መስከረም አበራ ለሶስተኛ ጊዜ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ዋለች

አበይት ጉዳይ

4/9/20232 min read

“ኢትዮ ንቃት” የተሰኘው የዩ-ቲዩብ መገናኛ ብዙኃን መስራች እና ባለቤት የሆነችው መስከረም አበራ፤ ዛሬ እሁድ ሚያዝያ 1 አመሻሽ ላይ በፌደራል ፖሊስ በቁጥጥር ስር መዋሏን ባለቤቷ አቶ ፍጹም ገብረ ሚካኤል ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናገሩ። መስከረም በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ለእስር ስትዳረግ የዛሬው ለሶስተኛ ጊዜ ነው።

በራሷም ሆነ በሌሎች መገናኛ ብዙኃን በምታቀርባቸው የፖለቲካ ትንታኔዎች ይበልጥ የምትታወቀው መስከረም፤ በአዲስ አበባ ጎሮ አካባቢ ከሚገኘው መኖሪያ ቤቷ በቁጥጥር ስር የዋለችው 10 ገደማ በሚሆኑ የፌደራል ፖሊስ አባላት መሆኑን አቶ ፍጹም ገልጸዋል። መስከረም በቁጥጥር ስር ከመዋሏ በፊት፤ በመኖሪያ ቤታቸው 50 ደቂቃዎች ገደማ የወሰደ “ብርበራ” መደረጉን ባለቤቷ ተናግረዋል።

ሲቪል እና የፌደራል ፖሊስ የደንብ ልብስ የለበሱ “የታጠቁ” የጸጥታ አካላት፤ መጀመሪያ “ለፍተሻ ነው የመጣነው” ሲሉ መናገራቸውን አቶ ፍጹም አስታውሰዋል። “የፍርድ ቤት ማዘዣ ይዛችኋል ወይ?” የሚል ጥያቄ ማቅረባቸውን የሚያነሱት አቶ ፍጹም፤ ሆኖም የፌደራል ፖሊስ አባላቱ “በemergency ጊዜ ፍተሻ ይደረጋል። እኛ ደግሞ የፌደራል ፖሊስ አባላት ነን። መታወቂያም ማሳየት እንችላለን” ሲሉ ምላሽ ሰጥተውኛል ብለዋል።

ጎረቤቶቻቸው በተገኙበት ከተደረገው ፍተሻ በኋላ፤ ሶስት የመስከረም አበራ ረቂቅ ጽሁፎችን እና የእርሷን “ሳምሰንግ” ሞባይል እንደወሰዱ ባለቤቷ ገልጸዋል። ከፍተሻው መጠናቀቅ በኋላ በሁለት “ፒክ አፕ” ተሸከርካሪዎች የመጡት የጸጥታ አካላት፤ “ለጥያቄ ስለምንፈልግሽ በቁጥጥር ስር ውለሻል” ብለው እንደወሰዷት ባለቤቷ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አስረድተዋል።

ባለቤታቸው ወዴት እንደምትወስድ ጥያቄ ሲያቀርቡ፤ የፈለጋት “የአዲስ አበባ ፖሊስ ነው” የምል ምላሽ ማግኘታቸውን አቶ ፍጹም አክለዋል። መስከረም የምትወሰድበትን ለማረጋገጥ ከጸጥታ አካላቱ ጋር አብረው መጓዛቸውን የሚናገሩት አቶ ፍጹም፤ በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ዋና መስሪያ ቤት በሚገኘው ሶስተኛ ፖሊስ ጣቢያ ሲያስረክቧት መመልከታቸውን አብራርተዋል።

መስከረም በባለቤትነት የምታስተዳድረው “ኢትዮ ንቃት” የዩቲዩብ መገናኛ ብዙሃን፤ ከሶስት ወራት ስራ ማቋረጥ በኋላ እንደገና ከተከታታዮቹ ጋር ለመገናኘት የበቃው ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ መጋቢት 23፤ 2015 ነበር። ለመገናኛ ብዙሃኑ ስራ መስተጓጎል፤ የመስከረም እስር በምክንያትነት ተጠቅሷል። ባለፈው ታህሳስ ወር መጀመሪያ ላይ በቁጥጥር ስር ውላ የነበረችው መስከረም፤ “ጥላቻ፣ አመጽ፣ ሁከትና ግጭት በመቀስቀስ” በፌደራል ዐቃቤ ህግ ክስ ተመስርቶባታል። በዚያኑ ወር መጨረሻ፤ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የ50 ሺህ ብር በዋስትና በማስያዝ ጉዳይዋን በውጭ ሆና እንድትከታትል ውሳኔ በማስተላለፉ ከእስር ተፈትታለች።

ባለፈው ታህሳስ ወር መጀመሪያ ላይ በቁጥጥር ስር ውላ የነበረችው መስከረም፤ “ጥላቻ፣ አመጽ፣ ሁከትና ግጭት በመቀስቀስ” በፌደራል ዐቃቤ ህግ ክስ ተመስርቶባታል። በዚያኑ ወር መጨረሻ፤ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የ50 ሺህ ብር በዋስትና በማስያዝ ጉዳይዋን በውጭ ሆና እንድትከታትል ውሳኔ በማስተላለፉ ከእስር ተፈትታለች።

መስከረም አበራ ለመጀመሪያ ጊዜ በፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋለችው፤ ከአስራ አንድ ወራት ገደማ በፊት በግንቦት 2014 ዓ.ም ነበር። ፖሊስ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዋን የያዘው “ሁከት እና ብጥብጥ በማነሳሳት” ጠርጥሮ መሆኑን በወቅቱ ማስታወቁ አይዘነጋም። በዚህ ወቅት ለ25 ቀናት ያህል በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ዋና መስሪያ ቤት በእስር ላይ የቆየችው መስከረም፤ ምንም አይነት ክስ ሳይመሰረትባት በ30 ሺህ ብር ዋስትና ከእስር ተለቅቃለች።

Related Stories