይ ቤቶች መፍረሳቸውን ኢሰመጉ አስታወቀ

በአዲስ አበባ እና በኦሮሚያ ክልል ሸገር ከተሞች እየተካሄደ ነው ባለው የቤት ፈረሳ እና የግዳጅ የማስነሳት ሂደት 111 ሺህ 811 ቤቶች መፍረሳቸውን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ (ኢሰመጉ) አስታወቀ።

አበይት ጉዳይየዜና ትንታኔ

editors

6/1/2023

በአዲስ አበባ እና በኦሮሚያ ክልል ሸገር ከተሞች እየተካሄደ ነው ባለው የቤት ፈረሳ እና የግዳጅ የማስነሳት ሂደት 111 ሺህ 811 ቤቶች መፍረሳቸውን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ (ኢሰመጉ) አስታወቀ።

ኢሰመጉ ይህንን የገለጸው ከጥቅምት 2015 ዓ.ም. ጀምሮ በጉዳዩ ላይ ያካሄደውን የምርመራ ሪፖርት ግንቦት 23/2015 ዓ.ም. ይፋ ባደረገበት ጊዜ ነው።

ኮሚሽኑ ይህንን አሃዝ ይፋ ያደረገው በአዲስ አበባ እና በሸገር ከተሞች ከሚኖሩ ነዋሪዎች የደረሰውን አቤቱታ፣ እንዲሁም አቤቱታ አቅራቢዎች በተወካዮቻቸው በኩል ያቀረቡት መረጃዎች መሠረት በማድረግ ነው።

ባለሥልጣናት ሕገወጥ በማለት ባካሄዱት የማፍረስ ድርጊት ከመኖሪያ ቤቶች በተጨማሪ የእምነት ተቋማት መፍረሳቸውንም ሪፖርቱ አመልክቷል።

ኢሰመጉ ከኦሮሚያ ክልል የእስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት አገኘሁት ባለው የቃል መረጃ መሠረት ከ19 በላይ መሰጂዶች መፍረሳቸውን ጠቅሷል።

ኢሰመጉ በዚህ ሪፖርቱ በርካታ ቦታዎችን ላካሄደው የምርመራ ሥራው መሸፈኑን አስታውቋል።

ከእነዚህም መካከከልም በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እና በኦሮሚያ ክልል ሸገር ከተማ አስተዳደር ውስጥ የሚገኙ ኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ወረዳ 03 ልዩ ስሙ ሌንጮ ሰፈር፣ ማርያም ሰፈር እና ፋኑኤል ቤተክርስቲያን ሰፈር ይገኙበታል።

በተጨማሪም በየካ ክፍለ ከተማ በተለምዶ አንቆርጫ ገብርኤል፣ በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 11 በተለምዶ አሳማ እርባታ፣ ለገጣፎ ለገዳዲ 44 ማዞሪያ፣ ለገዳዲ የውሃ ግድብ ኬላ እና ሥላሴ እንዲሁም ኦሮምያ ክልል አዳማ ከተማ ቦኩ ሸነን ተጠቅሰዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በኦሮሚያ ክልል የሸገር የከተማን ጨምሮ ከ600 በላይ ከተሞች ሕገወጥ የቤት ግንባታ ላይ እርምጃ እየተወሰደ መሆኑን የኦሮሚያ ክልል ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ኃይሉ አዱኛ ረቡዕ ግንቦት 23/ 2015 ማስታወቃቸውን የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

የከተሞችን ፕላን ለማስጠበቅ እና በሕገወጥ መልኩ የተያዙ መሬቶችን ለማስመለስ አቅዷል በተባለው በዚህ ፈረሳ፣ ሕገወጥ ግንባታ አስፋፍተዋል የተባሉ አመራሮችም በሕግ ተጠያቂ ይሆናሉ ተብሏል።

እነዚህ ፈረሳዎች ብሔር እና ሃይማኖት ላይ ያነጣጠረ ነው መባሉን አስመልክቶ ምላሽ የሰጡት አቶ ኃይሉ፣ ሕግን እና ሥርዓትን በተከተለ መልኩ እየተከናወነ እንደሆነ እንዲሁም ሕገወጥ ቤቶች ላይ ያነጣጠረ ብቻ መሆኑን ገልጸዋል።

ኢሰመጉ በበኩሉ የቤት ፈረሳው የተለያዩ ቤቶችን እንደሚያካትት እና ከእነዚህም መካከል የባለይዞታነት ማስረጃ (እንደ አየር ካርታ) ያላቸው ቤቶች መካተታቸውን ገልጿል።

በተጨማሪ ከፈረሱት መካከል ከገበሬ ላይ በኢመደበኛ መልኩ የተገዙ መሬቶች ላይ የተሰሩ ቤቶች፣ አዋጅ ቁጥር 721/2004 ከመውጣቱ በፊት የተያዙ እና ግንባታ የተደረገባቸው ቤቶች (ከእነዚህም መካከል በሕጉ መሠረት ወደ መደበኛ ይዞታነት እንዲዞሩ ከመንግሥት አካላት ጋር ሲነጋገሩ የነበሩ እና በመጠባበቅ ላይ የነበሩ) እንደሚገኙበት ተካትቷል።

የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) በበኩሉ “ሕገወጥ አሰራርን ተከትሎ ሕግን ማስከበር አይቻልም” በሚል ግንቦት 23/ 2015 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ በሸገር ከተማ እየተካሄደ ያለው የቤቶች እና የእምነት ተቋማት ፈረሳ “ሕጋዊነትን ያልተከተለ ነው” ሲል ተችቶታል።

በተጨማሪም “በተሳሳተ ፖሊሲ ላይ የተመሰረተ፣ ወቅታዊነትን ያላገናዘበ፣ አማራጭ መፍትሄዎችን ያላካተተ፣ በአድሏዊ መንገድ እየተፈፀመ ያለ እና ብዙ ሺህ ዜጎችን ለማኅራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ያጋለጠ ሕገወጥ ተግባር” ነው ሲልም ኮንኖታል።

“በሸገር ከተማ ብዛት ያላቸው መስጂዶች፣ ቤተ ክርስቲያኖች እና የፕሮቴስታንት ቤተ እምነቶች የሃይማኖት መብቶችን በሚዳፈር እና የአማኞችን ክብር በሚነካ መንገድ በአፍራሽ ግብረ ኃይል በግዳጅ እንዲፈርሱ ተደርገዋል” ብሏል።

ኢሰመኮ ከዚህ ቀደም የቤት ፈረሳው ሂደት ተገቢ ልየታ ያልተደረገበት ስለመሆነ፣ ያለበቂ ቅድመ ማስጠንቀቂያ፣ አድሎአዊ እርምጃ ስለመኖሩም በሪፖርቱ ማካተቱ ይታወሳል።ኢሰመጉ ሪፖርቱን ለማጠናቀር በአካል በመገኘት ምልከታዎችን በማድረግ፣ ከተጎጂዎች ጋር በመነጋገር እና ከተጎጂች ቃል በመቀበል መረጃዎችን ለማሰባሰብ መሞከሩን ገልጾ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፣ ኦሮሚያ ክልል እና ሸገር ከተማ አስተዳደር ባለስልጣናት በኩል መረጃ ለማግኘት ሞክሮ እንዳልተሳካለት ገልጿል።

በዚህ ሪፖርት ውስጥም የደረሱ ሰብዓዊ መብት ጥሰቶችም ተካትተዋል።

በኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ከፈረሰባቸው መካከል ቦታውን ከገዙ አስራ ስምንት ዓመት የሞላቸው፣ አብዛኛዎቹ ነዋሪዎች መንገድ እና ድልድይ በመዋጮ የገነቡ እንዲሁም መብራት እና ውሃ የመሳሰሉ መሠረተ ልማቶችን አስገብተው ሲከፍሉ መቆያታቸው ተጠቅሷል።

ምንም ዓይነት ማስጠንቀቂያም ሳይደርሳቸው ቤቶቻቸው መፍረሱን እና ለተለያዩ የኢኮኖሚዊ፣ ማኅበራዊ እና የሥነ ልቦናዊ ቀውሶች መዳረጋቸውን ከአቤቱታ አቅራቢዎቹ መስማቱን ኢሰመጉ አመልክቷል።

በኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ወረዳ 3፣ ከ10 ሺህ በላይ የሚሆኑ ቤቶች እንደፈረሱም ቅሬታ አቅራቢዎቹ ለኢሰመጉ ገልጸዋል።

ቤቶችን በማፍረሱ በኩል የኦሮሚያ ልዩ ኃይል እና የፖሊስ አባላት ተሳትፈዋል የተባለ ሲሆን፣ ግሰለቦቹ ንብረታቸውን ለማውጣትም ጊዜ ሳይሰጣቸው ከነእቃቸው በግሬደር የፈረሰባቸው አሉ ተብሏል።

ቤቶች በሚፈርሱበት ወቅት ድብደባዎች እና እስራቶች ስለመፈጸማቸው እንዲሁም ለኦሮሚያ ክልል እና ለአዲስ አባባ ከተማ አስተዳደር ቅሬታቸውን ቢያቀርቡም ምላሽ ያላገኙ፣ ይህንን በማድረጋቸው የታሰሩም እንዳሉ የመብት ድርጅቱ ከአቤቱታ አቅራቢዎቹ መረጃ ማግኘቱን ጠቅሷል።

ሌላኛው በዚህ ሪፖርት የተካተተው በጠቅላይ ሚንስትር ጽ/ቤት አማካኝነት ሊሰራ ለታሰበው የጫካ ፕሮጀክት ይነሳሉ የተባሉ ቤቶች ጉዳይን ነው።

ለዚህ ፕሮጀክት በአዲስ አበባ ከተማ በየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 10 በተለምዶ አንቆርጫ ገብርኤል፣ ወረዳ 05፣ ወረዳ 12 ቀበሌ 2/21 በአሁኑ ለሚኩራ ክፍለ ከተማ ወረዳ 14 ቁሊቲ ቀጠና አካባቢ ያሉ ቤቶች እንደሚፈርሱ እና እንደሚነሱ እንደተነገራቸው ተጠቅሷል።

ከተለያዩ የመንግሥት አካላት ሕጉን በተከተለ መልኩ እንደሚነሱ ቃል ቢገባላቸውም ይህ ተፈጻሚ አልሆነም ማለታቸው ተጠቅሷል።

በዚህ የጫካ ፕሮጀክት ምክንያት ከሦስት ወረዳዎች በላይ ያለ ማስጠንቂቂያ ቤት መፍረስ፣ ሕገወጥ እስራት፣ በተለያዩ አካላት የቤት እቃ እና የቤት መስሪያ ቁሳቁሶች ስርቆት እንደተፈጸመባቸው እና ከእዚህ ጋር ተያይዞ ለእስር የተዳረጉ ሰዎች እንዳሉ ለኢሰመጉ ገልጸዋል፡፡

በለገጣፎ ለገዳዲ አቤቱታ አቅራቢዎቹ ብሔርን መሠረት ያደረገ ጥቃት እንደተፈጸመባቸው ገልጸዋል። በብሔር ተለይቶ ቤት መፍረስ፣ ንብረት መዘረፍ እና ያፈሩትን ንብረት ይዘው እንዳይንቀሳቀሱ እንዲሁም ቤት በአካባቢው እንዳይከራዪ እና ለእነሱም አከራይቶ የተገኘ ቤታቸው እንደሚፈርስ ማስፈራሪያ በመስጠት “አሳምጸውብን ከነቤተሰቦቻቸው ችግር ውስጥ ወድቀናል” ብለዋል።

በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ 01 ለቡ ኤርቱ ተክለሃይማኖት ሰፈር አንዳንድ ቤቶች በሌሊት እንደፈረሱ እና መጥረቢያ፣ ገጀራ፣ መዶሻ እና ትልልቅ አጠና የያዙ ወጣቶች እንደ አፍራሽ ግብረ ኃይል ተደራጅተው ማፍረስ መጀመራቸው እና ነዋሪዎቹም ንብረታቸውን ማውጣት ባለመቻላቸው አብሮ መውደሙንም ለኢሰመጉ ተናግረዋል።

ከእነዚህም ውስጥ አንዳንዶቹ የአየር ካርታ የነበራቸው ናቸው ተብሏል።

ለምን ይፈርሳል ብለው የጠየቁ ነዋሪዎች መደብደባቸውን፣ “መጤ የሚሉ እና የተለያዩ የጥላቻ ንግግሮች፣ ስድብ እና ዘለፋዎችን” ማስተናገዳቸውንም ኢሰመጉ አቤቱታ አቅራቢዎቹን ዋቢ አድርጎ በሪፖርቱ አካቷል።

በአዳማ ከተማ ቤት ከፈረሰባቸው መካከል በጸዴቻ አራራ ቀበሌ 04/ በ1985 ዓ.ም. ጀምሮ ከኤርትራ ወደ ከተማዋ በመግባት የመኖሪያ ፍቃድ በመጠየቅ ቦታ ተመርቶላቸው ቤት ሰርተው ይኖሩ የነበሩ 14 ቤቶች መፍረሳቸው ተገልጿል።

ግለሰቦቹ በእነዚህ ቤቶች ከ28 ዓመት በላይ የኖሩ ሲሆን የከተማ አስተዳደሩ ግንቦት 10 /2014 ዓ.ም. ሕገወጥ ናችሁ በሚል ማፍረሱን ነዋሪዎቹ የተናገሩ ሲሆን፣ ኢሰመጉም በስፍራው በመሄድ የቤቶቹን መፍረስ ማረጋገጡን አስታውቋል።

ኢሰመጉ ሕዝቡን ማወያየት፣ ጊዜያዊ መጠለያዎችን ማቅረብ፣ ምትክ መኖሪያዎችን መስጠት እንዲሁም መንግሥት ቤት የማፍረስ እና በግዳጅ የማፈናቀል እንቅስቃሴዎች በሚፈጸሙ ወቅት ሰዎች ቤት አልባ እንዳይሆኑ እና ለሌሎች ሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች ተጋላጭ እንዳይሆኑ ማናቸውንም እንዲወሰድ፣ ዓለም አቀፍ ድንጋጌን እንዲያከብር አማራጭ ሃሳብ አቅርቧል።

ተቃዋሚው የኦሮሞ ፌደራሊስ ኮንግረስ (ኦፌኮ) በበኩሉ፣ የሸገር ከተማ አስተዳደር እና የኦሮሚያ ክልል መንግሥት የግል ቤቶችን እና የእምነት ተቋማትን የማፍረሱን ተግባር በአፋጣኝ አቁሞ በሕጋዊነቱ እና በአተገባበሩ ዙሪያ እየተስተዋሉ ያሉ ክፍተቶችን እንደገና እንዲፈትሽ ጠይቋል።

የሸገር ከተማን ጨምሮ የከተሞች ልማት እና መሪ ዕቅዶች የሕዝቡን የመኖሪያ ቤት የማግኘት ሰብዓዊ መብት እና የሃይማኖት ተቋማትን የማደራጀት መብት ባገናዘበ መልኩ ብዝሃነትን ባከበረ እና ፍትሃዊነትን በተላበሰ መንገድ እንዲቀረፅም ጥሪ አቅርቧል።